አውሮፕላኑ ከኳታር አውሮፕላን ጋር ሊጋጭ ተቃርቦ ነበር ስለመባሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምላሽ ሰጠ

የፎቶው ባለመብት, ETHIOPIAN AIRLINES
በሶማሊያ አየር ክልል ውስጥ ሲበሩ የነበሩት የኢትዮጵያ እና የኳታር አየር መንገድ አውሮፕላኖች በሞቃዲሾ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ስህተት ምክንያት ሊጋጩ ተቃርበው ነበር በተባለው ክስተት ዙሪያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምላሽ ሰጠ።
ቅዳሜ የካቲት 16/2016 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ ዱባይ ሲጓዝ የነበረው የበረራ ቁጥር 602 አውሮፕላኑ በነበረበት ከፍታ ላይ የኳታር አውሮፕላን እየቀረበው እንደነበር መረጃ እንደተቀበለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቢቢሲ ሶማሊ በሰጠው ምላሽ ገልጿል።
ክስተቱን በተመለከተ ለተጨማሪ ምርመራ እንዲሁም የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለሶማሊያ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት ሪፖርት መደረጉንም አየር መንገዱ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሶማሊላንድ አቪዬሽን ባለሥልጣን ሁለቱ አውሮፕላኖች ለመጋጨት በአደገኛ ርቀት ነበር ላይ ስለመባሉ ያለው ነገር የለም።
የሶማሊላንድ አቪዬሽን የኳታር አውሮፕላን (ኳታር 6ዩ) ከሞቃዲሾ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በተሰጠው የተሳሳተ መረጃ ከፍታውን በመጨመሩ ከኢትዮጵያው አውሮፕላን ጋር አደገኛ በሆነ ርቀት ላይ እንደነበሩ እና ሊጋጩ ተቃርበው ነበር ሲልም አስታውቆ ነበር።
የሶማሊያ አቪዬሽን ባለሥልጣን በበኩሉ በሁለቱ አውሮፕላን መካከል የነበረው ርቀት ለአደጋ ስጋት ላይ የሚጥል አይደለም ሲል አስተባብሏል።
“በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል የነበረው ርቀት አደጋ አልነበረውም። በዓለም ላይ በተለመደው የከፍታ ርቀት ላይ ነበሩ” ሲሉም የሶማሊያ አቪዬሽን ባለሥልጣን አሕመድ ማኬሊን ሃሰን ለቢቢሲ ሶማሊ ተናግረው ነበር።
በሶማሊያ የአየር ክልል ላይ ከአዲስ አበባ ወደ ዱባይ በ39 ሺህ የጫማ ከፍታ እየበረረ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በረራ ቁጥር 602 በነበረበት ከፍታ ሌላ አውሮፕላን እየተጠጋው እንደሆነ የትራፊክ ምክር (የትራፊክ አድቫይዘሪ) እንደደረሰው አስታውቋል።
ንብረትነቱ የኳታር የሆነው (ኳታር 6ዩ) አውሮፕላን ከቀኑ 6፡32 አካባቢ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን እየበረረ በነበረበት ከፍታ ላይ እየተቃረበ ነው የሚልም የትራፊክ አድቫይዘሪ እንደደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቢቢሲ ሶማሊ በኢሜይል በሰጠው ምላሽ ገልጿል።
ከዶሃ ወደ ኡጋንዳ እየበረረ የነበረው የኳታር አውሮፕላን መጀመሪያ ላይ በ38 ሺህ ጫማ ሲበር የነበረ ቢሆንም፣ በዳታ ሊንክ በተሰጠው መረጃ ወደ 40 ሺህ ጫማ ከፍ እንዲል ፍቃድ እንዳገኘ ሪፖርት ማድረጉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጠቅሷል።
ይህ ክስተት በተፈጠረበት ወቅት በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል የነበረው ርቀት 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ነበር ብሏል።
