የአሜሪካው አየር መንገድ ‘በሰከሩ መንገደኞች’ ምክንያት የበረራ አቅጣጫውን ቀየረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ተነስቶ ወደ አሜሪካዋ ኒውጀርሲ እየበረረ የነበረው የአሜሪካው ዩናይትድ አየር መንገድ ‘በሰከሩ ሁለት መንገደኞች’ ምክንያት አቅጣጫውን ቀይሮ በሌላ ግዛት አረፈ።
አውሮፕላኑ ሁለት የሰከሩ የሚመስሉ መንገደኞች “ረብሻ በማስነሳታቸው” አቅጣጫውን ቀይሮ ሜይን በተባለችው ግዛት ማረፉንም አየር መንገዱ ገልጿል።
አርብ ጥዋት ከለንደኑ ሂትሮው አየር ማረፊያ የተነሳው የበረራ ቁጥር ዩኤ883 አውሮፕላን ኒዋርክ ማረፍ ቢኖርበትም፣ አቅጣጫውን ቀይሮ በባንጎር ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲያርፍ ተደርጓል።
አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላም ፖሊስ ሁለቱን ተሳፋሪዎች ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ እንዳደረጋቸውም ዩናይትድ አየር መንገድ ለቢቢሲ በላከው ኢሜይል ገልጿል።
እነዚህ መንገደኞች ለወደፊቱም ከየትኛውም የዩናይትድ አየር መንገድ በረራዎች ይታገዳሉ ተብሏል።
አውሮፕላኑ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ለሰባት ሰዓታት ጉዞ ካደረገ በኋላ የበረራ እንቅስቃሴዎችን የሚቆጣጠረው ፍላይትራዳር እንዳሳየው ወደ መዳረሻው ከመሄዱ በፊ አቅጣጫውን ቀይሮ ባንጎር አየር ማረፊያ ላይ አርፏል።
“ዩናይትድ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 883 ሁለት የሰከሩ የሚመስሉ መንገደኞች ረብሻ በማስነሳታቸው በባንጎር አውሮፕላን ማረፊያ አርፏል” በማለት አየር መንገዱ በመግለጫው አትቷል።
“የሕግ አስከባሪዎች ሁለቱን መንገደኞች ካስወረዷቸው በኋላ አውሮፕላኑ ወደ ቀደመ መዳረሻው ኒዋርክ ሊበርቲ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሄዷል። ጉዳዩን እስክናጣራ ድረስ ሁለቱ መንገደኞች ከማንኛውም የዩናይትድ በረራዎች ይታገዳሉ” ብሏል።
አስር የበረራ ሠራተኞችን እና 150 መንገደኞችን አሳፍሮ የነበረው አውሮፕላኑ ከለንደን ጥዋት 1፡52 ተነስቶም በሜይን አራት ስዓት ላይ በሰላም ማረፉንም የአሜሪካ የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር ገልጿል።
አስተዳደሩ በቦይንግ 767 አውሮፕላኑ ላይ የተከሰተውን ነገርም “የተሳፋሪዎች ረብሻ” ሲል ገልጾታል።
የባንጎር ፖሊስ አባላት ሁለቱን ተሳፋሪዎች ከአውሮፕላኑ በማስወረድ የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ እንዲሁም ምርመራውን እየካሄዱ ያሉትን ኤፍቢአይን መርዳታቸውን አስታውቋል።












