የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ልጅ ትራምፕ በሀገሩ ላይ የጣሉትን ታሪፍ አደነቀ

የቀድሞው የብራዚል ፕሬዚዳንት ዣየር ቦልሶናሮ ልጅ፤ በሀገሩ ላይ ከፍተኛ ቀረጥ የጣሉትን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማድነቅ፤ ብራዚል ላይ ተጨማሪ እርምጃዎች ሊወሰድ እንደሚችሉ አስጠነቀቀ።
ብራዚል ውስጥ ተመራጭ የኮንግረስ አባል የሆነው ኤድዋርዶ ቦልሶናሮ፤ በዋሽንግተን ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ አድርጓል።
ኤድዋርድ በዋሽንግተን በመገኘት የትራምፕ አስተዳደር አባቱን በመፈንቅለ መንግሥት ወንጀል ለፍርድ ያቀረቡ ባለሥልጣናትን እንዲቀጣ ለወራት የጉትጎታ ስራ ሲያከናውን ቆይቷል።
የኮንግረስ አባሉ በግለሰቦች ላይ የሚጣሉ ተጨማሪ ማዕቀቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተናግሯል።
"ማዕቀቦችን ተግባራዊ ማድረግ እና በሌሎች ሰዎች ላይ የሚጣሉ የማግኒቲስኪ ማዕቀቦችን ማራዘም የሚያስችል ትልቅ እድል አለ። ለምሳሌ ብራዚልን እያጋጠማት ካለው ተቋማዊ ቀውስ ለማውጣት ከሚያደርጉት ሌሎች ግፊት ማድረጊያ ዘዴዎች መካከል አንዱ የሆነው ቪዛ ማስወገድን የተመለከተ እርምጃ በሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ዴስክ ላይ ይገኛል" ብሏል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሀሙስ በዋይት ሀውስ ባደረጉት ንግግር ብራዚልን መጥፎ የንግድ አጋር እንደሆነች በመጥቀስ ከስሰዋል። አሜሪካ ከብራዚል ጋር በምታደርገው የንግድ ልውውጥ ጉድለት እንዳለ በማንሳት ስህተት ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት አሜሪካ ከብራዚል ጋር ባደረገችው ንግድ 7.4 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ትርፍ ተመዝግቧል።
"በእውነቱ ቦልሶናሮ ላይ ለማድረግ እየሞከሩ ያሉት የፖለቲካዊ ግድያ ነው። ይህ በጣም መጥፎ ነው ብዬ አስባለሁ" ሲሉም ዣይር ቦልሶናሮን ተከላክለዋል።
የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት የተከሰሱት በ2022 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፏቸውን ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ስልጣኑን እንዳይይዙ ለማድረግ መፈንቅለ መንግሥት አሲረዋል በሚል ነው።
ቦልሶናሮ መንግሥትን ለመገልበጥ ሙከራ አድርገዋል የሚለውን ውንጀላ ቢያጣጥሉም፤ በምርጫው የደረሰውን ሽንፈት ለመቀልበስ በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ መሳተፋቸውን አምነዋል።
ፍርድ ቤቱ በቀጣዮቹ ሳምንታት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ቦልሶናሮ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ እንደሆኑ የሚወሰን ከሆነ አስርት ዓመታት የሚደርስ እስር ይጠብቃቸዋል።
ትራምፕ፤ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጋር ባላቸው ተመሳስሎሽ ምክንያት "ትራምፕ ኦፍ ዘ ትሮፒክስ" በሚል ስያሜ በሚጠሩት ቦልሶናሮ ላይ የቀረበውን ክስ "የሀሰት ውንጀላ ምርመራ" ሲሉ ገልጸውታል። ጉዳዩንም ትራምፕ በ2020 አሜሪካ ምርጫ የደረሰባቸውን ሽንፈት አለመቀበላቸውን ተከትሎ ከተከፈተባቸው ክስ ጋርም አመሳስለውታል።
በሐምሌ ወር ትራምፕ ከብራዚል ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለውን ቀረጥ ወደ 50 በመቶ ከፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ለዚህ እርምጃቸው በምክንያትነት የጠቀሱት የዣይር ቦልሶናሮን ጉዳይ ነው።

የፎቶው ባለመብት, ANDRE BORGES/EPA/Shutterstock
ከዚህም በተጨማሪ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስምንት የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ አግዷል። ከእነዚህ ዳኞች መካከል የቦልሶናሮን ክስ የሚመሩት ዳኛ አሌክሳንደር ዴ ሞሬስ ይገኙበታል።
የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉላ እርምጃው በሀገራቸው የፍትህ ስርዓት ውስጥ ተቀባይነት የሌለው ጣልቃ ገብነት እንደሆነ በመግለጽ እንደማይንበረከኩ ተናግረዋል።
ይህንን ተከትሎም የትራምፕ የ50 በመቶ ታሪፍ ባለፈው ሳምንት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ልጅ ኢድዋርዶ ቦልሶናሮ በዋሽንግተን ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ስላለው ቅርበት ወይም በብራዚል ላይ ታሪፍ እንዲጣል ተጽዕኖ አድርጎ እንደሆነ በግልጽ ከመናገር ተቆጥቧል።
"ፕሬዝዳንት ትራምፕን አደንቃለሁ። በመጀመሪያው እና በሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸው ብዙ ጊዜ ተገናኝተናል። በመጀመሪያ አሌክሳንድር ዴ ሞሬስ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ታግለናል። ነገር ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ታሪፍ በመጣል ቢጀምሩ ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ፤ በዚህ ምክንያትም እደግፈዋለሁ" ብሏል።
ከመጋቢት ወር ጀምሮ በአሜሪካ ውስጥ የሚገኘው የ41 ዓመቱ ኤድዋርዶ ቦልሶናሮ፤ ወደ ብራዚል ከተመለሰ እስር እንደሚጠብቀው በመስጋት "በስደት" እንደሚኖር ተናግሯል።
የሀገሩን ኢኮኖሚ የሚጎዳ ማዕቀብ እንዲጣል መጎትጎቱን ተከትሎ የሚቀርብበትን ሀገር ወዳድ አይደለም የሚሉት ትችቶችን ውድቅ አድርጓል። "ከኢኮኖሚ በፊት ነጻነት እንደሚቀድም አምናለሁ" ሲል አቋሙን አስረድቷል።















