የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ የሚፈልገውን ግለሰብ ከኢራን ጠልፎ መውሰዱን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, ISRAEL MINISTRY OF FOREIGN AFFAIRS
የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ ቆጵሮስ ውስጥ እስራኤላውያንን ለመግደል አቅዷል የተባለ ቡድን መሪ ነው ተብሎ የተጠረጠረን ግለሰብ ኢራን ውስጥ ዘልቆ በመግባት ለመያዝ መቻሉን አስታወቀ።
ለመገናኛ ብዙኃን እምብዛም መረጃን የማይሰጠው የእስራኤል የስለላ ተቋም ሞሳድ እንዳለው፣ ከኢራን ጠልፎ የወሰደው ተጠርጣሪው ግለሰብ፣ ከኢራን አብዮታዊ ዘብ የተሰጠውን ትዕዛዝ በሚመለከት በዝርዝር “የዕምነት ቃሉን” እንደሰጠ ገልጿል።
ሞሳድ በእስራኤላውያን ዜጎች ላይ ቆጵሮስ ውስጥ ግድያን ሊፈጽም ስለነበረው ገዳይ ቡድን ለቆጵሮስ ባለሥልጣናት መረጃ መስጠቱን እና ጥቃት ፈጻሚ ህዋሱም እንዲበተን መደረጉን አመልክቷል።
ይህ የሞሳድ ኦፕሬሽን ለረጅም ዘመናት በጠላትነት ሲፈላለጉ በነበሩት እስራኤል እና ኢራን መካከል ያለው ተዘዋዋሪ ፍልሚያ መቀጠሉን ያመለክታል ተብሏል።
ባልተለመደ ሁኔታ ሞሳድ ኢራን ውስጥ ያካሄደውን ዘመቻ በይፋ ሊገልጽ የቻለው፣ አሜሪካ እና ኢራን ስለኑክሌር መረሃ ግብሯ በተዘዋዋሪ ሁኔታ ንግግር መጀመራቸውን የሚያመለክቱ ዘገባዎች በመውጣታቸው ሰበብ ሊሆን እንደሚችል አንድ የዘርፉ ባለሙያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“እስራኤል የወሰደችውን እርምጃ በተመለከተ ይፋ ያደረገችው፣ ከኢራን ጋር በኑክሌር መረሃ ግብሯ ዙሪያ ስምምነት ቢደረግ እንኳን ኢራን አስቸጋሪነቷ ዘላቂ መሆኑን ለዓለም ማሳየት ስለፈለገች ነው” ሲሉ በኢራን እና በእስራኤል የቆየ ፍጥጫ ዙሪያ መጽሐፍ ያሳተሙት ጋዜጠኛ እና ደራሲ ያኮቭ ካትዝ ተናግረዋል።
ጨምረውም “ኢራን አውሮፓን በመሳሰሉ ሥፍራዎች ነጋዴዎችን ለመግደል ሞክራለች፣ ስለዚህም ለኑክሌር ጦር መሳሪያ የሚውለውን ዩራኒየም ከማበልጸጓ ባሻገር በርካታ ነገሮችን ፈጽማለች” ብለዋል።
እስራኤል ቆጵሮስ ውስጥ ዜጎቿን ለመግደል በኢራን አማካይነት ተቀነባብሮ ነበር ያለችውን ሴራ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ ያልተቻለ ሲሆን፣ ከኢራንም ሆነ ከቆጵሮስ በኩል እስካሁን ስለጉዳዩ የተሰጠ ምላሽ የለም።
ሞሳድ ባወጣው መግለጫ ላይ ተካሄደ ያለውን ተልዕኮ “በኢራን ግዛት ውስጥ የተፈጸመ ልዩ ድፍረት የተሞላበት” በማለት ገልጾታል።
አንድ ከፍተኛ የሞሳድ ከፍተኛ ባለሥልጣንም “በየትኛውም የዓለም ክፍል ውስጥ በሚገኙ አይሁዳውያን እና እስራኤላውያን ላይ የሽብር ጥቃትን የሚያስፈጽሙ ባለሥልጣናትን የኢራን ግዛትን ጨምሮ ባሉበት ቦታ ሁሉ እናገኛቸዋለን” ማለታቸው ተጠቅሷል።
በእስራኤል ባለሥልጣናት ይፋ በተደረገ ቪዲዮ ላይ በጉዳዩ ዋነኛ ተጠርጣሪ እንደሆነ የተገለጸው ዩሴፍ ሻሃባዚ አባሳሊሉ የተባለ ግለሰብ፣ ከኢራን ውጭ ለሞሳድ ወኪሎች በፋርስ ቋንቋ ሲናገር አሳይቷል።
ግለሰቡ አንድ እስራኤላዊ ነጋዴን ለመግደል በቱርክ ቁጥጥር ሥር ወዳለው ሰሜን ቆጵሮስ በመግባት በሕገወጥ መንገድ ወደ ደቡቡ ክፍል መግባቱን ያስረዳል። የግለሰቡን አድራሻ እና ፎቶግራፍ በኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ውስጥ ያለ አዛዡ እንደላከለትም ተናግሯል።
“ግለሰቡን እዚያ መኖሩን እና የት ሊሄድ እንደሆነ ካወቅኩ በኋላ ዕቅዴ እንቅስቃሴ የሌለበት እና ጸጥ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር በጥይት መግደል ነበር” በማለት በሞሳድ ተይዟል የተባለው ግለሰብ ሲናገር ይሰማል።
