በአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቿ ስህተት የኢትዮጵያ እና የኳታር አውሮፕላኖች ሊጋጩ ነበር መባሉን ሶማሊያ አስተባበለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሶማሊያ የአየር ክልል ላይ ሲጓዙ የነበሩት የኢትዮጵያ እና የኳታር አየር መንገድ አውሮፕላኖች የሞቃዲሾ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በሰጧቸው የተሳሳተ መረጃ ሊጋጩ ተቃርበው ነበር መባሉን ስህተት ነው ሲል የሶማሊያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን አስተባበለ።
ቅዳሜ የካቲት 16/ 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 6፡30 ከዶሃ ወደ ኡጋንዳ እየበረረ የነበረው (ኳታር 6 ዩ) አውሮፕላን ከፍታውን እንዲጨምር በሞቃዲሾ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በስህተት ተነግሮት ከኢትዮጵያ አውሮፕላን ጋር ለመጋጨት በአደገኛ ርቀት ላይ ነበር ሲል የሶማሊላንድ አቪየሽን ባለሥልጣን አሳውቋል።
የሶማሊያ አቪዬሽን ባለሥልጣን በበኩሉ በሁለቱ አውሮፕላን መካከል የነበረው ርቀት ስጋት ላይ የሚጥል አይደለም ሲል አስተባብሏል።
“በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል የነበረው ርቀት አደጋ አልነበረውም። በዓለም ላይ በተለመደው የከፍታ ርቀት ላይ ነበሩ” ሲሉም የሶማሊያ አቪዬሽን ባለሥልጣን አሕመድ ማኬሊን ሃሰን ለቢቢሲ ሶማሊ ተናግረዋል።
ንብረትነቱ የኳታር አየር መንገድ የሆነው (ኳታር 6ዩ) አውሮፕላን ሲበርበት ከነበረው 38 ሺህ ጫማ ወደ 40 ሺህ ጫማ ከፍታ እንዲወጣ በሞቃዲሾ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ተነግሮታል ሲል የሶማሊላንድ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ገልጿል።
በተመሳሳይም ሰዓት ከአዲስ አበባ ወደ ዱባይ በ39 ሺህ የጫማ ከፍታ ሲበር ከነበረው የኢትዮጵያው አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 602ም ጋር መፋጠጣቸውም ተገልጿል።
በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል የነበረው ርቀት አደገኛ ነበር ያለው የሶማሊላንድ ሲቪል አቪየሽን ከመጋጨት ያተረፋቸውም በሁለቱ አውሮፕላኖች ላይ የተገጠመው የግጭት መከላከያ ሥርዓት መሆኑንም አመልክቷል።
“እንደ ዕድል ሆኖ በሁለቱ አውሮፕላን ላይ ያለው ሥርዓት (ትራፊክ አቮይዳንስ ኮሊዥን ሲስተም) አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በዚያው ከፍታ ላይ ሌላ አውሮፕላን መኖሩን አመልክቷል” ሲልም ባለሥልጣኑ ያወጣው መግለጫ ገልጿል።
ይህንንም አስመልክቶ የሶማሊያ አቪየሽን ባለሥልጣን ለአውሮፕላኖቹ ከግጭት መከላከያ ሥርዓቱ የተሰጣቸው መልዕክት የአደጋ ማስጠንቀቂያ ሳይሆን ምክር ነው ብለዋል።
አሕመድ ማኬሊን በበኩላቸው የኳታር የአየር መንገድ ጋር ግንኙነት በመፍጠር በ40 ሺህ የጫማ ከፍታ እንዲበር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በነበረው ከፍታ ሲበር እንደነበረ ገልጸው በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል የነበረው ርቀት ስጋት የለውም ብለዋል።
የኳታር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ከሶማሊያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የተሳሳተ መመሪያ እንደተሰጣቸው፣ እንዲሁም ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ሲነጋገሩ ተደምጠዋል ብሏል የሶማሊላንድ ሲቪል አቮየሽን ባለሥልጣን።
ከዚህ ክስተት በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ጂቡቲ ላይ አርፎ መንገደኞችን በማሳፈር ባቀደው መንገድም ጉዘውን ቀጥሏል ብለዋል።
ቢቢሲ ከሶማሊያ እና ከሶማሊላንድ ባለሥልጣናት በኩል ክስተቱን በተመለከተ የተሰጡትን ማብራሪያዎች በተናጥል ማረጋገጥ አልቻለም።
እንዲሁም የአውሮፕላኖቹ ባለቤቶች የሆኑት የኢትዮጵያም ሆነ የኳታር አየር መንገዶች ስለክስተቱ አስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም።












