ዩክሬን ከኔቶ አባል ሀገራት የተረከበችው ኤፍ-16 የጦር ጄት በሩሲያ ጥቃት ወደመ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩክሬን በቅርቡ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ካገኘቻቸው ኤፍ-16 የጦር ጄቶች መካከል አንዱ በሩሲያ ጥቃት መውደሙን የዩክሬን ወታደራዊ ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ሰኞ ዕለት ሩሲያ በተከታታይ ባደረጋቻቸው የሚሳዔል ጥቃቶች ምክንያት ጄቱ ሲወድም አብራሪው ኦሌክሲ ሜስ መገደሉን የዩክሬን ጦር አስታውቋል።
ሰኞ ዕለት በሩሲያ ሚሳኤል የተመታው ዘመናዊ የጦር ጄት ከአራት ሳምንታት በፊት ነበር ለዩክሬን በድጋፍ የተበረከተው።
የዩክሬን ጦር እንዳስታወቀው ጄቱ ከሩሲያ በተቃጣ ቀጥተኛ የሚሳዔል ጥቃት ምክንያት አይደለም ተመትቶ የወደቀው።
አክሎ ፓይለቱ ከመገደሉ በፊት ሶስት ክሩዝ ሚሳዔሎች እና አንድ ድሮን አውድሟል ብሏል የዩክሬን ጦር።
“ኦሌክሲ ከአደገኛ የሩሲያ የሚሳዔል ጥቃት ዩክሬናዊያንን ታድጓል” ይላል የዩክሬን አየር ኃይል በማኅበራዊ ሚድያ ገፁ ባሰራጨው መግለጫ።
“በሚያሳዝን ሁኔታ ራሱን ሰውቶ ነው ይህን ያደረገው።”
ምንም እንኳ አየር ኃይሉ ምን ዓይነት የጦር አውሮፕላን እንደወደመ ባይገልጥም የዩክሬን ወታደራዊ ምንጮች ፓይለቱ ኤፍ-16 ጄት እያበረረ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ማክሰኞ ዕለት አሜሪካ ሰራሹ ኤፍ-16 ጄት የሩሲያን ድሮን እና ሚሳዔል ለመመከት መሰማራታቸውን ማስታወቃች ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ በያዝነው ሳምንት ዩክሬን ረዥም ርቀት የሚጓዙ ሚሳዔሎችን ተጠቅማ ሩሲያ ድንበር ውስጥ ጥቃት እንድትሰነዝር አጋር ሀገራት እንዲፈቅዱላቸው ጠይቀዋል።
የኔዘርላንድስ ጦር ሠራዊት ኃላፊ ጄኔራል ኦኖ አይኽንሻይም ሀገራቸው 24 የጦር ጄቶች እና ሌሎች የጦር መሣሪያዎችን ለዩክሬን እንደምትሰጥ አስታውቀዋል።
እኒህን የጦር መሣሪያዎች ለመጠቀም ምንም ዓይነት ገደብ ያልተጣለ ሲሆን ነገር ግን የሰብዓዊነት ሕግን መጣስ አይቻልም ሲሉ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል። ይህ ማለት ዩክሬን ወደ ሩሲያ ድንበር ተሻግራ ጥቃት ማድረስ ትችላለች ማለት ነው።
በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 2023 የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የአውሮፓ አጋር ሀገራት ኤፍ-16 የጦር ጄቶችን ለዩክሬን መለገስ ይችላሉ ካሉ በኋላ የኔቶ አባል ሀገራት 65 ጄቶችን ለመላክ ቃል ገብተዋል።
የዩክሬን ኤፍ-16 ጄቶች ከሩሲያ የሚላኩ ቦታ ለይተው ጥቃት ከሚያደርሱ ልክ እንደአሜሪካው ጄዳም ዓይነት ቦምቦችን ለመከላከል ያገለግላሉ።
በሚቀጥለው ወር ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን “የድል ዕቅድ” ለማቅረብ ለተዘጋጁት ዜሌንስኪ የጄቱ መውደም መጥፎ ዜና ነው።
ዜሌንስኪ ሀገራቸው በቅርቡ የሠራችውን ባለስቲክ ሚሳዔል ሙከራ በተሳካ ሁኔታ ማድረጓን ቢገልፁም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።












