4 ጨቅላ ልጆቿን ገድላለች የተባለች እናት ከ20 ዓመታት በኋላ ነጻ ወጣች

የፎቶው ባለመብት, EPA
አራት ጨቅላ ልጆቿን ገድላለች በሚል “የአውስትራሊያዋ አደገኛ ገዳይ” የሚል ስም ወጥቶላት የነበረችው እናት አዲስ ማስረጃ መገኘቱን ተከትሎ ከእስር ነጻ ወጣች።
ካትሊን ፎልቢግ የተባለችው እናት በአራት ልጆቿ ግድያ ጥፋተኛ ተብላ 20 ዓመታትን በእስር ካሳለፈች በኋላ ነው የልጆቹን አሟሟት በሚመለከት አዲስ መረጃ መገኘቱን ተከትሎ ከእስር ነጻ የወጣችው።
ሳይቲስቶች በቅርቡ ባካሄዱት ምርመራ ከ19 ቀን እስከ 19 ወራት እድሜ የነበራቸው ካሌብ፣ ፓትሪክ፣ ሳራ እና ሎውራ የተባሉት ልጆች የመሞታቸው መንስዔ ተፈጥሯዊ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን ሰጥተዋል።
ይህን ተከትሎ የ55 ዓመቷ እናት ያለ ጥፋቷ ወንጀለኛ ተብላ ሁለት አስርት ዓመታትን በእስር በማሳለፏ የአውስትራሊያ ትልቁ የፍትሕ እጦት ተደርጎ ተወስዷል።
ካትሊን ፎልቢግ ሁልግዜም ልጆቿን አለመግደሏን በመግለጽ ጥፋተኛ አለመሆኗን ስትከራከር ብትቆይም እአአ 2003 ላይ የዳኞች ስብስብ ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ አራት ልጆቿን ግድላለች በሚል 25 ዓመት በእስር እንድታሳለፍ ውሳኔ አስተላልፈው ነበር።
እነዚህ ጨቅላ ሕጻናት በእአአ 1989 እና 1999 መካከል ድንገት የሞቱ ሲሆን በወቅቱ ጉዳዩን የተመለከቱ መርማሪዎች ሕጻናቱ በእናቲቱ ታፍነው ተገድለዋል ከሚል ድምዳሜ ደርሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, FAIRFAX MEDIA/GETTY IMAGES
ከዚህ ቀደም ጥፋተኛ የተባለችው ካትሊን ፍሎቢግ ያቀረበቻቸው ይገባኝ እንዲሁም እአአ 2019 ላይ ጉዳዩ ዳግም ታይቶ የመጀመሪያው ውሳኔን የሚሽር ምንም ማስረጃ የለም ተብሎ ነበር።
ይሁን እንጂ በቅርቡ የተካሄደው ሳይንሳዊ ምርመራ የልጆቹን አሟሟት ተፈጥሯዊ ሊሆን እንደሚችል አሳይቷል።
መርማሪዎች ሕይወታቸው ያለፉ ሴቶች ልጆች ለድንገተኛ ተፈጥሯዊ ሞት ምክንያት ሊሆን የሚችል ጂን እንዳላቸው በምርመራ አረጋግጠዋል። ከዚህ በተጨማሪም የካትሊን ፍሎቢግ ወንድ ልጅ እንዲሁ ከድንገተኛ ሞት ጋር የሚቆራኝ ጂን እንዳለው ገልጸዋል።
የኒው ሳውዝ ዌልስ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጥፋተኛ የተባለችውን እናት ጉዳይ የመረመሩት ዳኛ እናቲቱ ጥፋተኛ በተባለችበት መንገድ ልጆቿን ስለመግደሏ የሚያመላክት ነገር አላገኙም ብሏል።
ይህን ተከትሎም ፍሎቢግ ሙሉ ይቅርታ እንዲደረግላት እና በእስቸኳይ ከእስር እንድትወጣት የኒው ሳውዝ ዌልስ ገዢ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።












