ቻይና መሳሪያ ለሩሲያ ልትሰጥ ትችላለች ስትል አሜሪካ አስጠነቀቀች

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ሩሲያ በዩክሬን እያደረገች ያለችውን ጦርነት ለመደገፍ ቻይና ጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ ለመስጠት እያጤነች ነው አሉ።

ብሊንከን ለሲቢኤስ ሲናገሩ የቻይና ኩባንያዎች ወታደራዊ ያልሆኑ ድጋፎችን ቀድሞውኑ ለሩሲያ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው፤ አሁን ላይ አሜሪካ ያላት መረጃ ቤጂንግ ወታደራዊ ድጋፍ ልታደርግ እንደምትችል ነው ብለዋል።

ቻይና የጦር መሳሪያ ድጋፉን ለሞስኮ የምታደርግ ከሆነ የሚጠብቃት ምላሽ አደገኛ ይሆናል ሲሉ ብሊንከን አስጠንቅቀዋል።

ቻይና በበኩሏ ከሞስኮ ወታደራዊ ድጋፍ ቀርቦላታል የሚሉ ሪፖርቶችን አጣጥላለች። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቤጂንግ ከሞስኮ ጋር ባላት ግንኙነት ምክንያት ከአሜሪካ ‘ማስፈራሪያዎችን’ እንደማትቀበል አስታውቋል።

ብሊንከን ግን ቤጂንግ ድጋፉን የምታደርግ ከሆነ ለአሜሪካ እና ቻይና ግንኙነት ከባድ ችግር ይሆናል ብለዋል።

የፕሬዝዳንት ቭላደሚር ፑቲን አጋር የሆኑት ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያሉት ነገር የለም። ፕሬዝዳንቱ ለሰላም ጥሪ ካቀረቡ ወዲህ በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ብሊንከን ጀርመን ሚዩኒክ በተካሄደው የደኅንነት ኮንፍረንስ ላይ ከቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ጋር ከተገናኙ በኋላ ቻይና ወታደራዊ ድጋፍ ለሩሲያ ልታደርግ መቻሏ ‘እጅጉን አሳስቦናል’ ብለዋል።

“እስከ ዛሬ የቻይና ኩባንያዎች ሩሲያ በዩክሬን ለምታደርገው ጦርነት ወታደራዊ ያልሆኑ ድጋፎችን ሲያደርጉ ነበር። አሳሳቢ የሆነው አሁን ባለን መረጃ መሠረት ወታደራዊ ድጋፎችን ስለማድረግ እያጤኑ ነው” ብለዋል።

ብሊንከን በቃለ ምልልሳቸው በቻይና ኩባንያዎች እና በቤጂንግ አስተዳደር መካከል ምንም ልዩነት የለም ብለዋል።

ከዚህ ቀደም አሜሪካ የዩክሬንን የሳተላይት ምስል ዋግነር ለተሰኘው የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ሰጥቷል ባለችው የቻይና ኩባንያ ላይ ማዕቀብ ጥላ ነበር።

ብሊንከን ቻይና ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ እያጤነች ነው ከማለታቸው በተጨማሪ ምዕራባውያን ሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ የተፈለገውን ውጤት እንዳያመጣ እያደረገች ነው ሲሉ ቻይናን ከሰዋል።

ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ምዕራባውያን አገራት የሞስኮን ምጣኔ ሃብት ለማዳከም በርካታ ማዕቀቦችን መጣላቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ቤጂንግ ከሞስኮ ጋር ያላት የንግድ ልውውጥ እያደገ በመሄዱ የምዕራባውያን ፍላጎት ተፈጻሚ እንዳይሆን እያደረገች ነው የሚል ወቀሳ ቻይና ላይ ይነሳል።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገራት ለዩክሬን ታንክን ጨምሮ ጦር መሳሪያዎችን እና ተተኳሾችን ሲልኩ ቆይተዋል።

ብሊንከን ይህን ይበሉ እንጂ በሚዩኒኩ የደኅንት ኮንፍረንስ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የቻይናው ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋንግ ዪ አገራቸው ጦርነቱን በተመለከተ ‘ዳር ቆማ አልተመለከተችም’ እንዲሁም ለጦርነቱ ተሳታፊዎች ድጋፍ በማድረግ ‘እሳቱ ላይ ቤንዚን አላርከፈከፈችም’ ሲሉ ተናግረዋል።

ዋንግ ጦርነቱን ለማቆም በተለይ ደግሞ በአውሮፓ የሚገኙ ወዳጆቻችን ምን አይነት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው በጥሞና ማጤን አለባቸው ብለዋል።

የቻይናው ከፍተኛ ዲፕሎማት “ድርድሩ እንዳይሳካ ወይም ጦርነቱ በፍጥነት እንዳያልቅ የሚፈልጉ አንዳንድ ኃይሎች አሉ” ብለዋል።