የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ መፈንቅለ መንግሥት አሲረዋል በሚል 27 ዓመት ተፈረደባቸው

የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ

የፎቶው ባለመብት, EVARISTO SA/AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ

የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ለመያዝ ሞክረዋል በሚል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የ27 ዓመት ከ3 ወራት እስር ተፈርደባቸው።

አምስት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ቅጣቱን ያስተላለፉት የቀድሞው መሪ ላይ ጥፋተኝነት ውሳኔ ከሰጡ ከሰዓታት በኋላ ነው።

እአአ በ2022 በተካሄደው ምርጫ በግራ ክንፍ ተቀናቃኛቸው ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ከተሸነፉ በኋላ በሥልጣን ላይ ለመቆየት አቅደው ነበር በሚል ነው የተፈረደባቸው።

አራቱ ዳኞች ጥፋተኛ ሆነው ሲያገኙዋቸው አንዱ በነፃ እንዲሰናበቱ ድምጽ ሰጥተዋል።

የቦልሶናሮ ጠበቆች ቅጣቱን "በጣም ከመጠን በላይ የተጋነነ" ሲሉ ገልጸው፤ "ይግባኝ" እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እስከ 2033 ድረስ ከየትኛውም ፖለቲካዊ ምርጫ ፉክክር ውጭ እንዲሆኑ አግዷል።

ከአገር ሊወጡ ይችላሉ በሚል በቁም እስር እንዲቆዩ የተደረጉት ቦልሶናሮ ውሳኔው ሲሰጥ ፍርድ ቤት በአካል አልተገኙም።

እአአ በ2026 በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዳይወዳደሩ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ቀደም ሲል ገልጸው ነበር። በሌላ ክስም ከተፎካካሪነት የታገዱ ቢሆኑም ጉዳዩን "መሠረተ ቢስ ጥቃት" ብለውታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሃሳቡን የደገፉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለቦልሶናሮ ክስ የበቀል እርምጃ መሆኑን በመግለጽ በብራዚል ምርቶች ላይ 50 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል።

የጥፋተኝነት ውሳኔውን አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት ትራምፕ "በጣም አስገራሚ ሆኖ አግኝቸዋለሁ" በማለት ከራሳቸው ጋር በማነጻጸር "እኔ ላይ ሊያደርጉት ከሞከሩት ጋር ይመሳሰላል። ግን ምንም አላሳኩም" ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ እንዲታሰሩ ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ መስጠቱን እና "ለዚህ መሰረተ ቢስ ጥቃት ምላሽ እንደሚሰጡ" ዝተዋል።

የብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስ ላይ በሰጠው ፈጣን ምላሽ "የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በብራዚል ላይ በሰነዘሩት የጥቃት መግለጫ የብራዚልን ሥልጣንን፣ እውነታውን እና በመዝገብ ላይ ያሉትን አሳማኝ ማስረጃዎች ችላ ያለ ቢሆንም ዲሞክራሲያችንን አያሸማቅቀውም" ብሏል።

የ70 ዓመቱ ቦልሶናሮ ቀሪ ሕይወታቸውን በእስር ቤት የማሳለፍ ግዴታ ተጋርጦባቸዋል።

ጠበቆቻቸው እስር ቤት ከመውረድ ይልቅ በቁም እስር እንዲቆዩ እና የቅጣት ማቅለያ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የጥፋተኝነት ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቁ ቢናገሩም የሕግ ባለሙያዎች ግን ይህ ሊሆን የሚችለው ከአምስቱ ዳኞች ሁለቱ በነፃ እንዲሰናበቱ ድምጽ ሰጥተው ቢሆን ብቻ እንደሆነ በመግለጽ ከባድ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ቦልሶናሮ በ2022 ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሙከራ አድርገዋል በሚል በአምስት ክሶች ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

በሥልጣን ላይ ለመቆየት ማሴር የጀመሩት ከረዥም ጊዜ በፊት እንደሆነ የገለጸው አቃቤ ሕግ ወታደራዊ አዛዦች ላይ መፈንቅለ መንግሥት በማሴር እና በምርጫ ሥርዓቱ ላይ መሠረተ ቢስ ጥርጣሬ እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።

በተጨማሪም ሉላን እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተወዳደሩትን ግለሰብ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛን ለመግደል ቦልሶናሮ ዕቅድ እንደነበራቸው እንደሚያውቅ ገልጿል።

ዳኞቹ ሴራውን መምራቱን ያረጋገጡ ሲሆን በሰባቱ ከፍተኛ የጦር መኮንን ተባባሪዎቻቸውንም ጥፋተኛ ብለዋል።

ከእነዚህ መካከል ሁለቱ የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር፣ አንድ የቀድሞ የስለላ ኃላፊ እና አንድ የቀድሞ የደህንነት ሚኒስትር ይገኙበታል።

ሴራው እንዲከወን ከጦሩ በቂ ድጋፍ ማግኘት ባይችልም፣ እአአ ጥር 8 ቀን 2023 የቦልሶናሮ ደጋፊዎች የመንግስት መስሪያ ቤቶችን መውረራቸውን ዳኞቹ ገልጸዋል።

ጉዳዩ በፍጥነት በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ከአንድ ሺህ 500 በላይ ሰዎችም ታስረዋል።

ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት የሕግ ባለሙያው አሌክሳንደር ዴ ሞራስ ብራዚል ወደ አምባገነንነት ልትሸጋገር ተቃርባ ነበር ብለዋል።

"ብራዚል ወደ 20 ዓመታት አምባገነንነቷ ልትመለስ የተቃረበች መሆኗን ቀስ በቀስ እየረሳን ነው። ምክንያቱም የፖለቲካ ቡድን ያቀፈ ወንጀለኛ ድርጅት በምርጫ እንዴት መሸነፍ እንዳለበት አያውቅም" ሲሉ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ተናግረዋል።

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ከ"ቫይረስ" ጋር በማነጻጸር ከተተወ የተለከፈውን ማኅበረሰብ ሊገድል ይችላል ብለዋል።

ከአምስት የዳኞች አባላት ውስጥ ክሱን ውድቅ ያደረጉት ዳኛው ሉዊዝ ፉክስ ረቡዕ ዕለት ለ11 ሰዓታት ባደረጉት ንግግር በዢየር ቦልሶናሮ ላይ የቀረበው ክስ መሠረተ ቢስ ነው በማለት ተከራክረዋል። በዚህም ክሱ እንዲቋረጥ ድምጽ ሰጥተዋል ።

ከአባላቱ ውስጥ ብቸኛ ሴት ዳኛ የሆኑት ካርመን ሉቺያ የብራዚል ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበር በመግለጽ "ለአምባገነንነት ምንም ዓይነት መከላከያ አይቀርብም" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።