ናይጄሪያዊው ፖለቲከኛ 500 ሺህ ዶላር ይዘው በቁጥጥር ስር ዋሉ

500 ሺህ ዶላር

የፎቶው ባለመብት, Rivers state Police Command

500 ሺህ ዶላር ይዘው የተገኙት ናይጄሪያዊው ፖለቲከኛ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ፖለቲከኛው በቁጥጥር ስር የዋሉት ሃገሪቱ ቅዳሜ ከምታደርገው ብሔራዊ ምርጫ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።

ፖሊስ ዶላሩን ያገኘው በፖለቲከኛው ቺንየሬ ኢግዌ መኪና ውስጥ ነው።

ፒዲፒ የተሰኘውን ተቃዋሚ ፓርቲ በመወከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት የሆኑት ኢግዌ ገንዘቡን የሚያከፋፍሏቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ይዘው መገኘታቸውንም ፖሊስ ገልጿል።

በቀደሙት የናይጄሪያ ምርጫዎች ፖለቲከኞች በገንዘባቸው ድምጽ በመግዛት ምርጫዎችን አጭበርበዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ናይጄሪያ በቅርቡ አዲስ የገንዘብ ኖቶችን ያስተዋወቀች ሲሆን ይህም በከፊል ፖለቲከኞች መራጮችን ለመደለል ገንዘብ ማሰባሰብ ፈታኝ እንዲሆንባቸው ለማድረግ እንደሆነም ተገልጿል።

ሆኖም አዲሶቹ ኖቶች በበቂ ሁኔታ በገበያ ላይ ባለመሰራጨታቸው በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል።

በርካቶችም ገንዘብ ከባንኮች ለማግኘት ረጅም ሰዓታት ተሰልፈው ቢጠብቁም ሳይሳካላቸው የቀረ ሲሆን አንዳንዶቹም በዚህ ምክንያት ባንኮች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

40 በመቶ የሚሆኑት ናይጄሪያውያን የባንክ አካውንት ስለሌላቸው ምግብ ለመግዛትም ሆነ ለሌሎች የዕለት ተዕለት ፍጆታዎች ጥሬ ገንዘብ መያዝ አለባቸው።

ፖለቲከኛው ኢግዌ በቁጥጥር ስር የዋሉበት የሪቨርስ ግዛት ፖሊስ “ሁሉም ተወዳዳሪዎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ህጎችን እንዲያከብሩ” በትዊተር ገጺ አሳስቧል።

ፖርት ሃርኮት የተሰኘችው ከተማ ተወካይ የሆኑት ፖለቲከኛ በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

የናይጄሪያ ወታደራዊ አገዛዝ በአውሮፓውያኑ 1999 ካከተመ በኋላ የዘንድሮው ምርጫ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚደረግበት ተተንብይዋል። በተለይም በሶስቱ ፕሬዚዳንታዊ እጩዎች በፒዲፒ ፓርቲ አቲኩ አቡበከር፣ የሌበር ፓርቲ ፒተር ኦቢ እና የገዥው ፓርቲ ኤፒሲ ቦላ ቲኒው መካከል ከፍተኛ ፉክክር የሚጠበቅ ሲሆን ሁሉም የአሸናፊነት ሰፍራ ተሰጥቷቸዋል።