የቀድሞው የብራዚል ፕሬዚዳንት የተፈረደባቸውን የ27 ዓመት የእስር ቅጣት እንዲጀምሩ ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የብራዚል ከፍተኛው ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዣየር ቦልሶናሮ ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ በማሴር ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የተጣለባቸውን የ27 ዓመት ከሦስት ወር እስር እንዲጀምሩ ወሰነ።
ዳኛው አሌክሳንደር ዴ ሞራስ ማክሰኞ ዕለት ጉዳዩ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መድረሱን እና ምንም ተጨማሪ ይግባኝ ሊቀርብ እንደማይችል ብይን ሰጥተዋል።
የ70 ዓመቱ ቦልሶናሮ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጣር በ2022 በተካሄደው ምርጫ በተቀናቃኛቸው ሉላ ዳ ሲልቫ ከተሸነፉ በኋላ በሥልጣን ላይ ለማቆየት ሲሉ የመፈንቅለ መንግሥት ሴራን በመምራት ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።
የእስር ጊዜያቸውን በዋና ከተማዋ ብራዚሊያ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ እስር ቤት እንደሚፈጽሙ ተገልጿል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከቅዳሜ ጀምሮ ሊያመልጡ ይችላሉ በሚል ስጋት ከነበሩበት የቁም እስር ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ተደርጓል።
እሁድ ዕለት የዋለው ችሎት ቦልሶናሮ "እያደረጉ ያለውን እስኪነገነዘቡ ድረስ" ቁርጭምጭሚታቸው ላይ የታሰረላቸውን መቆጣጠሪያ ለመክፈት መሞከራቸውን አምነዋል።
ለማምለጥ ምንም ሀሳብ እንዳልነበራቸው በመግለጽ የተከራከሩት ቦልሶናሮ በመቆጣጠሪያ ላይ ለደረሰው ውድመት በመድኃኒት ምክንያት የተፈጠረ "አደጋ ይደርስብኛል የሚል ስጋት" ነው ሲሉ አስተባብለዋል።
ዳኛ ሞሬስ ማክሰኞ ዕለት ቦልሶናሮ ሙሉ የሕክምና እንክብካቤ እንዲያገኙ አዝዘዋል።
ከዚህ በፊት የቦልሶናሮ የሕክምና ቡድን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በሚሄድ የጤና መታወክ መጎዳታቸውን ተናግሮ ነበር።
ቦልሶናሮ እአአ በ2022 ምርጫ ሲሸነፉ ከሥልጣን ላለመውረድ ሲሉ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሞክረዋል በሚል ነበር የተከሰሱት።
ቦልሶናሮን ያሸነፉት ግራ ዘመሙ ሉዊዝ ኢንሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ናቸው።
የቦልሶናሮ የመፈንቅለ መንግሥት ውጥን ሉላን እንዲሁም ምክትላቸው ጄራልዶ አልክሚንን መግደልን ያካተተ እንደነበር የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ተናግረዋል።
ዕቅዱ በብራዚል ወታደሮች እና በአየር ኃይሉ ድጋፍ ስላላገኘ ሳይሳካ ቀርቷል። የሉላን በዓለ ሲመት ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የቦልሶናሮ ደጋፊዎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጥሰው ገብተዋል። ነውጥ አስነስተዋል በሚል 1,500 የሚሆኑት ታስረዋል።
ዳኞቹ ሁከት ፈጣሪዎቹ በቦልሶናሮ ቅስቀሳ እንደተነሳሱ ማረጋገጣቸውን እና የአገሪቱ ጦር ጣልቃ ገብቶ ወደ ሥልጣን አንዲመልሳቸው አቅደው እንደነበር ተናግረዋል።
ቦልሶናሮ እስከ 2060 ድረስ፣ የእስር ጊዜያቸውን ከጨረሱ ከስምንት ዓመት በኋላ፣ ለሕዝብ ሥልጣን እንዳይወዳደሩ ታግደዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ውሳኔውን በ2026 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዳይወዳደሩ ለማድረግ የተነደፈ "ያልተፈጠረ ነገርን መፈለግ" ነው ብለው ኮንነውታል።
ዳኛ ሞሬስ ማክሰኞ ዕለት የቦልሶናሮ አባሪ ተባባሪ በመሆን ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ሌሎች ግለሰቦችም ቅጣታቸውን መፈፀም እንዲጀምሩ አዝዘዋል።
በዚህ ውሳኔ ላይ የተቋማት ደህንነት ሚኒስትር የነበሩት ጄኔራል አውጉስቶ ሄሌኖ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል ፓውሎ ሰርጆ ኖጌይራ ዴ ኦሊቬራ ይገኙበታል።















