የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር 'ንጉሡ' ኤል ቻፖ ሚስት ውጣ ውረድ

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES
ከቀናት በፊት የታዋቂው ሜክሲኳዊ አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪ ዮዋኪን "ኤል ቻፖ" ጉዝማን ሚስት ጥፋተኛ መሆኗን አምናለች።
አሜሪካ ዋሺንግተን የሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረበችው ኤማ ኮሮኔል አይስፑሮ ብዙ አፍ የሚያስዙ ጉዳዮችን አምናለች።
ኤማ፤ ኤል ቻፖ ጉዝማን ከእሥር ቤት እንደሚያልጥ አግዣለሁ፤ የሲናሎዋ የዕፅ አዘዋዋሪዎች 'ንጉሥ' እያለ ረድቸዋለሁ ብላለች።
የ31 ዓመቷ ኤማ የዕድሜ ልክ እሥራት እንዲሁም የ10 ሚሊዮን ብር ቅጣት ይጠብቃታል።
ኤማ ኮሮኔል አስገራሚ ህይወት
ኤማ ኮሮኔል አይስፑሮ በኒው ዮርክ የነበራት ሕይወት አብረቅራቂ የሚባል ነበር።
ምስጋና (ምስጋና ከተባለ) ለባለቤቷ እና ዕፅ አዘዋዋሪው ኤል ቻፖ ይግባውና። ኤል ቻፖ የመዝገብ ስሙ ጆአኪን ጉዝማን ሎዬራ ነው።
ኤማ በኋላ ላይ በፖሊስ ተይዛ ወደ ቨርጂኒያ እስር ቤት ተወረወረች፡፡ ታዲያ የዓለም የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር 'ንግሥቷ' ምን ገጠማት?
በአሌክሳንድሪያ የሚገኘው የዊልያም ትሩስዴል የአዋቂዎች እስር ቤት ጠባብ ክፍሎች አሉት። በቀይ ጡብ የተሠራችው አነስተኛ ክፍል ኤማ ኮሮኔል አይስፑሮ ብቻዋን የታሰረችበት ነው፡፡
ጊዜዋን የምታሳልፈው በማንበብ ነው። እንደ ጠበቃዋ ከሆነ "የፍቅር" ልብ ወለዶችን ማንበብ ትመርጣለች።
ማረሚያ ቤቱ በአንድ ወቅት ከነበራት ሕይወት ጋር የሚነጻጸር አይደለም፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ኤል ቻፖ ጉዝማን የተባሉ አልባሳት ለገበያ ለማቅረብ ዕቅድ ነበራት፡፡ ባልና ሚስቱ ሜክሲኮ ውስጥ በቅንጡ ኑሯቸው ሲታወቁ ሴት ልጁም ስሙን ተጠቅማ ወደ ፋሽን ጎራ ብላለች፡፡
በ2019 የባለቤቷ የፍርድ ሒደት ሲከናወን ኒው ዮርክ ነበረች። በውድ ጌጣ ጌጦች እና ሰዓት አሸብርቃ ነበር።
ከወራት በኋላ የ31 ዓመቷ ኤማ ኮሮኔል አይስፑሮ፤ ቨርጂኒያ የሚገኘው ዱለስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተያዘች።
ምክንያቱ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪው ባሏን ረድታለች በሚል ነው። የ64 ዓመቱ ኤል ቻፖ በኮሎራዶ ማረሚያ ቤት የዕድሜ ልክ እስራት ተከናንቦ ይገኛል፡፡
የኤፍቢአይ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ኮሮኔል ኮኬይን ለማከፋፈል አሲራለች። ባሏ እአአ በ2015 ከሜክሲኮ እስር ቤት ለማምለጥ ሲያቅድም አግዛዋለች ብለዋል፡፡

የፎቶው ባለመብት, ANADOLU AGENCY VIA GETTY IMAGES
