በኢራን ፋብሪካ ላይ እሳት ያስነሳውን የበይነ መረብ ጥቃት የፈጸመው ማነው?

የፎቶው ባለመብት, Predatory Sparrow
በዚህ ዘመን አገራትን ከሚያሳስቡ ጥቃቶች መካከል ቀዳሚው በበይነ መረብ በኩል የሚፈጸሙት እየሆኑ ነው።
በበይነ መረብ በኩል የሚፈጸም ጥቃት የአገራትን የትራንስፖርት፣ የኃይል እና ሌሎች የመሠረታዊ አገልግሎቶችን በማቃወስ እያንዳንዱን ዜጋ ይነካል።
አስካሁን ባለው ልምድ በበይነ መረብ በኩል የሚፈጸሙ ጥቃቶች መረጃዎችን በማዛባት እና በማስተጓጎል የተለመዱትን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎችን በማወክ፣ በአገራት ደኅንነትና ምጣኔ ሀብት ላይ ቀውስን ሲፈጥሩ ነው የሚታወቁት።
አሁን ግን በበይነ መረብ በኩል የሚፈጸሙት ጥቃቶች የሚታዩ ተጨባጭ፣ ቁሳዊና እና አካላዊ ጉዳትን ማድረስ እንደሚችሉ የሚያመለክቱ ክስተቶች እየታዩ ነው።
ይህም መረጃዎችን በመመዝበር በሚታወቁት የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች (ሃከርስ) አማካይነት የሚፈጸም ጥቃት ነው።
እንዲህ አይነቱ ተጨባጭ ጉዳት የሚያደርስ ጥቃት ከሁለት ሳምንት በፊት በኢራን የብረት ብረት ማምረቻ ፋብሪካ ላይ ተፈጽሞ፣ በበይነ መረብ በኩል የሚታይ እና የሚዳሰስ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ማሳያ ሆኗል።
ለዚህ ጥቃት ‘ፕሬዳቶሪ ስፓሮው’ የሚባል የበይነ መረብ ሰርሳሪ ቡድን ኃላፊነቱን ወስዷል። ቡድኑ በኢራኑ ፋብሪካ ላይ ከባድ የእሳት ቃጠሎን እንዳስነሳ በመግለጽ፣ ይህንንም የሚያሳይ የቪዲዮ ማስረጃ ይፋ አድርጓል።
ቪዲዮው በደኅንነት ካሜራ የተቀረጸ ሲሆን፣ አንደኛው ማሽን በእሳት ተያይዞ የቀለጠ ብረት መርጨት ከመጀመሩ በፊት የብረት ማቅለጫ ፋብሪካው ሠራተኞች ከቦታው ሲወጡ እና በመጨረሻም እሳቱን ለማጥፋት ሲጥሩ ይታያሉ።
በሌላ ቪዲዮ ላይ ደግሞ አንድ የፋብሪካው ሠራተኞ የእሳት አደጋ ሠራተኞች እንዲጠሩና በማሽን ላይ ስለደረሰው ጉዳት ጮክ ብሎ ሲናገር ይታያል።

የፎቶው ባለመብት, Predatory Sparrow
“ጥንቃቄ የተሞላበት ጥቃት”
ከዚህ ጥቃት ጀርባ እንዳለ የሚናገረው ‘ፕሬዳቶሪ ስፓሮው’ ባለፈው ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ በኢራን የብረታ ብረት ማምረቻዎች ላይ ሦስት ጥቃቶችን መድረሱን አመልክቷል። ለዚህም በግለጽ ያላብራራውና በኢራን ተፈጽመዋል ላላቸው “የፀብ አጫሪነት” ድርጊት ምላሽ ነው ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ ከፋብሪካዎቹ ሰረቅኳቸው ያላቸውን ምስጢራዊ ኢሜይሎችን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን መረጃዎች ይፋ ማድረግ ጀምሯል።
የበይነ መረብ ሰርሳሪው ‘ፕሬዳቶሪ ስፓሮው’ በቴሌግራም ገጹ ላይ እንዳሰፈረው የጥቃቱ ኢላማ የሆነት ፋብሪካዎች “ዓለም አቀፍ ማዕቀብ የተጣለባቸው ቢሆንም ሥራቸውን ቀጥለዋል። በተፈጸሙት የበይነ መረብ ጥቃቶቻችን ንጹሃን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ አድርገናል።”
ይህም የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች የሚፈጽሙት ጥቃት የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል መግለጻቸው፣ እንዲህ አይነቶቹ ጥቃቶች አካላዊ ጉዳት ማድረስ ወደሚችሉበት ደረጃ መሸጋገራቸውን ያመለክታል። ይህም አገራትን ከሚያሳስባቸው ጉዳይ አንዱ መሆኑ ተነግሯል።
