የቱርክ ርዕደ መሬት፡ አስከሬኖች በየመንገዱ ወድቀዋል፤ እርዳታ ባለመቅረቡም ቁጣ እየተቀሰቀሰ ነው

አንታክያ ከተማ

በርዕደ መሬት በተመታው ደቡብ ቱርክ የነፍስ አድን ሥራው በቀጠለበት ወቅት በአደጋው የሞቱ ሰዎች አስከሬን በየመንገዱ ወድቆ መታየቱ ታውቋል።

በርዕደ መሬቱ በተጎዱት ቱርክ እና ሰሜን ሶሪያ ከስምንት ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።

ከሟቾቹ መካከል በሺህዎች የሚቆጠሩት ህጻናት ናቸው ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠንቅቋል።

ሰኞ ዕለት የደረሰው ርዕደ መሬት በሬከተር ስኬል 7.8 መመዝገቡ ታውቋል።

ቀጥሎ የደረሰው ንዝረትም ተቀራራቢ መጠን የነበረው ሲሆን ማዕከሉም ኤልቢስታን አውራጃ ነበር።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በርዕደ መሬቱ በተጎዱ 10 ክልሎች ለሦስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተላልፈዋል።

አዋጁ የእርዳታ ሠራተኞችን እና የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያግዝ ቢገልጹም ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ወደ 70 የሚደርሱ ሃገራት ድጋፍ ወደ ቱርክ ልከዋል። በቂ ድጋፍ አልተደረገልንም በሚል በአንዳንድ አካባቢዎች ቁጣ መቀስቀሱ ተነግሯል።

የደረሰው አደጋ ከእርዳታ ሠራተኞች እና አምቡላንሶች አቅም በላይ በመሆኑ በአንታክያ ከተማ አስከሬኖች ለሰዓታት በመተላለፊያዎች ላይ መቆየታቸው ታውቋል።

የቤተሰብ አባላት የጠፉ ዘመዶቻቸውን ሲፈልጉ ታይተዋል። የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በህይወት ያሉ ሰዎችን ማውጣት ላይ በማተኮራቸው አስከሬኖችን የማውጣት ኃላፊነት በቤተሰብ አባላት ላይ ወድል።

በቂ ድጋፍ አልተደረገም የሚል ቁጣም እየጨመረ ይገኛል። የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች 11 ሰዎች ይገኙበታል የተባለበተን የፈረሰ ህንጻ ፎቶ አንስተው ከመሄድ ውጭ ያደረጉት ነገር የለም በሚል አንዲት ነዋሪ ለቢቢሲ ገልጻልች።

ለሰዓታት ፍርስራሹ ስር ድምጽ ይሰማ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ጸጥ ማለቱን ተናግራለች።

ተራራማ ቦታዎች የሚበዙበት መንገድ አደጋውን በሚሸሹ ሰዎች በመጨናነቁ ከርዕደ መሬቱ ማዕከል በቅርብ ርቀት በምትገኘው ካህራማንማራስ ዕርዳታ በፍጥነት ሊቀርብ አልቻለም።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ከቀዝቃዛው ንፋስ እና ከፍርስራሾች ከሚነሳው አቧራ ጋር በመታገል ሥራቸውን ለማከናወን በመጣር ላይ ይገኛሉ።

ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ኑሯቸውን በመንገዶች ላይ ያደረጉ ሲሆን ብርዱን ለመከላከልም ዕቃዎችን እያቃጠሉ ይሞቃሉ። በዚህ ሳምንት ቅዝቃዜው ይበልጥ እንደሚጨምር ይጠበቃል።

በወደብ ከተማዋ ኢስኬንዴረንም ቤታቸው የወደመባቸው ሰዎች ከህንጻዎች ራቅ ብለው ለመጠለል እየሞከሩ ይገኛሉ።

አንዲት ሴት ከልጆቿ እና ከልጅ ልጆቿ ጋር መጠለያ ውስጥ እንደምትገኝ ለቢቢሲ ተናግራለች። የእርዳታ ሠራተኞች ከብርድ ልብስ እና ከዳቦ ውጭ ምንም ድጋፍ እንዳላደረጉላቸው አስታውቃለች።

“ደንግጫለሁ። ሁሉም ቦታ አስከሬኖችን እመለከታለሁ። በሥራዬ ምክንያት አስከሬን የማየት ልምድ ቢኖረኝም ይህ ለእኔ በጣም ከባድ ነው” ሲሉ አንድ የሕክምና ባለሙያ ለሬውተርስ ተናግረዋል።

በኢስኬንዴረንም ወደብ በደረሰ ከባድ እሳት ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ በመዘጋቱ በተጎጂዎች በመርብ የተጫኑ ድጋፎች አቅጣጫ እንዲቀይሩ ተገደዋል።

እሳቱ ነዳጅ በጫነ መርከብ ተከስቶ መስፋፋቱ ተነግሯል።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ወደ ቦታው ለመድረስ መቸገራቸው ታውቋል። በእሳት ማጥፊያ መርከብ ለመቆጣጠር የተደረገው ሙከራም አልተሳካም።

ኢስኬንዴረንም ወደብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በተለይም በተቃዋሚዎች በተያዙት የሶሪያ አካባቢዎችም ዕርዳታ ለማድረስ አስቸጋሪ መሆኑን ሪፖርቶች ጠቁመዋል። በእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ግጭቶችም በተደጋጋሚ ይከሰታሉ።

ከአደጋው በፊትም ቢሆን በቀዝቃዛ አየር፣ በወደመ መሠረተ ልማት እና በኮሌራ መስፋፋት ምክንያት አካባቢው ችግር ውስጥ ነበር። ሴቶችን እና ህጻናትን ጨምሮ ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቀድሞውንም ኑሯቸው የተመሠረተው በእርዳታ ላይ ነበር።

በመንገድ መጎዳት ምክንያት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደ ሶሪያ ዕርዳታ ማድረሱን ለጊዜው እንደሚያቋርጥ አስታውቋል። መቼ ይጀመራል ለሚለውም ምንም ምላሽ አልተሰጠም።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶሪያ ልዑክ ወደ አካባቢዎቹ የሚላከው እርዳታ በሃገሪቱ በኩል ብቻ እንዲላክ ጠይቀዋል። ይህ ግን ፖለቲካዊ አንድምታ አለው የሚል ምላሽ በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስራ ካሉ ባለስልጣናት ተደምጧል።

ከርዕደ መሬቱ በኋላ አንዳንድ ተስፋ ሰጪ መረጃዎችም ወጥተዋል። በስብርባሪዎች ውስጥ የተወለደ ህጻን በህይወት ሊወጣ ችሏል። ህጻኑ ሲገኝ ከእናቱ ያልተለያየ ሲሆን እናቱ ግን ህይወቷ አልፎ ነበር።