ግለሰቡ ኢላማው የሆነውን እስራኤላዊ ከለየ እና የመኖሪያ ቤቱን ፎቶ ካነሳ በኋላ፣ በፖሊስ እየተፈለገ መሆኑ ስለተነገረው ከቆጵሮስ በመውጣት ወደ ኢራን ተመልሷል ተብሏል።
በሞሳድ ከኢራን ተይዞ የወጣው እና ግድያውን ሊፈጽም እንደነበር ሲያምን በቪዲዮ የተቀዳው ግለሰብ በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቃሉን እየሰጠ ይሁን አይሁን ግልጽ አይደለም።
ሞሳድ ግለሰቡን ከኢራን ግዛት ውስጥ መቼ እና ከየት ቦታ ይዞ እንዳወጣው እንዲሁም ቆጵሮስ ውስጥ ሊፈጸም የነበረው ጥቃት ለመቼ ታስቦ እንደነበር ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
የኢራን መንግሥት እስራኤልን ለማውደም የሚያደርገውን ተደጋጋሚ ዛቻ እና ጥቃት የሚፈጽሙባትን ታጣቂ ቡድኖችን ትደግፋለች በማለት እሰራኤል ለረጅም ዘመናት ኢራንን እንደ ዋነኛ ጠላቷ ስትመለከታት ቆይታለች።
እንደ አሜሪካ እና አውሮፓ አገራት ሁሉ እስራኤልም ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለመገንባት እየጣረች መሆኗን ታምናለች። ነገር ግን ኢራን የኑክሌር መረሃ ግብሯ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል ነው ትላለች።
በቅርብ ዓመታትም እስራኤል በኢራን የኑክሌር ተቋማት ላይ ተከታታይ ጥቃቶችን የፈጸመች ሲሆን፣ በርካታ የኢራን የኑክሌር ሳይንቲስቶችን በመግደልም ትከሰሳለች።
ከአምስት ዓመት በፊት ድፍረት በተሞላበት ተልዕኮ የሞሳድ ወኪሎች በኢራን ዋና ከተማ የሚገኝ የሰነዶች ማከማቻን ሰብረው በመግባት ከፍተኛ መጠን ያላቸውን የአገሪቱን የኑክሌር መረሃ ግብርን የተመለከቱ ሰነዶች መዝረፋቸውን እስራኤል ማሳወቋ ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት ቱርክ ውስጥ የሚገኙ እስራኤላውያን እና ቱሪስቶች ከኢራን በኩል ስጋት እንዳለ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ከቱርክ በአስቸኳይ እንዲወጡ ታዘው ነበር።
ኋላ ላይ የቱርክ የፀጥታ ኃይሎች ከዚሁ ማስጠንቀቂያ ጋር በተያያዘ የታጠቁ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አሳውቀዋል።
የመገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡትም የእስራኤል የደኅንነት ሠራተኞች ኢራን ውስጥ ሁለት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባለሥልጣናትን ጠልፈው ምርመራ አድርገውባቸዋል።
ከመካከላቸውም አንዱ ቱርክ ውስጥ አንድ የእስራኤል ዲፕሎማትን፣ ጀርመን ውስጥ ያሉ የአሜሪካ ጄኔራልን እንዲሁም ፈረንሳይ ውስጥ ያለ ጋዜጠኛን ለመግደል በተደረጉ ጥረቶች ውስጥ የተሳተፉ ናቸው ተብሏል። ይህንን የሚያመለክት ያልተረጋገጠ የድምጽ ቅጂም ይፋ ተደርጎ ነበር።
ያኮቭ ካትዝ እንደሚያምኑት ሞሳድ ኢራን ውስጥ ፈጽሞታል የተባለውን ዘመቻ ዝርዝር ይፋ የማድረጉ ዋና አላማ እስራኤል በዓለም ዙሪያ ላሉ ወዳጆቿ “ኢራን በምዕራቡ ዓለም ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኗን” ለማሳሰብ እና ከተመሳሳይ ድርጊት እንድትታቀብ ለማስጠንቀቅ ያደረገችው ነው።
“ኢራናውያን በደኅንነት እና በስለላ ተቋሞቻቸው ሥራ ውስጥ እስራኤላውያን በተሳካ ሁኔታ ሰርገው በመግባት የተሳካ ሥራ ማከናወናቸውን ያውቃሉ” ይላሉ ካትዝ።
አክለውም እንደ አሁኑ ያከናወኗቸውን ተልዕኮዎች ይፋ ሲያደርጉ “ለኢራናውያን ከፍተኛ ሃፍረት ሲሆን፣ የእስራኤላውያንን የስለላ ድርጅት ጥንካሬን አጉልቶ ያሳያል” ብለዋል።












