በቱርክ ርዕደ መሬት ሕይወቱን ያጣው የክርስቲያን አትሱ አስክሬን ወደ ጋና ተወሰደ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቱርክ እና ሶሪያ ባጋጠውም ርዕደ መሬት ሕይወቱን ያጣው እግር ኳስ ተጫዋቹ ክርስቲያን አትሱ አስክሬን ወደ ትውልድ አገሩ ጋና ተወሰደ።
የአትሱ እስክሬን በቤተሰብ አባላቱ እንዲሁም በቱርክ የጋና አምባሳደር ታጅቦ ጋና መዲና አክራ ሲደርስ የአገሪቱ ጦር የክብር አቀባበል አድርጎለታል።
ርዕደ መሬቱ ከተከሰተ በኋላ ለሁለት ሳምንታት ተጫዋቹን ለማግኘት ፍለጋ ሲደረግ ቢቆይም ከትናንት በስቲያ በመኖሪያ ቤቱ ፍርስራሽ ውስጥ ሕይወቱ አልፎ ተገኝቷል።
የመስመር ተጫዋቹ ለብሔራዊ ቡድኑ 65 ግዜ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን፤ እአአ 2015 ላይ ጋና ለአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ እንድትደርስም አስችሏል።
የ31 ዓመቱ ተጫዋች በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለቼልሲ፣ ኤቨርተን እና ኒውካስትል ጨምር ተጫውቷል።
የጋና ምክትል ፕሬዝዳንት ማሐሙዱ ባዋሚያ በአስክሬን አቀበባል ስነ-ስርዓት ላይ ተጫዋቹ በሕይወት እንዲገኝ ጸሎት ሲያደርጉ እንደነበረ ገልጸው በአትሱ ሕይወት ማለፍ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
ምከትል ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም የእግር ኳስ ተጫዋቹ ክብር የሚመጥን የቀብር ስነ-ስርዓት ይካሄዳል ብለዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡን ተከትሎ አትሱ “ጉዳት ደርሶበት ተርፏል” ሲል የሚጫወትበት ክለብ ሃታይስፖር አሳውቆ የነበረ ቢሆንም፤ በኋላ ላይ በተደረገ ማጣራት እግር ኳስ ተጫዋቹ አለመገኘቱ ተረጋግጦ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ 7.8 ማግኒቲዩድ የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባት ሃታይ ግዛት በሚኖርበት የጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ አስክሬኑ አልፎ ተገኝቷል።
እስካሁን ድረስ በቱርክ እና ሶሪያ ከ44ሺህ ሰዎች በላይ በርዕደ መሬቱ ሕይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።
አትሱ የመጨረሻ ጨዋታውን በፈረንጆቹ የካቲት 05/2023 ሲያደርግ ለክለቡ የማሸነፊያዋን ግብ አስቆጥሮ ነበር።
ክርስቲያን አትሱ ለኒውካስል ዩናይትድ 107 ጨዋታዎችን አድርጓል። ክለቡ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ከሊቨርፑል ጋር የነበረው ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ባለቤቱ እና ሦስቱ ልጆቹ በተገኙበት የሕሊና ጸሎት ተደርጎለታል።