ጥቃት ፈጻሚዎቹ በሰው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ያደረጉት ጥንቃቄ ሙያተኞች መሆናቸውንና በመንግሥት የሚደገፉ ወታደራዊ የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬንም ፈጥሯል። ጥቃቱን ከመፈጸማቸው በፊትም ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በመገምገም በጥንቃቄ መደረጉ የመረጃ መረብ ጥቃት ወደ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን አመልካች ነው።

የፎቶው ባለመብት, PREDATORY SPARROW
ኢራን እና እስራኤል
ከእስራኤልና ከአሜሪካ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ያለችው ኢራን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከታታይ የበይነ መረብ ጥቃቶች ኢላማ ሆናለች። ከዚህ በፊት የተፈጸሙት ጥቃቶች የራሳቸው የሆነ ተጽእኖን ያስከተሉ ቢሆንም የአሁኑን አይነት ግን ከባድ ተጨባጭ ጉዳትን አላደረሱባትም።
ከ12 ዓመት በፊት ኢራንን ከምዕራባውያን ጥርስ ውስጥ ባስገባት የዩራኒየም ማበልጸጊያ ማዕከሏ ላይ ‘ስተክስኔት’ የተባለው የበይነ መረብ ጥቃትም እንዲሁ በተቋሙ ላይ ተጨባጭ ጉዳትን አስከትሎ ነበር።
ይህ ‘ስተክስኔት’ የኮምፒውተር ቫይረስ ጥቃት፣ ናትዛን በሚባለው ቦታ ኢራን ባላት የዩራኒየም ማበልጸጊያ ማዕከል ውስጥ ያሉ ማብላያዎችን በመጉዳት ወይም ማውደም፣ የአገሪቱን የኑክሌር ፕሮግራምን አደናቅፎታል ተብሎ ይታመናል።
ከዚያ በኋላ ግን እንዲህ አይነቱ ተጨባጭ ቁሳዊ ጉዳትን ያደረሱ የተረጋገጡ በጣም ጥቂት ጥቃቶች ብቻ አጋጥመዋል።
ተመሳሳይ ጥቃት ጀርመን ውስጥ በ2014 (እአአ) ተከስቶ በአንድ የብረት ፋብሪካ ላይ “ከባድ ጉዳት” በማድረስ ሥራው እንዲቆም ማስገደዱን የአገሪቱ የመረጃ መረብ ደኅንነት ባለሥልጣን ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
በተጨማሪም የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች የአንድ የውሃ ማጣሪያ ተቋም የመረጃ መረብን ሰብረው በመግባት በውሃ አቅርቦቱ ላይ ኬሚካል ለመጨመር ሞክረው ከሽፎባቸዋል። ይህ ጥቃት ቢሳካ ኖሮ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችል ነበር ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
አሳሳቢው የበይነ መረብ ጥቃት አይነት
በበይነ መረብ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የትራንስፖርት ሥርዓትን በማወክ መስተጓጎል ከመፍጠር ባሻገር ተጨባጭ ጉዳትን ሲያስከትሉ አልታዩም ነበር።
ይህ በኢራን ላይ ተጨባጭ ጉዳትን ያስከተለው የ‘ፕሬዳቶሪ ስፓሮው’ የበይነ መረብ ጥቃት ወዴት ሊያመራ እንደሚችል አስካሁን አልታወቀም።
ይህ ጥቃት በአንድ አገር አማካይነት የተፈጸመ ከሆነ ግን ኢራን ዓለም አቀፍ ሕግን መሠረት አድርጋ ምላሽ ለመስጠት ያስችላታል ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።
በብረታ ብረት ፋብሪካዋ ላይ የተፈጸመው የበይነ መረብ ጥቃት በመንግሥት የሚደገፍ ወታደራዊ ጥቃት ከሆነ ከበስተጀርባው ያለው አገር ማን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ለመገመት ብዙም አስቸጋሪ አይሆንም።
ቀደም ሲል በዩራኒየም ማበልጸጊያ ተቋሟ ላይ የተፈጸመው ‘ስተክስኔት’ የተሰኘው ጥቃትን አስራኤል በአሜሪካ ድጋፍ እንደፈጸመችው ይታሰባል።
‘ፕሬዳቶሪ ስፓሮው’ በተባለው ቡድን አሁን የተፈጸመው የበይነ መረብ አደገኛ ጥቃት በእሷ ተፈጽሟል በሚሉ ይፋ ባልወጡ ሹክሹክታዎች ምክንያት የእስራኤል መንግሥት አንዳች ነገር ለማድረግ ተገዷል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ፣ የአስራኤል ጋዜጠኞችን ከኢራኑ ጥቃት ጀርባ አገራቸው እንዳለች ፍንጭ በሰጣቸው ጉዳይ ላይ ምርመራ እንዲደረግ አዘዋል።
