159 ድመቶችን ባልተገባ ሁኔታ የያዙ ፈረንሳዊያን ጥንዶች የቤት እንስሳትን እንዳያሳድጉ ታገዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፈረንሳዊያኑ ጥንዶች 159 ድመቶችን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በመያዛቸው የአንድ ዓመት የእስር ገደብ እና እና በሕይወት ዘመናቸው እንስሳትን እንዳያሳድጉ እገዳ ተጣለባቸው።
በአንድ ዓመቱ ወቅት የተጣሉባቸውን ገደቦች ተላልፈው ከተገኙም የእስር ቅጣት ተፈጻሚ ይሆንባቸዋል።
ኒስ በተባለችው የፈረንሳይ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ጥንዶቹ 159 ድመቶችንና ሰባት ውሻዎችን 80 ካሬ ሜትር በሆነ ጠባብ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ አቆይተዋል።
እነዚህ እንስሳት ባለፈው ዓመት ንጽህናቸው ባልተጠበቀበት ሁኔታ ውስጥ ተይዘው የተገኙ ሲሆን፣ በርካቶቹ በፈሳሽ እና በምግብ እጥረት የተዳረጉ እና በጥገኛ ተህዋስ የተጠቁ ነበሩ።
በጥንዶቹ ላይ ውሳኔውን ያሳለፉት ዳኛ ጥንዶቹ ለእነዚህ እንስሳቶች ተገቢውን እንክብካቤ አላደረጉም ብለዋል።
በዚህም ምክንያት የ68 ዓመቷ እና የ52 ዓመቱ ጥንዶች የቤት እንስሳትን እንዳያሳድጉ ቋሚ እግድ ተጥሎባቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ለእንስሳት መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና ሲቪል ተቋማት ከ128 ሺህ ዩሮ በላይ ገንዘብ እንዲከፍሉ ተበይኖባቸዋል።
ባለፈው ዓመት ፖሊስ አለመግባባትን ለመፍታት ጥንዶቹ በሚኖሩበት ቤት ውስጥ ገብቶ በነበረበት ወቅት በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ በርካታ እንስሳትን አግኝቶ ነበር።
የእንስሳቱ ጽዳጅም በየቦታው እንደነበር ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
የተወሰኑ ድመቶች እና ውሻዎችም በአያያዝ ጉድለት ምክንያት ባጋጠማቸው የጤና እክል ሞተዋል።
መርማሪዎች ቢያንስ የሁለት ድመቶች እና ሁለት ውሻዎች አስክሬን በመታጠቢያ ቤት ውስጥ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የቤቱ ባለቤት የሆኑት ግለሰቧ ለፍርድ ቤቱ ለእንስሳቶች የተለየ ፍቅር እንዳላቸውና የአዕምሮ ጭንቀት እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ግለሰቧ አገልግሎት በማይሰጥ ሕንጻ ውስጥ የተጣሉ 30 ድመቶችን ከመውሰዳቸው በፊት እንደ አውሮፓውያኑ 2018 የእንስሳቶቹ ወላጆች የሆኑትን ሦስት ድመት እና ሦስት ውሻዎችን ነበር የሚያሳድጉት። ከዚያም በጊዜ ሂደት እነዚህ እንስሳት ተራብተው በቁጥር ሊበረክቱ ችለዋል።
የተተው እንስሳትን ባያነሷቸው እርሳቸውም እንደተጣሉ እንደሚሰማቸውም ተናግረዋል።
የአዕምሮ ጤናቸውን አስመልክቶ የተደረገው ግምገማም ምቹ ሁኔታ ባይኖር እንኳን እንስሳትን የመጠበቅ ሥነ ልቦናዊ ፍላጎት የሚያሳድር ‘ኖህ ሲንድረም’ የተባለ ህመም እንዳለባቸው አሳይቷል።
ጥንዶቹ በ2014፣18 ካሬ ሜትር በሆነች ክፍል ውስጥ ከ13 ድመቶች እና ከአንድ ውሻ ጋር ሲኖሩ ምርመራ ተካሂዶባቸው ነበር።












