የእስራኤል ተወካይ ከአዲስ አበባው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ እንዲወጡ ተደረገ

የእስራኤሏ ዲፕሎማት ሻረን ባር-ሊ በአፍሪካ ኅብረት የደኅንነት አባላት ታጅበው ከአዳራሹ ሲወጡ

የፎቶው ባለመብት, @WALLANEWS

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤሏ ዲፕሎማት ሻረን ባር-ሊ በአፍሪካ ኅብረት የደኅንነት አባላት ታጅበው ከአዳራሹ ሲወጡ

ቅዳሜ ዕለት በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ አንዲት የእስራኤል ተወካይ ከስብሰባው አዳራሽ እንዲወጡ ተደረገ።

የአፍሪካ አገራት መሪዎች ከታደሙበት የስብሰባው አዳራሽ እንዲወጡ የተደረጉት ሻረን ባር-ሊ የተባሉ በእስራኤል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር መሆናቸው ተገልጿል።

የአፍሪካ ኅብረት ቃል አቀባይ ዲፕሎማቷ ከስብሰባው አዳራሽ እንዲወጡ የተደረገው እስራኤልን ለመወከል ከኅብረቱ ፈቃድ የተሰጣቸው ግለሰብ እሳቸው ባለመሆናቸው እንደሆን ቢገልጹም የእስራኤል መንግሥት ግን እርምጃውን ተቃውሞታል።

በበይነ መረብ ላይ በተዘዋወረ ቪዲዮ ላይ እንደታየው ዲፕሎማቷ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጽህፈት ቤት የመሪዎች ስብሰባ ከሚካሄድበት አዳራሽ በጥበቃ ሠራተኞች ታጅበው ሲወጡ ታይቷል።

በጉዳዩ ዙሪያ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይን ለክስተቱ ደቡብ አፍሪካን እና አልጄሪያን ተጠያቂ አድርገዋል።

እስራኤል በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ያላት ቦታ በአባል አገራት መካከል የውዝግብ ምንጭ ሆኖ የቆየ ነው።

ቪዲዮው የ36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ቅዳሜ ዕለት ተጀምሮ የመክፈቻው ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ በነበረበት ጊዜ የጥበቃ ሠራተኞች ወደ እስራኤል ልዑካን ሲቀርቡ ያሳያል።

በእስራኤል ከፍተኛ ዲፕሎማቷ ባር-ሊ እና በጥበቃ ሠራተኞቹ መካከል ንግግር የነበረ ሲሆን፣ ከዚያም በኋላ ዲፕሎማቷ እና የኅብረቱ የደኅንነት ሠራተኞች ከስብሰባው አዳራሽ አብረው ሲወጡ ታይቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ የሆኑት አምባሳደር ሻረን ባር-ሊ ስብሰባው ላይ በታዛቢነት ለመገኘት ፈቃድ እና የመግቢያ መታወቂያ ይዘው፣ ከአፍሪካ ኅብረት የስብሰባ አዳራሽ እንዲወጡ የተደረገበትን ይህንን ክስተት እስራኤል በቀላሉ አትመለከተውም” ሲሉ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊዮር ሃያት ለታይምስ ኦፍ ኢዝራኤል ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ለዚህ ክስተት አልጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካን የከሰሱ ሲሆን፣ አገራቱ “በጥላቻ ተገፍተው” የፈጽሙት ነው ብለዋል።

ነገር ግን አንድ የአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣን ባር-ሊ ከስብሰባው አዳራሽ “እንዲወጡ የተጠየቁት” በጉባዔው ላይ ለመታደም ስላልተጋበዙ መሆኑ ገልጸዋል።

ኅብረቱ በመሪዎቹ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የጋበዘው በአፍሪካ ኅብረት የእስራኤል አምባሳደር የሆኑትን አሌሊ አድማሱን ብቻ መሆኑን እና ግብዣውም ለሌላ ሰው የሚተላለፍ እንዳልሆነ የፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) ዘግቧል።

“ከስብሰባው እንዲወጡ የተደረጉት ግለሰብ ይህንን ግብዣ አላግባብ መጠቀማቸው የሚያሳዝን ነው” ስማቸው ያልተጠቀሱት የአፍሪካ ኅብረት ባለስልጣን ማለታቸውን ዜና ወኪሉ ገልጿል።

እስራኤል በአህጉራዊው ድርጅት ውስጥ የታዛቢነት ፈቃድ ከአንድ ዓመት በፊት ያገኘች ሲሆን፣ ፍልስጤማውያን ኅብረቱ ውሳኔውን መልሶ እንዲያጤነው መጠየቃቸውን ተከትሎ ግን ውሳኔው ጥያቄ ተነስቶበታል። ባለፈው ዓመትም ጉዳዩን የሚመረምር ኮሚቴ ተቋቁሟል።

በእስራኤል በኩል በአገራቸው ላይ የቀረበውን ክስ ውድቅ ያደረጉት የደቡብ አፍሪካው ቃል አቀባይ፣ አገራቸው ከዲፕሎማቷ ከስብሰባው እንዲወጡ መደረግ ጋር የሚያገናኛት ነገር እንደሌለ በመጥቀስ፣ በኅብረቱ ውስጥ የእስራኤል ውክልና ጉዳይ ውሳኔ ያላገኘ መሆኑን ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

በደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መሥሪያ ቤት ውስጥ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ኃላፊ የሆኑት ክሌይሰን ሞንዬላ “የአፍሪካ ኅብረት በእስራኤል የታዛቢነት ቦታ ላይ ውሳኔ አስኪሰጥ ድረስ፣ እንደ አገር በስብሰባው ላይ ታድሞ ለመታዘብ አይቻልም” ማለታቸው ተዘግቧል።

እስራኤል በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ያላትን ተሳትፎ በተመለከተ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአባል አገራት መካከል አከራካሪ ሆኗል።

ባለፉት ዓመታት እስራኤል ከአፍሪካ አገራት ጋር የቀረበ ግንኙነት ለመፍጠር ዓላማ አድርጋ እየሠራች ሲሆን፣ ያላትንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን እያሻሻለች ነው።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የቻዱ ፕሬዝዳንት የአገራቸውን ኤምባሲ ቴል አቪቭ ውስጥ ለመክፈት ወደ እስራኤል ተጉዘው ነበር።