የእሷ ታሪክ ከሚወሰልተው ባሏ እና ከወንጀል ድርጅቱ ጋር ተደምሮ የአደንዛዥ ዕፅ ንግድ ምስጢራዊ ዓለም በውስጡ ስለያዛቸው ሴቶች ፍንጭ ይሰጣል።
የኤማ ኮሮኔል ሚና
የዓለም የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን የሚያጠኑ ተንታኞች ኤማ ያልተለመደ ሚና እንዳላት ይናገራሉ፡፡
ታዋቂ እና ሥራ ፈጣሪ ናት። ባለቤቷ የዕፁን ንግድ ሲያሽከረክር ማን እንደሚያገኘው እና እንደማያገኘው በመወሰን ጠባቂው ትሆናለች።
በተለምዶ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ሚስቶች "በጣም ሳቢ" እና "ምንም ድርጅት የሌላቸው" ተደርገው ይታያሉ የሚሉት በሳንዲያጎ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ምሁር የሆኑት ሲሲሊያ ፋርኣን-ሜንዴዝ ናቸው፡፡
ኤማ ግን የተለየች በመሆን "ሴቶች የሥልጣን ቦታዎችን መያዝ እንደሚችሉ አሳይታለች" ይላሉ፡፡
በዕፅ ንግድ ሰንሰለት ውስጥ ኃይልን መጠቀም አደገኛ ሥራ ነው።
የአሜሪካ የአደንዛዥ ዕፅ ማስፈጸሚያ አስተዳደር ባልደረባ የነበሩት ዴሪክ ማልዝ "በዚህ ሥራ ውስጥ ሲሆኑ ሊያዙ አልያም ሊገደሉ ይችላሉ" ብለዋል፡፡
ኤማ ለፋሽን ኩባንያዋ ዕቅዷን እያጠናቀቀች ነበር። የፌዴራል መርማሪዎች ደግሞ አፍንጫዋ ስር ደርሰዋል። ማልትዝ "ዓለሟ በዙሪያዋ እየፈራረሰ ነበር። ግድግዳዎቿ እየረገፉ ነበር" ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
አፈና እና ግድያ
ባለቤቷ በችሎት ሲቀርብ ኤማ በብሩክሊን የፌዴራል አውራጃ ፍርድ ቤት ሰላጣ እየተመገበች ነበር፡፡ ሰላጣ ነፍሷ ነው። ከጓደኞቿ ጋር ካፍቴሪያ ሆና ስለ እናቶች እና እንዴት እነሱን መቋቋም እንደሚቻል እየቀለደች ነበር፡፡
ጠበቃዋ ሚሮ "ትልቅ ስብዕና አላት" ትላለች፡፡ "እኔ የማውቃት ኤማ በኃይል የተሞላች እና ሁልጊዜም ፈገግታ የማይለያት ናት፡፡"
ኤማ ጥምር የሜክሲኮ እና የአሜሪካ ዜግነት አላት። በ17 ዓመቷ ከጉዝማን ጋር ተዋወቀች። ብዙ ሳይቆይም ተጋቡ፡፡
ሁለት ልጆች አፈፍርተዋል። ማሪያ ጆአኪና እና ኤማሊ ይባላሉ፡፡
ባሏ ፍርድ ቤት በቀረበባቸው ጊዜያት በሙሉ በሚባል ደረጃ ችሎቱን ታድማለች። በእረፍት ጊዜ ደረጃዎች ላይ ታወራለች፡፡
በሜክሲኮ የዕፅ አዘዋወሪዎች ሰንሰለትን በማጥናት ያሳለፉት የፓሪሱ የደኅንነት ተንታኝ ሮማይን ለ ኩር ግራንድማይሰን "የሲናሎዋ ታዋቂ" ይሏታል። በቀይ የከንፈር ቀለም፣ በአልማዝ፣ በጠባብ ጂንስ፣ 'ቡቾና' የተሰኘ ዝነኛ ምስል ፈጥራለች፡፡
የጆርጅ ሜሶን ዩኒቨርስቲው ጓዳሉፔ ኮሬአ-ካብራ የኤል ቻፖ የእፅ ዝውውር ሰንሰለት በሚሠራበት በሜክሲኮ ሲናሎዋ ዙሪያ ጥናት አካሂዷል፡፡
ቡቾናን ሲገልጹም "በጣም ውድ ልብሶችን ይለብሳሉ፣ ሉዊ ቨታን ቦርሳዎች ያነግታሉ። ሁሉም ነገር በግነት የተሞላ ነው። ኤማ የምስሉ ቀንደኛ ወካይ ነች። ሁሉም ነገር ስለ መልክ እና ስለ ፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ነው" ይላሉ።
