የብራዚል የቀድሞ ፕሬዚዳንት ቦልሶናሮ የቁም እስር ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀኝ አክራሪ የሆኑት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ በቁም እስር እንዲቆዩ አዘዘ።
የቀድሞ ፕሬዚዳንት መፈንቅለ መንግሥት አቀነባብረዋል በሚል ክስ ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም እርሳቸው ግን ክደው ተከራክረዋል።
የቦልሶናሮን የክስ መዝገብ እያዩ የሚገኙት ዳኛ አሌክሳንደር ዴ ሞራስ በቀድሞ ፕሬዚዳንቱ ላይ ውሳኔው ያሳለፉት ባለፈው ወር የተጣለባቸውን የእገዳ ትዕዛዞች ባለማክበራቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ቦልሶናሮ ከአውሮፓውያኑ 2019 እስከ 2022 ብራዚልን የመሩ ሲሆን፤ ተተኪያቸው ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ሥልጣን እንዳይረከቡ ለማድረግ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማድረግ ተከስሰዋል።
የቦልሶናሮ የሕግ ቡድን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ማንኛውንም የእገዳ ትዕዛዝ ጥሰዋል መባሉን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቁ መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ቢሮ በኤክስ ገፁ ላይ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ "ኮንኖ"፤ "ማዕቀብ የተጣለበትን ተግባር የሚደግፉትን እና የሚተባበሩትን ሁሉ ተጠያቂ እናደርጋለን" ብሏል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት፤ የቀድሞውን የብራዚል ፕሬዝዳንት ዣይር ቦልሶናሮ ላይ የሚካሄደውን ምርመራ በሚመሩት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አሌክሳንድር ዴ ሞሬስ ላይ ማዕቀብ ከመጣል ባሻገር፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በብራዚል ላይ 50 በመቶ ታሪፍ የሚጥል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።
በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው ዳኛው ሞራስ፣ ቦልሶናሮ ልጆቹን ጨምሮ የደጋፊዎቻቸውን ማኅበራዊ መረብ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እና በብራዚል የፍትህ አካላት ውስጥ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያበረታቱ መልዕክቶችን ለማሰራጨት ተጠቅመውበታል ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።
እሁድ ዕለት ቦልሶናሮ የሚደግፉ ሰልፎች በተለያዩ የብራዚል ከተሞች ተካሂደዋል።
ከልጆቹ መካከል አንዱ እና የምክርቤቱ አባሉ ፍላቪዮ፣ በሪዮ ዴ ጄኔሮ ለተሰበሰበው ሕዝብ የአባቱ ድምጽ ለአጭር ደቂቃ በስልኩ ስፒከር ላይ እንዲሰማ አድርጓል።
ፍላቪዮ በኋላ ላይ ደግሞ አባቱ ለደጋፊዎች መልዕክት ሲያስተላልፍ የሚያሳይ ቪዲዮ በድረ ገጽ ላይ ካተመ በኋላ አንስቶታል።
ዳኛ ሞራስ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከጠበቆቻቸው ወይም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ከተፈቀዱ ሰዎች በስተቀር ማንም እንዳይጎበኛቸው እና ሞባይል በቀጥታም ሆነ በሦስተኛ ወገን በኩል እንዳይጠቀሙ ከልክለዋል።
ከዚህ ቀደም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቦልሶናሮ ሊጠፉ ይችላሉ በሚል እግራቸው ላይ የሚታሰር መከታተያ እንዲደረግላቸው፣ የሰዓት እላፊ እንዲጣልባቸው፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ፣ እና የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጣልቃ እንዲገቡ የሚወተውተውን ልጃቸውን ኤድዋርዶ ቦልሶናሮን እንዳያነጋግሩ ትዕዝዝ ተላልፎ ነበር።
እነዚህ እገዳዎች የተጣሉት ዶናልድ ትራምፕ በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ እያበረታቱ ነው በሚል ከተወነጀሉ በኋላ ነው።
የፕሬዚዳንቱን ክስ ተከትሎ አሜሪካ በብራዚል ላይ የ50 በመቶ ታሪፍ የጣለች ሲሆን ይህም እንደ የብርቱካን ጭማቂ፣ የተወሰኑ የአውሮፕላን ክፍሎችን እና የኃይል ምርቶችን ያሉ በርካታ የአገሪቱ ዋነኛ የወጪ ንግድ ምርቶችን አላካተተም።
ይህ የትራምፕ ውሳኔ፤ ብራዚል "ቦልሶናሮ ላይ ከተመሰረተው ፖለቲካዊ ምክንያት ያለው ክስ፣ ማስፈራራት፣ ትንኮሳ፣ ሳንሱር እና ክስ" ጋር በቀጥታ እንደሚገናኝ ተገልጿል።
ብራዚል በበኩሏ በአሜሪካ በሚጣልባት ማንኛውንም ታሪፍ ልክ የአጸፋ ቀረጥ እንደምትጥል አስጠንቅቃለች።
አሜሪካ ከቻይና ቀጥሎ ሁለተኛዋ ትልቅ የብራዚል የንግድ አጋር በመሆኗ፤ የዋጋ ጭማሪው ደቡብ አሜሪካዊቷን አገር በእጅጉ ሊጎዳት ይችላል።
ብራዚል ለአሜሪካ 15ኛዋ ትልቅ የንግድ አጋር ነች። ብራዚል ከአሜሪካ የምታስገባቸው ዋና ዋና ምርቶች የማዕድን ነዳጆች፣ አውሮፕላኖች እና ማሽኖች ናቸው። አሜሪካ በበኩሏ ጋዝ እና ነዳጅ እንዲሁም አይረን እና ቡና ከብራዚል ታስገባለች።
ትራምፕ እና ቦልሶናሮ በተመሳሳይ ወቅት ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ጥሩ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን እአአ በ2019 በዋይት ሐውስ ተገናኝተዋል።
ባለፈው ወር ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ቦልሶናሮ "ምንም ጥፋት የለበትም" ሲሉ ድጋፋቸውን ገልፀው "አገሩን በእውነት የሚወድ ጠንካራ መሪ" ሲሉ አወድሰዋቸዋል።















