የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ለ8 ዓመታት ለመንግሥታዊ ሥልጣን እንዳይወዳደሩ ታገዱ

ጃየር ቦልሶናሮ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ጃየር ቦልሶናሮ

የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርቡ በምርጫ ተሸንፈው ሥልጣን የለቀቁት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጃየር ቦልሶናሮ ለስምንት ዓመታት መንግሥታዊ ሥልጣን ለመያዝ እንዳይወዳደሩ አገደ።

ቦልሶናሮ በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ከተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት ሥልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመዋል ተብለው ጥፋተኛ መሆናቸው በፍርድ ቤት ተረጋግጦባቸዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለምርጫ ጥቅም ላይ የዋሉት ኤሌክትሮኒክ የድምጽ መስጫ መሳሪያዎች ለስርቆት እና ለማጭበርበር የተጋለጡ ናቸው በማለት የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሐሰት አንኳሰዋል በሚል ተከሰው ነበር።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ቦልሶናሮን ለስምንት ዓመታት ለሥልጣን እንዳይወዳደሩ የወሰነው አምስት ለሁለት በሆነ አብላጫ ድምጽ ሲሆን፣ ጠበቆቻቸው በውሳኔው ላይ ይግባኝ ይጠይቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጠበቆቻቸው ቦልሶናሮ የምርጫውን ሂደት በተመለከተ የሰጡት አስተያየት በምርጫው ውጤት ላይ ተጽእኖ አልነበረውም በማለት የቀረበባቸውን ክስ ተገቢ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ።

በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ የተጣለው የስምንት ዓመታት ዕገዳ የሚጀምረው ምርጫው ከተካሄደበት ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ነው።

ይህ የእገዳ ውሳኔ የሚጸና ከሆነ ቦልሶናሮ በአውሮፓውያኑ 2026 በሚካሄደው የብራዚል ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ መሳተፍ የማይችሉ ሲሆን፣ በ2030 ግን የዕግድ ገደቡ ስለሚያበቃ ሊሳተፉ ይችላሉ።

በተጨማሪም በሚቀጥለው ዓመት 2024 እና ከዚያም በኋላ በ2028 በሚካሄዱ የከተሞች ማዘጋጃ ቤት ምርጫ ላይ በዕጩነት ሊቀርቡ አይችሉም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቦልሶናሮ በውሳኔው “ከጀርባ የመውጋት” ድርጊት እንደተፈጸመባቸው በመግለጽ፣ በብራዚል ውስጥ የቀኝ ክንፍ ፖለቲካን ለማራመድ መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ የቀረበው ዋነኛው ክስ በሥልጣን ላይ ሳሉ ባደረጉት ንግግር ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው።

በዚህም ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ከምርጫው በፊት በዋና ከተማዋ ብራዚሊያ ውስጥ ባለው በመኖሪያ ቤታቸው ዲፕሎማቶችን ጋብዘው ባደረጉት ንግግር ላይ፣ ያለማስረጃ የብራዚል የምርጫ ድምጽ መስጫ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ለመጠነ ሰፊ ስርቆት እና ለማጭበርበር የተጋለጡ ናቸው ብለው ነበር።

ነገር ግን ቦልሶናሮ በንግግራቸው “ብራዚል ውስጥ ምርጫ እንዴት እንደሚካሄድ ነው የተናገርኩት” በማለት የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓትን እንዳላጠቁ እና እንዳልተቹ በመናገር አስተባብለዋል።

ንግግራቸው እጅግ በተካረረ ሁኔታ ሲካሄድ በነበረው የምርጫ ፉክክር ወቅት የነበረ ሲሆን፣ ቦልሶናሮ ተቀናቃኛቸው የሆኑት የግራ ክንፉ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ዳ ሲልቫ ከባድ ፈተና ገጥሟቸው ነበር።

በሁለቱ ዕጩዎች መካከል ከባድ ፉክክር የተካሄደብት የመጀመሪያው ዙር ምርጫ አሸናፊው ባለመለየቱ ወደ ሁለተኛ ዙር ፉክክር ተሸጋግሮ ሉላ በጠባብ የድምጽ ብልጫ ማሸነፍ መቻላቸው ይታወሳል።

ቦልሶናሮ ግን እስካሁን ድረስ በይፋ ሽንፈታቸውን ያልተቀበሉ ሲሆን፣ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ቃለ መሐላ ፈጽመው ሥልጣን ከመረከባቸው ሁለት ቀናት በፊት ወደ አሜሪካ ሄደዋል።

በጥር ወር መጀመሪያ ላይም የቦልሶናሮን ሽንፈት ያልተቀበሉት ደጋፊዎቻቸው የብራዚል ምክር ቤትን፣ የፕሬዝዳንቱን ቤተ መንግሥትን እና የአገሪቱን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንጻን ወረው ጥቃት ፈጽመዋል።