በጣም ከሚያስደንቋት ባህሪዎች መካከል አንዱ የዳሌዋ አስደናቂ ቅርጽ ነው፡፡
የእሷ አንፀባራቂ ምስል ከኤል ቻፖ የእፅ ዝውውር ሰንሰለት እንቅስቃሴዎች አስከፊ እውነታ ጋር ተቃራኒ ነው፡፡
ኤል ቻፖ ሕገ ወጥ የአደገኛ ዕፅ ገበያን ለመቆጣጠር ኃይል ይጠቀማል። ትርፉን ሚስቱ እና ቤተሰቡ ላይ አፍስሷል፡፡
በ2006 በሜክሲኮ ከ300,000 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። በዚያው ዓመት መንግሥት በእፅ አዘዋዋሪዎቹ ላይ ጦርነት ከፍቷል፡፡
የኤል ቻፖ ጠላቶች እና የቅርብ ጓደኞቹ ተጎጂ ሆነዋል። የአንዷ ፍቅረኛው አስከሬን መኪና ውስጥ ተገኝቷል። ግድያው በተቀናቃኝ ቡድን የተፈጸመ ነው ተብሏል፡፡
የታማኝነት ዋጋ
የኤል ቻፖ የረዥም ጊዜ ሚስቱ የነበረችው ሉሴሮ ጓዳሉፔ ሳንቼዝ ሎፔዝ በፍርድ ወቅት መስክራበታለች። ሰኔ 2017 በአሜሪካ-ሜክሲኮ ድንበር አቅራቢያ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ክስ በቁጥጥር ስር ዋለች፡፡
ጥፋተኛ መሆኗን አምና የአሥር ዓመታት እስር ተከናነበች፡፡ የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሳንቼዝ ከዓቃቤ ሕግ ጋር በመተባበር የይግባኝ ጥያቄ አቅርባለች።
ሰማያዊ የእስር ቤት ልብስ ለብሳ ስለ ግንኙነታቸው እና የእፅ ዝውውር ሰንሰለት መሪ ስለመሆኑ ፍርድ ቤት ቀርባ ገልፃለች፡፡ በቅርበት የተቀመጠው ኤል ቻፖ ትዕግሥት ያጣ ይመስል ነበር። በተደጋጋሚም የግድግዳው ሰዓት ማየቱን ቀጠለ፡፡
ኤማ በሁለተኛው ረድፍ ላይ ተቀመጣ ነበር፡፡ ረዣዥም ጸጉሯን አስሬ በጣቶቿ ታበጥራለች። በዕለቱ ከባሏ ጋር ተመሳሳይ ጃኬት ለብሳ ነበር፡፡
የኤል ቻፖ ጠበቃ ሆነው ያገለገሉት ዊሊያም ፑርፑራ ተመሳሳዩ ጃኬት የትዳራቸውን ጥንካሬ ያሳያል ይላሉ፡፡ የቀድሞው ሚስቱ ስትመሰክርበት ኤማ ግን ተመሳሳይ ልብስ ለብሳ ለሳንቼዝ መልዕክት ለማስተላለፍ ፈለገች፡፡
"ለቀድሞ ሚስቱ 'የእኔ ነው' እያለች ነበር" ይላሉ ፑርፑራ፡፡
ከችሎቱ መልስ ሳንቼዝ ወደ ማረሚያ ቤት ክፍሏ ተመለሰች፡፡ ኤማ ደግሞ ለእራት ኒው ዮርክ ወደሚገኘው ቅንጡ ምግብ ቤት፡፡
የሁለቱ ሴቶች እጣ ፈንታ ሲቀያየር ብዙም ጊዜ አልፈጀ፡፡ ሳንቼዝ ነጸ ተብላ ከእስር ተለቃለች፡፡ ኤማ ደግሞ ማረሚያ ቤት ያለ ዋስትና መብት እንድትታሰር ተደርጓል፡፡
በችሎቱ ወቅት ኤማ የአኗኗር ዘይቤዋን ያሳየችበት መንገድ ብዙዎችን ያስደነገጠ ሲሆን ለባሏ ታማኝ በመሆኗም ቅር ተሰኝተዋል፡፡
የደኅንነት ተንታኙ ግራንድ ማይሰን "ሞኝ ሆና ታየች" ብለዋል፡፡
ይህን ግን ሳንቼዝ አልደገመችውም።
ኤማ እስር ቤት እንደሆነች ጠበቃዋ ሄዘር ሻነር ስትነግራት ሳንቼዝ በባለንጣዋ ችግር የመደሰት ምልክት አላሳየችም፡፡
ይልቁንም ጠበቃዋን ስታስታውስ "ሀዘን ተሰምቷት ስለነበረ 'ከልጆቿ ለመራቅ የተገደደች ሌላ እናት ናት' " ብላለች፡፡












