የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሶማሊያ የአየር ክልል በኩል መብረር ማቆሙን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጹ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, ethiopian/fb

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እስያ አገራት ለሚያደርጋቸው በረራዎች ይጠቀምበት በነበረው የሶማሊያ የአየር ክልል በኩል መብረር ማቆሙን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለቢቢሲ ገለጹ።

አየር መንገዱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከሶማሊያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች “አስተማማኝ የአየር ትራፊክ አገልግሎት” ባለማግኘቱ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው ለቢቢሲ አማርኛ አርብ ከሰዓት በኋላ የተናገሩ ቢሆንም፣ ድርጅቱ ምሽት ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባሰራጨው መግለጫ የአቶ መስፍንን አስተያየት አስተባብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ባወጣው መግለጫ “ሪፖርቱ ትክክል ያልሆነ እና የተዛባ ነው” ያለ ሲሆን፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው “የሶማሊያ አየር ክልል ደኅንነቱ አስተማማኝ አይደለም” አለማለታቸውን በመግለጽ፣ ቢቢሲ ማስተካከያ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ቢቢሲ ዘገባውን ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ጋር የተደረገን ቃለ ምልልስ መሠረት አድርጎ የሠራ ሲሆን፣ እንደተባለው አቶ መስፍን ከተናገሩት ውጪ የተካተተ ወይም የተዛባ አስተያየት እንደሌለ ያረጋግጣል።

ለዚህም ከዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ እዚህ አያይዟል።

Skip ከአቶ መስፍን ጣሰው ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ከ6ኛ ደቂቃ ጀምረው ያድምጡ and continue readingከአቶ መስፍን ጣሰው ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ከ6ኛ ደቂቃ ጀምረው ያድምጡ

End of ከአቶ መስፍን ጣሰው ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ከ6ኛ ደቂቃ ጀምረው ያድምጡ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እስያ ለሚደርጋቸው በረራዎች “ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ” ይጠቀምበት በነበረው የሶማሊያ አየር ክልል መብረር ያቆመው፤ የአየር መንገዱ አውሮፕላን ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የካቲት 16/2016 ዓ.ም. በአገሪቱ የአየር ክልል ውስጥ ካጋጠመው ክስተት ጋር በተያያዘ መሆኑን አቶ መስፍን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን፤ “በዓለም አቀፍ አሠራር መሠረት እንደዚህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥም ለሚመለከታቸው የሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣናት ሪፖርት እናደርጋለን። [የቅዳሜውን ክስተት በተመለከተም] ለሶማሊያ እና ለኢትዮጵያ የሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣናት ሪፖርት ተደርጓል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይሁንና እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩን አክለዋል።

የቅዳሜ ዕለቱ ክስተት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሶማሊያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚሰጠውን አገልግሎት “አስተማማኝ ሆኖ እንዳያገኘው” ማድረጉን አቶ መስፍን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ይህ ክስተት ካጋጠመበት ማግስት እሁድ የካቲት 17/2016 ዓ.ም. አንስቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሶማሊያን አየር ክልል መጠቀም ለማቆም መወሰኑን አስታውቀዋል።

ቢቢሲ ፍላይትራዳር24 እና ፍላትአዌር የተባሉ ዓለም አቀፍ የበረራ መስመሮች መከታተያ ድረ ገጾች ላይ ባደረገው ማጣራት ባለፈው ሳምንት በሶማሊያ የአየር ክልል ውስጥ በኢትዮጵያ እና በኳታር አውሮፕላኖች መካከል ያጋጠመውን ክስተት ተከትሎ የበረራ መስመር ለውጥ እንዳለ ለመረዳት ችሏል።

በዚህም አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት የሚያደርጋቸው በረራዎች በሶማሊያ የአየር ክልል በኩል የነበሩ ሲሆን፣ ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ግን ጉዞዎቹ በጂቡቲ በኩል እንደሆኑ ድረገጾቹ ያመለክታሉ።

የበረራ መስመር ለውጥ ያደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን የኳታር አየር መንገድም ቀደም ሲል ከኡጋንዳ ኢንተቤ ወደ ዶሃ፣ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በኩል ጉዞ ሲያደርግ የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት ቀናት ግን በኢትዮጵያ እና በኤርትራ በኩል እየበረረ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ መስፍን፤ ከክስተቱ በኋላ ካለው ቀን አንስቶ “አማራጭ ለመጠቀም ወስነናል። ለዚህም ዋናው ምክንያት [የቅዳሜ ዕለቱ ክስተት] ነው። እዚያ በነበረው ሁኔታ፤ የአየር ክልሉ አስተማማኝ የአየር ትራፊክ አገልግሎት ስላላገኘንበት ለደኅንነት ስንል አማራጭ መንገዶች እየተጠቀምን ነው” ሲሉ የአየር መንገዱን ውሳኔ አብራርተዋል።

አየር መንገዱ ወደ እስያ ለሚያደርጋቸው በረራዎች የሚጠቀመው የሶማሊያን የአየር ክልል እንደነበር ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በአሁኑ ሰዓት እነዚህ በራረዎች የሚደረጉት በጂቡቲ አየር ክልል በኩል መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጂቡቲን የአየር ክልል እየተጠቀመ ያለው “ተጨማሪ ወጪ በማያመጣ መልኩ” እንደሆነም አክለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሌለሎች አገራት ለሚደረጉ በራረዎች የሶማሊያን አየር ክልል መጠቀም ቢያቆምም ወደ ሞቃዲሾ እና ወደ የሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳ ከተማዎች የሚያደርጋቸውን በራረዎች “ያለ ችግር” መቀጠሉን አብራርተዋል።

ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ ወደ ዱባይ ሲጓዝ የነበረው የአየር መንገዱ የበረራ ቁጥር 602 አውሮፕላን፤ የኳታር ኤር ዌይስ አውሮፕላን እየቀረበው እንደሆነ መረጃ መቀበሉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

በሶማሊያ የአየር ክልል ውስጥ እየበረረ የነበረው የኳታሩ አውሮፕላን የነበረበትን ከፍታ በመጨመር ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የቀረበው ከሞቃዲሾ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በተሰጠው ፈቃድ መሆኑን አየር መንገዱ ጠቅሶ ነበር።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢሜል ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል የነበረው ርቀት 23 ኪሎ ሜትር እንደሆነ ገልጿል።

ይህንን ክስተት አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው የሶማሊላንድ አቪየሽን እና ኤርፖርቶች ባለሥልጣን የኢትዮጵያ እና የኳታር አውሮፕላኖች “አደገኛ በሆነ ርቀት” ላይ እንደነበሩ እና “ሊጋጩ ተቃርበው” እንደነበር መግለጹ ይታወሳል። ይህም የሆነው በሞቃዲሾ የሚገኙት የሶማሊያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በሰጡት “የተሳሳተ መረጃ” እንደሆነ በመግለጽም ከስሶ ነበር።

ይሁንና የሶማሊያ አቪዬሽን ባለሥልጣን በበኩሉ በሁለቱ አውሮፕላን መካከል የነበረው ርቀት አደጋን የሚያስከትል ስጋት ላይ አልነበረም ሲል ጉዳዩን አስተባብሏል።