“ሁለቱም አውሮፕላኖች እጅግ ዘመናዊ የሆነ የግጭት መከላከያ ሥርዓት (ትራፊክ አቮይዳንስ ኮሊዥን ሲስተም) የተገጠመላቸው ሲሆን ይህ ከስተት በተፈጠረበት ወቅትም በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል የነበረው ርቀት 13 ናውቲካል ማይልስ (23 ኪሎሜትር) ነበር” ብሏል።
በተጨማሪም ሁለቱም አውሮፕላኖች በከፍታ ብቻ ሳይሆን በተጨማሪ በአግድመት ያላቸውን ርቀት የሚያስጠብቀውን ስትራቴጂካል ላተራል ኦፍሴት ፕሮሲጀር ስሎፕ በመተግበር ላይ እንደነበሩም ገልጿል።
ሁለቱም አውሮፕላኖች ላይ የተገጠመው የግጭት መከላከያ ሥርዓት ለሁለቱም አውሮፕላን አብራሪዎች መደረግ ስላለባቸው ጉዳዮችን የትራፊክ ምክር መረጃዎችን በተመለከተ የሚሰጠው ለጥንቃቄ ያህል እንደሆነ ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምላሽ ያስረዳው።
አብራሪዎቹ ይዘውት የነበረውን የበረራ መስመር ከፍታን ጠብቀው ጉዟቸውን ቀጥለው በሰላም በመዳረሻቸው ማረፋቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገልጿል።
ሲበርበት ከነበረውን ከፍታ እንዲጨምር ተደርጓል የተባለው የኳታር አየር መንገድ በበኩሉ ይህ ክስተትን በተመለከተ ለሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ሪፖርት እንደተደረገም ለቢቢሲ ሶማሊ ገልጿል።
“በወቅቱም ከኳታር አየር መንገድ አሰራር ጋር በተጣጣመ መልኩ በአውሮፕላኑ ሠራተኞች ምላሽ ተሰጥቷል። በተፈጠረው ሁኔታ የአውሮፕላኑን ሠራተኞችንም ሆነ ተሳፋሪዎችን ደኅንነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነገር አልገጠመም” ሲልም ለቢቢሲ ሶማሊ በላከው የኢሜይል መልዕክት ገልጿል።
በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል የነበረው ርቀት አደገኛ ነበር ያለው የሶማሊላንድ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከመጋጨት ያተረፋቸውም በሁለቱ አውሮፕላኖች ላይ የተገጠመው የግጭት መከላከያ ሥርዓት መሆኑንም ጠቅሷል።
“እንደ ዕድል ሆኖ በሁለቱ አውሮፕላኖች ላይ ያለው ሥርዓት (ትራፊክ አቮይዳንስ ኮሊዥን ሲስተም) አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በዚያው ከፍታ ላይ ሌላ አውሮፕላን መኖሩን አመልክቷል” ሲልም ባለሥልጣኑ ያወጣው መግለጫ አሳውቋል።
ይህንንም አስመልክቶ የሶማሊያ አቪዬሽን ባለሥልጣን ለአውሮፕላኖቹ ከግጭት መከላከያ ሥርዓቱ የተሰጣቸው መልዕክት የአደጋ ማስጠንቀቂያ ሳይሆን ምክር ነው ብለዋል።
አሕመድ ማኬሊን በበኩላቸው የኳታር የአየር መንገድ ጋር ግንኙነት በመፍጠር በ40 ሺህ የጫማ ከፍታ እንዲበር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በነበረው ከፍታ ሲበር እንደነበረ ገልጸው በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል የነበረው ርቀት ስጋት የለውም ብለዋል።
የኳታር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ከሶማሊያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የተሳሳተ መመሪያ እንደተሰጣቸው፣ እንዲሁም ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ሲነጋገሩ ተደምጠዋል ብሏል የሶማሊላንድ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን።
ከዚህ ክስተት በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ጂቡቲ ላይ አርፎ መንገደኞችን በማሳፈር በጉዞው ዕቅድ መሠረት በራራውን ቀጥሏል ብለዋል።












