በግድያ ወንጀል ለ40 ዓመታት ሲፈለግ የነበረው አሜሪካዊ ተያዘ

የ65 ዓመቱ አዛውንት ዶናልድ ሳንቲኒ ካሊፎርኒያ ውስጥ ተይዞ ፍሎሪዳ ሲደርስ

የፎቶው ባለመብት, HILLSBOROUGH COUNTY SHERIFF’S OFFICE

የምስሉ መግለጫ, የ65 ዓመቱ አዛውንት ዶናልድ ሳንቲኒ ካሊፎርኒያ ውስጥ ተይዞ ፍሎሪዳ ሲደርስ

አሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ውስጥ ከዛሬ 40 ዓመት በፊት በተፈጸመ ግድያ ተጠርጥሮ በፖሊስ ሲፈለግ የቆየው ግለሰብ ለአስርታት ተሰውሮ ከቆየ በኋላ በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ግለሰቡ በአደገኛ ወንጀለኛነት ሦስት ጊዜ በአሜሪካ ውስጥ በፖሊስ “በጥብቅ ከሚፈለጉ” ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካቶ አርባ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሲታደን ቆይቷል።

የ65 ዓመቱ አዛውንት ዶናልድ ሳንቲኒ፣ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር አንዲት የ33 ዓመት ሴትን ገድሏል ተብሎ ተጠርጥሮ ነው ሲፈለግ የቆየው።

ለአርባ ዓመታት ያህል ከፖሊስ ተሰውሮ በቆየበት ጊዜም 13 ጊዜ ማንነቱን እየቀያየረ ከመያዝ ለማምለጥ ሙከራ ማድረጉን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ዶናልድ በተያዘበት ጊዜ በካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ የሚገኝ የውሃ ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ሆኖ በማገለግል ላይ ነበረ።

ተጠርጣሪው ካሊፎርኒያ ውስጥ ከተያዘ በኋላም በግድያ ወንጀል ድርጊት ወደ'ሚፈለግበት ፍሎሪዳ ግዛት ተላልፎ ተሰጥቷል።

ግለሰቡ ከባሏ ጋር በፍቺ ሂደት ላይ ከነበረችው ከ33 ዓመቷ ሲንቲያ ዉድ ግድያ ጋር በተያያዘ ነበር ሲፈለግ የቆየው። ግለሰቧ በመጨረሻ የታየችው እንደ አውሮፓውያኑ ሰኔ 06/1984 ግድያው በተፈጸመበት ዕለት ከተጠርጣሪው ጋር ነበር።

“የዶናልድ ሳንቲኒ መያዝ ለአራት አስርታት ለሚጠጋ ጊዜ በእንጥልጥል የቆየውን የግድያ ወንጀል መቋጫ እንዲያገኝ በማድረግ፣ ለሟቿ እና በሐዘን ውስጥ ለኖሩት ቤተሰቦቿ ፍትሕን የሚያስገኝ ነው” ሲሉ በፍሎሪዳ ሂልስቦሮ አካባቢ የፖሊስ ባለሥልጣን የሆኑት ቻድ ክሮኒስተር ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ተፈላጊው ግለሰብ ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ ነበር በተጠርጣሪነት ሲፈለግ የነበረው፤ ነገር ግን ወዲያውኑ መኖሪያውን ለቆ ወደ ሌላ ግዛት በመሄድ ለአርባ ዓመታት መደበቅ ችሎ እንደነበር ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ዶናልድ ሳንቲኒ በአውሮፓውያኑ በ1990፣ በ2005 እና በ2013 በአሜሪካ ውስጥ በጥብቅ የሚፈለግ ወንጀለኛ ተብሎ ለበርካታ ጊዜያት በቴሌቪዥን ቀርቦ ነበር።

ግለሰቡን ለመያዝም ግዙፉን የአሜሪካ የአገር ውስጥ የወንጀል ምርመራ ተቋምን ጨምሮ በርካታ አካላት ግለሰቡን ለማግኘት ለዓመታት ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

ፍለጋውን ያደርጉ የነበሩት መርማሪዎችም ወደ ቴክሳስ፣ ካሊፎርኒያ እና ከአሜሪካ ውጪም ታይላንድ ድረስ ቢጓዙም ሳይሳካላቸው ቆይቷል።

በመጨረሻም ፍሎሪዳ ውስጥ የሚገኝ ተፈላጊዎችን ከሚያድን አንድ ገብረ ኃይል በተገኘ ጥቆማ አማካይነት ነበር ተጠርጣሪው ሊያዝ የቻለው።

ሳንቲኒ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወደ ፍሎሪዳ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት ከተያዘ በኋላ ከ40 ዓመታት በፊት ፈጽሞታል ተብሎ በተጠረጠረበት ወንጀል የመጀመሪያ ደረጃ የግድያ ክስ ተመስርቶበታል።

ተጠርጣሪው በተያዘበት ጊዜ ሳንዲያጎ ውስጥ በምትገኝ ካምፖ ተብላ በምትጠራ አንዲት ትንሽ ከተማ ውስጥ ዌልማን ሲመንድስ በሚል መጠሪያ ተሸሽጎ ይኖር ነበር።

የአካባቢው ባለሥልጣናት እንዳሉት ግለሰቡ የአካባቢው የውሃ ቦርድ ሰብሳቢ በመሆኑ በመደበኝነት በስብሰባዎች ላይ ሲሳተፍ ቆይቷል።

ተጠርጣሪው ለአንድ የሳን ዲዬጎ የዜና ጣቢያ በእጁ ጽፎ በላከው ባለ16 ገጽ ደብዳቤ ላይ “ለረጅም ዓመታት ተሰውሮ የቆየው በፍቅር የተሞላ የተከበረ ሕይወት ለመኖር” ሲል መሆኑን ገልጿል።

ሲፈለግ በቆየባቸው ዓመታት ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት በሮታሪ ክለብ ውስጥ ማገለገሉን፣ የታይላንድ ባሕላዊ ምግብ ቤት መክፈቱን እና የመኖሪያ አፓርታማን ሲያስተዳድር መቆየቱን ገልጿል።

ግለሰቡ ከግድያው በፊት ጀርመን ውስጥ በነበረበት ጊዜ አንዲት ሴትን በመድፈሩ በእስር የተቀጣ ሲሆን፣ እንደ አውሮፓውያኑ በ1983 ደግሞ ቴክሳስ ግዛት ውስጥ በአንድ መደብር ላይ በተፈጸመ ዘረፋ ተከሶ ነበር።