የቀድሞው የእስራኤል ሰላይ ሞሳድ ኢራን ላይ ያካሄዳቸውን ዘመቻዎች አጋለጡ።

ዮሲ ኮሀን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ ኃላፊ የነበሩት ዮሲ ኮኽን፤ አገራቸው ኢራን ላይ ታካሂዳቸው ስለነበሩት ዘመቻዎች ይፋ የሚያደርግ ቃለ መጠይቅ ሰጡ።

ተሰናባቹ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ኮኽን የኢራን የኒውክሌር መረጃዎች እንዴት እንደተሰረቁም ይፋ አድርገዋል።

በአውሮፓውያኑ 2018 የእስራኤል የስለላ ሠራተኞች ከአንድ መጋዘን ውስጥ በርካታ ሰነዶችን ሰርቀው ወደ እስራኤል ስለመላካቸው ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ናንታዝ ውስጥ በሚገኘው የኢራን ኒውክሌር ማብላያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ውስጥ የእስራኤል እጅ እንዳለበት የጠቆሙ ሲሆን፤ ለአንድ ኢራናዊ የኒውክሌር ተመራማሪ ሞትም እስራኤል ተጠያቂ ልትሆን እንደምትችል ጠቁመዋል።

ዮሲ ኮኽን ከሞሳድ ኃላፊነታቸው ባለፈው ሳምንት ነበር በጡረታ የተሰናበቱት።

የቀድሞው ኃላፊ ቃለ መጠይቁን ያደረጉት 'ቻናል 12 ኡቭዳ' ከሚባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ ላን ዳያን ጋር ሲሆን፤ ከእሳቸው ጋር የተደረገው ቆይታ በእስራኤል ቴሌቪዥን ሐሙስ ዕለት ተላልፏል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ዮሲ ኮኽንን የሞሳድ ኃላፊ አድርገው የሾሟቸው በአውሮፓውያኑ 2015 ነበር።

ነገር ግን ዮሲ ሞሳድን የተቀላቀሉት ገና በሀያዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ እያሉ 1982 ላይ ነበር።

የቀድሞው ኃላፊ በቃለ መጠይቁ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ከኢራን የተሰረቁት ሰነዶች ትልቅ ትኩረትን አግኝቷል።

2018 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተሰረቁትን ሰነዶች በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይዘው በውምጣት ኢራን ኒውክሌር እያበለጸገች ስለመሆኑ ለማስረዳት ሞክረው ነበር።

ኢራን ግን በወቅቱ የተባለው ነገር ሐሰት እንደሆነ በመግለጽ ውንጀላውን አጣጥላዋለች።

ዮሲ ኮኽን በኃላፊነታቸው ዘመን ከቴል አቪቭ ሆነው ኦፕሬሽኖችን ይከታተሉ ነበር።

የኢራን መጋዘን ላይ በተካሄደው ኦፕሬሽንም ላይ ከቴል አቪቭ ሆነው ተሳትፈዋል። በወቅቱ የሞሳድ ሰላዮች የኢራን ኒውክሌር መጋዘን ውስጥ ገብተው እስከ 30 የሚደርሱ ካዝናዎችን ሲከፍቱ ነበር ብለዋል የቀድሞው ኃላፊው።