በአሜሪካዋ ከተማ ላስቬጋስ ውስጥ ‘ሊትል ኢትዮጵያ’ የሚባል ወረዳ ተሰየመ

ክላርክ ካውንቲ በምሽት

የፎቶው ባለመብት, Clark County/fb

የምስሉ መግለጫ, ክላርክ ካውንቲ በምሽት

በአሜሪካ ኔቫዳ ግዛት፣ ላስቬጋስ ውስጥ በምትገኘው ክላርክ ካውንቲ ‘ሊትል ኢትዮጵያ’ [ትንሿ ኢትዮጵያ ] የሚባል አካባቢ መሰየሙን የዘመቻው አስተባባሪ አቶ ግርማ ዛይድ ለቢቢሲ ገለጹ።

እንደ አቶ ግርማ ከሆነ ከ120 በላይ አገራት ዜጎች በሚኖሩባት ኔቫዳ ግዛት ለኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ‘ሊትል ኢትዮጵያ’ በሚል ወረዳ ሲሰይም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ምንም እንኳን በዘልማድ አንድ የአገር ዜጎች በብዛት የሚኖሩበት እና የሚሠሩበት አካባቢ የመጡበትን አገር መጠሪያ ቢያገኝም በአገረ ገዢ ደረጃ አዋጅ ወጥቶለት ሲጸድቅ ይህ የመጀመሪያው መሆኑን አቶ ግርማ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የአሜሪካ ከተሞች በሆኑት በዋሽንግተን ዲሲ እና በሎስ አንጀለስ እንዲሁም በካናዳ ቫንኮቨር ውስጥ መንገዶች ተሰይመውላታል።

ነገር ግን ይህ በኔቫዳ፣ ላስቬጋስ ውስጥ ትንሿ ኢትዮጵያ በሚል የሚጠራ አንድ አካባቢ ሲሰየም ይህ የመጀመሪያው መሆኑን አስተባባሪዎቹ ይናገራሉ።

ይህንን ስያሜ ለማግኘት እንቅስቃሴ የተጀመረው ከ40 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ባሉበት ከተማ እንዴት አንድ የባህል ማሳያ አካባቢ አይሰየምም በሚል መነሻ ነበር።

ሐሳቡን የጀመሩትም በላስቬጋስ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ሴንተር ሰብሳቢ አሌክሳንደር አሰፋ ነበሩ። ሒደቱም አራት ዓመታትን ወስዷል።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በሌሎች ተግዳሮቶች የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጓትቶ የቆየ ሲሆን፣ አቶ ግርማ ከኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ሴንተር ቦርድ ዳሬክተሮች ጋር በመነጋገር ነበር ፕሮጀክቱ እንደገና መንቀሳቀስ የጀመረው።

አቶ ግርማ ዛይድ አካባቢውን በኢትዮጵያ ስም እንዲሰየም ውሳኔው በተሰጠበት ጊዜ ምስጋና ሲያቀርቡ

የፎቶው ባለመብት, reviewjournal.com

የምስሉ መግለጫ, አቶ ግርማ ዛይድ አካባቢውን በኢትዮጵያ ስም እንዲሰየም ውሳኔው በተሰጠበት ጊዜ ምስጋና ሲያቀርቡ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ጀምሮም አቶ ግርማ የንዑስ ኮሚቴው ሊቀመንበር ሆነው ፕሮጀክቱን ሲመሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አቶ ግርማ እንዳሉት የኢትዮጵያን ባህል የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን በማንሳት እንዲሁም የፕሮጀክቱን አላማ ለግዛቱ ባለሥልጣናት ማቅረባቸውን እና ከዚያም በኋላ በተደረጉ ጥረቶች ሐሳቡ በሙሉ የኮሚሽነሮች ድምጽ ጸድቆ ወደ አገረ ገዢው ተልኮ ከአስር ቀናት በፊት ሊጸድቅ ችሏል።

“በኔቫዳ ታሪክ የመጀመሪያ ስለሆነ ውሳኔውን ያሳለፉት ተጠንቅቀው ነው” የሚሉት አቶ ግርማ፣ ለሁለት ዓመት በፖለቲከኞች እና በኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች በተደረገው ጥረት ውጥኑ ለስኬት መብቃቱን ይናገራሉ።

ለኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አንድ ሰፈር ማሰየም ከባድ ነው የሚሉት አቶ ግርማ፣ ፋይዳው ግን ዘርፈ ብዙ ነው ይላሉ።

የዓለም ቱሪስቶች ማዳረሻ በሆነችው ላስቬጋስ የትንሿ ኢትዮጵያ መመሥረት ኢትዮጵያን ለሰፊው ዓለም ማስተዋወቅ ዋነኛው ዓላማ ነው።

“አፄ ኃይል ሥላሴ የአፍሪካ ኅብረትን መቀመጫ አዲስ አበባ ሲያደርጉ ትልቅ ድል እንደነበረው ሁሉ ‘ሊትል ኢትዮጵያ’ የተባለ አካባቢ መሰየሙ ኢትዮጵያ የ3000 ዓመት ታሪክ ያላት፣ ቅኝ ያልተገዛች አፍሪካዊት አገር” መሆኗን ለልጅ ልጆች ለማስተላለፍ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪም ለኢትዮጵያውያኑ የንግድ ሱቆች እና ምግብ ቤቶች መስፋፋት አስተዋጽኦ ያደርጋል። ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳው ቀላል አይደለም።

አቶ ግርማ በቀጣይም ሌሎች ዕቅዶች አሏቸው። አንደኛው በላሊበላ ውቅር ቤተ ክርስቲያን አምሳያ 'እንኳን ወደ ትንሿ ኢትዮጵያ በደህና መጣችሁ' [ ዌልካም ቱ ሊትል ኢትዮጵያ] የሚል ሐውልት ማስቀረጽ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ወደ ቱሪስት አካባቢው በሚወስደው አውራ መንገድ ላይ 'ሊትል ኢትዮጵያ' ብሎ ማሰየም ነው።

በኔቫዳ ግዛት ውስጥ በኢትዮጵያ ስም የተሰየመ አካባቢ የሚገኝበት ክላርክ ካውንቲ ውስጥ ቢያንስ 17 የኢትዮጵያ ምግብ ቤቶችን ጨምሮ ከ50 በላይ የኢትዮጵያውያን የንግድ ተቋማት እንደሚገኙ የላስ ቬጋስ ሪቪው ጆርናል ዘገባ ያመለክታል።