“ኢራን እና አስራኤል በበይነ መረብ ጦርነት ላይ መሆናቸውን ሁለቱም አገራት በይፋ የሚያምኑት ጉዳይ ነው። እናም ኢራን ላይ የተፈጸመው የበይነ መረብ ጥቃት በመንግሥት የተቀናበረ ከሆነ፣ እስራኤል ቀዳሚዋ ተጠርጣሪ ትሆናለች” ሲሉ ቱርክ አንካራ ውስጥ የሚገኘው የኢራን ጥናት ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ኢርሲን ካህሙቶግሉ ተናግረዋል።
አክለውም “ሁለቱም አገራት በደኅንነት መሥሪያ ቤቶቻቸው አማካይነት የበይነ መረብ ጥቃት ሲያቀናብሩ ቆይተዋል። ይህም ከሁለት ዓመት በፊት ኢራን በእስራኤል የውሃ አቅርቦት መሠረተ ልማት ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት ተከትሎ ከአስራኤል በኩል በተሰነዘረ የአጸፋ ጥቃት ተባብሷል” ብለዋል።
በዚህ ጥቃት በአገሪቱ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ በተሞከረ የበይነ መረብ ጥቃት በውሃው ውስጥ የሚጨመረውን የክሎሪን መጠን ለመጨምር መሞከሩ ተነግሯል። ሙከራው ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ ከባድ የመመረዝ አደጋን ያስከተል እንደነበር ይታመናል።

ቀደም ያሉት ጥቃቶች
ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ይኸው ‘ፕሬዳቶሪ ስፓሮው’ የተባለው ቡድን በኢራን ብሔራዊ ነዳጅ ማደያ የክፍያ መፈጸሚያ ሥርዓት ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆን የሚያደርግ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።
በተጨማሪም በኢራን ውስጥ ያሉ ዲጂታል የመንገድ ላይ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን በመጥለፍ፣ የአገሪቱን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒን የሚጠቅስ መልዕክት እንዲታይ አድርጓል። እንዲሁም በኢራን የባቡር ጣቢያዎች የጉዞ ሰሌዳዎች ላይ የተሳሳቱ መልዕክቶች ከታዩበት ጥቃት ጋርም ግንኙነት እንዳለው ይታመናል።
ነገር ግን እነዚህ ጥቃቶች ቀላል የሚባሉ ሲሆኑ፣ በተጨባጭ የሚታዩ ጉዳቶችን ያስከተሉ አልነበሩም። ባለሙያዎች እንደሚሉት አሁን በአገሪቱ የብረታ ብረት ፋብሪካ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ግን የበይነ መረብ ጥቃቶች የት ድረስ ሊሄዱ እንደሚችሉ አመልክቷል።
የበይነ መረብ ጥቃቱ የተፈጸመበት ሞባራካህ የተባለው የብረት ማምረቻ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ግን፣ በጥቃቱ የፋብሪካው ሥራ እንዳልተስተጓጎለና የተጎዳም ሰው እንደሌለ ተናግረዋል። ኢላማ የተደረጉ ሌሎች ሁለት ተቋማትም ምንም ችግር እንዳልገጠማቸው ገልጸዋል።
መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው ኢራናዊ ተቃዋሚ እና በግል የመረጃ መረብ ስለላዎችን የሚመረምረው ናሪም ጋሪብ፣ በብረት ፋብሪካው ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የሚያሳየው ቪዲዮ ትክክለኛ ነው ይላል። የእሳት አደጋውን የሚያሳዩ ተጨማሪ ሁለት ቪዲዮዎች ትዊተር ላይ መውጣታቸውን ገልጿል።
በበይነ መረብ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከዝቅተኛው ደረጃ አልፈው ጠንከር ወዳለ ደረጃ መድረሳቸውንም ይናገራል።
“አስራኤል ከዚህ ጥቃት ጀርባ ካለች፣ የበይነ መረብ ጥቃት አገልግሎቶችን ከማቋረጥ ባሻገር አሁን ተጨባጭ ጉዳትን ማድረስ እንደሚችሉ እያሳዩ ይመስለኛል። ይህ ደግሞ ሁኔታዎች በፍጥነት ሊባባሱ እንደሚችሉ ጠቋሚ ነው” ብሏል።
















