የቴሌግራም ሥራ አስኪያጅ በወንጀል በመጠርጠሩ ምክንያት ፈረንሳይን ለቆ እንዳይወጣ ታገደ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቴሌግራም መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ የሆነው ፓቬል ዱሮቭ በተከፈተበት ክስ መሠረት ምርመራ እንደተከፈተበት የፈረንሳይ አቃቤ ሕግ አስታወቁ።
ቴሌግራም በተሰኘው የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ ምክንያት የተደራጀ ወንጀል ተፈፅሟል በሚል ነው ዱሮቭ በቁጥጥር ሥር የዋለው።
የ39 ዓመቱ እሥር ቤት ባይገባም በሕግ አስፈፃሚ ዕይታ ሥር እንዲቆይ እና 5 ሚሊዮን ዩሮ ማስያዣ እንዲከፍል ታዟል።
ሩሲያ የተወለደው እና የፈረንሳይ ዜግነት ያለው ዱሮቭ በሳምንት ሁለት ጊዜ ፖሊስ ጣቢያ እንዲያመለክት እንዲሁም ፈረንሳይን ለቆ እንዳይወጣ ዕግድ ተጥሎበታል።
ባለፈው ቅዳሜ ነው ዱሮቭ በግል አውሮፕላኑ ወደ ፈረንሳይ አቅንቶ ገና መሬት ከመንካቱ ከቴሌግራም ጋር በተያያዘ ምርመራ ምክንያት በቁጥጥር ሥር እንዲውል የተደረገው።
የፓሪስ አቃቤ ሕግ ረቡዕ በለቀቀው መግለጫ ዱሮቭ በይፋ ምርመራ እንደተከፈተበት ገልጿል።
[ቴሌግራም ላይ ] በተደራጀ ቡድን ሕገ-ወጥ ድርጊት ሲደረግ ተባባሪ ሆኗል፤ ከባለሥልጣናት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አይደለም፤ እንዲሁም የሕፃናት ወሲባዊ ምስሎች በተደራጀ የወንጀል ቡድን ሲሰራጩ ተባባሪ ሆኗል የሚሉ ክሶች ናቸው የቀረቡበት።
በፈረንሳይ ሕግ መሠረት አንድ ምርመራ የተከፈተበት ሰው ወንጀለኛ ነው አሊያም ችሎት ፊት ይቀርባል ማለት አይደለም። ነገር ግን የፍርድ ቤቱ ዳኛ ጉዳዩን ተመልክተው ምርመራ እንዲቀጥል ሊያዙ ይችላሉ።
ዱሮቭ እስካሁን በቁጥጥር መዋሉን በተለመከተ አሊያም ስለተከፈተበት ክስ ምንም ያለው ነገር የለም።
ጠበቃው ዴቪድ-ኦሊቨር ካሚንስኪ እንዳሉት ቴሌግራም በአውሮፓ የዲጂታል ቁጥጥር መመሪያ መሠረት ነው የሚሠራው፤ አልፎም ልክ እንደሌሎች ማኅበራዊ ሚድያዎች ቁጥጥር ይደረግበታል ብለዋል።
ደንበኛቸው “በቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በወንጀል ድርጊት ተሳትፈዋል” መባሉን “የሚያስገርም ነው” ይላሉ።
የአንድ ማኅበራዊ ሚድያ ባለቤት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ብዙዎችን ያነጋገረ ሲሆን የንግግር ነፃነት እና ተጠያቂነትን በተመለከተ ሰዎች ለሁለት ተከፍለው ክርክር እያደረጉበት ይገኛሉ።
እርግጥ ነው የማኅበራዊ ሚድያ ባለቤቶች ሕግ አውጭዎች ፊት ቀርበው ምላሽ ሲሰጡ ቢታዩም በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው አያውቁም።
የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ ባለቤት የሆነው ኢላን መስክ ‘ይዘት መቆጣጠር’ የፕሮፖጋንዳ ቃል ነው ብሎ ዱሮቭ ከእስር ቤት እንዲለቀቅ በተደጋጋሚ ጠይቋል።
ራምብል የተባለው አወዛጋቢ የቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያ መሥራች የሆነው ክሪስ ፓቭሎቭስኪ ከዱሮቭ መታሰር በኋላ አውሮፓን ለቆ እንደሸሸ ተናግሯል።
በርካታ ማኅበራዊ ሚድያዎች ከሀገር ቤትም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንከር ያሉ እንደ የሕፃናት ወሲባዊ ምስሎችን ማጋራት ያሉ ክሶች ሲቀርቡባቸው ከመንግሥታት ጋር የሚተባበሩ ቢሆኑም ቴሌግራም ግን ይህን ችላ ብሏል ተብሎ ይወቀሳል።
ዋና መሥሪያ ቤቱ ዱባይ የሚገኘው ቴሌግራም ይዘትን የሚቆጣጠርባቸው ቴክኖሎጂ በኢንዱስትሪው ተቀባይነት ያላቸው ናቸው ይላል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማኽሮን በያዝነው ሳምንት መባቻ በሰጡት አስተያየት ሀገራቸው የንግግር ነፃነትን ለማስከበር ቁርጠኛ እንደሆነች ተናግረው የዱሮቭ በቁጥጥር ሥር መዋል “በፍፁም ፖለቲካዊ አይደለም” ብለዋል።
ቴሌግራም በአንድ ‘ግሩፕ’ ውስጥ እስከ 200 ሺህ ሰዎች እንዲጠቀሙ የሚፈቅድ ሲሆን ዋትስአፕ በተቃራኒው ከ1000 ሰዎች በላይ አይፈቅድም።
ሩሲያ “ያለምንም ማስረጃ” ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ማዋል አንድ የቴክኖሎጂ ኩባንያን ለፖለቲካ አላማ በመጠቀም እንደ “ማስፈራራት” ነው የሚቆጠረው ብላለች።
ቴሌግራም በዓለማችን በርካታ ተጠቃሚ ካላቸው ማኅበራዊ ሚድያዎች አንዱ ነው።
በ2013 የተመሠረተው ቴሌግራም መጀመሪያ ሰሞን በሩሲያ፣ ዩክሬን እና ኢራን እንዲሁም በቀድሞ የሶቪዬት ሕብረት ሀገራት ታዋቂ ነበር።
በ2014 ከመንግሥት የቀረበበትን ጫና በመሸሽ ሩሲያን ጥሎ የወጣው ፓቬል ዱሮቭ የሴይንት ኪትስ ኤንድ ኔቪስ እና የዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ዜግነት አለው።












