የብራዚል ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዚዳንት በእግራቸው ላይ መከታተያ እንዲያጠልቁና የሰዓት እላፊ እንዲጣልባቸው ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የብራዚል ፍርድ ቤት በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተከሰሱት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጄይር ቦልሶናሮ ሊያመልጡ ይችላሉ በሚል ስጋት በእግራቸው ላይ መከታተያ እንዲያጠልቁ እና የሰዓት እላፊ እንዲጣልባቸው ውሳኔ አሳለፈ።
ቦልሶናሮ ከአውሮፓውያኑ 2019 እስከ 2022 ብራዚልን የመሩ ሲሆን፤ ተተኪያቸው ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ሥልጣን እንዳይረከቡ ለማድረግ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማድረግ ተከስሰዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ምንም ዓይነት ጥፋት አልፈጸምኩም ሲሉ ያስተባብላሉ።
ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቦልሶናሮ ላይ የተመሠረተው ክስ እሳቸውን ለማሳደድ ነው በሚል እንዲቀለበስ ካለበለዚያ ብራዚል ከፍተኛ ታሪፍ እንደሚጣልባት ማስፈራራታቸውን ተከትሎ ነው።
ቦልሶናሮ የፍርድ ቤቱን የእንቅስቃሴ እገዳ ውሳኔ "ከፍተኛ ውርደት" ሲሉ ጠርተው ብራዚልን ለቀው ለመውጣት አስበው እንደማያውቁ ተናግረዋል።
አርብ ዕለት ፖሊስ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የቀድሞውን ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት እና ዋና መሥሪያ ቤታቸው ላይ ድንገተኛ ፍተሻ አድርጓል።
ቦልሶናሮ ከየትኛውም ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲታገዱ እንዲሁም ክሳቸው እንዲሰረዝ በአሜሪካ እየወተወተ ካለው ልጃቸው ኤድዋርድ ቦልሶናሮ ጋር እንዳይገናኙም ዳኛ አሌሳንድሬ ዴ ሞራስ ወስነዋል።
በተጨማሪም ከውጭ አገር አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች ወይም ኤምባሲዎች ጋር ግንኙት እንዳይኖራቸውም ታግደዋል።
ቦልሶናሮ የ24 ሰዓት ክትትል የሚደረግባቸው ሲሆን፣ የምሽት ሰዓት እላፊም ተጥሎባቸዋል።
ዳኛ ሞራስ እንዳሉት ቦልሶናሮ ከልጃቸው ኤድዋርድ ጋር በመሆን ሆነ ብለው እና በሕገወጥ መንገድ በብራዚል ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል እየሠሩ ነው።
የቦልሶናሮ ጠበቆች የፍርድ ቤቱን ውሳኔ "አስደንጋጭ እና አስደናቂ" ሲሉ ገልጸው፤ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሁልጊዜም የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንደሚያከብሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአገሪቱ ፌደራል ፖሊስ በበኩሉ ቦልሶናሮ የፍርድ ሂደቱን ለማደናቀፍ ሞክረዋል እንዲሁም አገሪቱን የምትገደድበት ሁኔታ ውስጥ በማስገባት በብሔራዊ ሉዓላዊነት ላይ ጥሰትን ፈጽመዋል ሲል ከሷቸዋል።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የቦልሶናሮ ክስን በመጥቀስ አገሪቱ 50 በመቶ ታሪፍ በቅርቡ ይጣልባታል ሲሉ ዝተው ነበር።
ፕሬዚዳንት ሉላ በበኩላቸው አሜሪካ ለምትጥለው ታሪፍ አገራቸው አጸፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቀዋል።
ብራዚል "ገለልተኛ ተቋማት ያሏት ሉዓላዊት አገር ናት" እንዲሁም "ማንም ከሕግ በላይ አይደለም" ሲሉ ፕሬዚዳንት ሉላ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባወጡት እና ለቦልሶናሮ በላኩት ደብዳቤ፣ የተመሠረተባቸው የወንጀል ክስ ፖለቲካዊ ማሳደድ እንደሆነ እና የታሪፍ ዛቻቸው የብራዚል ባለሥልጣናት ክሱን እንዲያቋርጡ ጫና ለመፍጠር ነው ብለዋል።
ትራምፕ የቦልሶናሮን ክስ በሁለት የፕሬዚዳንትነት የሥልጣን ዘመናቸው ካጋጠሟቸው የሕግ ጉዳዮች ጋር አነጻጽረውታል።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሉላ በአውሮፓውያኑ 2023 ሥልጣን ከተረከቡ ከሳምንት በኋላ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ደጋፊዎች ቤተ መንግሥት፣ ምክር ቤት እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችን ጥሰው በመግባት አመጽ ያስነሱ ሲሆን፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ቦልሶናሮ እና ሌሎች 7 ሰዎች ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ስምንቱ ተከሳሾች በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፣ በታጣቂ ወንጀለኛ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ፣ የሕግ የበላይነትን በኃይል ለመገርሰስ በመሞከር እና ቅርሶችን በማበላሸት ጨምሮ አምስት ክሶች ቀርቦባቸዋል።
የ70 ዓመቱ ቦልሶናሮ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ አስርት ዓመታትን በእስር ሊያሳልፉ ይችላሉ።















