ዩናይትድ ኪንግደም የትግራይ ኃይሎች ከአማራ፣ የኤርትራ ደግሞ ከትግራይ እንዲወጡ ጠየቀች

የዩኬ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚንስትር ቪኪ ፎርድ

የፎቶው ባለመብት, gov.uk

የምስሉ መግለጫ, የዩኬ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚንስትር ቪኪ ፎርድ

እንደአዲስ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የትግራይ ኃይሎች በአስቸኳይ ተኩስ አቁመው ከአማራ ክልል እንዲሁም የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ክልል እንዲወጡጠየቀች።

የዩኬ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚንስትር ቪኪ ፎርድ 22 ወራት ላስቆጠረው ግጭት ጦርነት መፍትሄ ስላልሆነ ተፋላዊሚዎች ልዩነታቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት አለባቸው ሲሉ ጥሪ አቀርበዋል።

ሁለት ዓመት ሊደፍርን የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ጋብ ብሎ ከቆየ በኋላ ከአንድ ሳምንት በፊት እንደ አዲስ ተቀስቅሷል።

ጦርነቱ ዳግም ላገረሸበት ምክንያት የጦርነቱ ተፋላሚ ወገኖች አንዳቸው ሌላኛውን ተጠያቂ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ጦርነቱ መልሶ በመጀመር በጥቂት ቀናት ውስጥ የትግራይ ኃይሎች ቆቦ ከተማን ጨምሮ አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች ይዘዋል።

ቪኪ ፎርድ ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 26/2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፤ “የትግራይ ኃይሎች በአስቸኳይ ግጭት አቁመው አማራ ክልል በመውጣት ወደ ትግራይ መመለስ አለባቸው። የኤርትራ ኃይሎች ትግራይን መልቀቅ አለባቸው” ብለዋል።

ቪኪ ፎርድ ይህን መግለጫ ያወጡት የኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት በተጨማሪ ግንባሮች ተስፋፍቶ ስለመቀጠሉ የሚያመለክቱ መረጃዎች በወጡበት ወቅት ነው።

የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ ነሐሴ 26/2014 ዓ.ም. ማለዳ ላይ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሠራዊት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በኩል በአራት አቅጣጫዎች አዲስ ጥቃት እንደከፈቱ አስታውቀዋል።

የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት ዳግም ወደ ጦርነት መመለሳቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስከፊ ነው ያሉት ሚንስትሯ ቪኪ ፎርድ፤ በቀጥታ በጦርነት ምክንያት እና በጦርነት ምክንያት የሰብዓዊ ሥራዎች ተስጓጉለው በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ለሞት አደጋ ያጋልጣል ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩኬ የአፍሪካ ሚንስትሯ ቪኪ ፎርድ፤ “ጦርነቱ ከጀመረ 22 ወራት ተቆጥረዋል፤ ወታደራዊ እርምጃ መፍትሄ አለመሆኑ ግልጽ ነው” ብለዋል።

የግጭቱ ዳግም ማገርሸት በሰላም ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል ያሉት ቪኪ ፎርድ፤ ኅዳር 2014 ዓ.ም. ተደርሶ የነበረው የሰብዓዊነት የተኩስ አቁም እርምጃ ግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያገኝ እና የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ዳግም እንዲያንሰራራ እድል ፈጥሮ ነበር ብለዋል።

ይሁን እንጂ ግጭቱ እንደ አዲስ መጀመሩ “የሠላም መንገድን የበለጠ አስቸጋሪ ያደርገዋል” ብለዋል። ሚንስትሯ ተፋላሚ ወገኖች ለንግግር ቢቀመጡ ሰላም ሊመጣ እንደሚችል የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እምነት እንዳለው ገልጸዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ከ13 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ አድርጎት እንደነበረ ያስታወሱት ሚንስትሯ፤ ከቀናት በፊት የትግራይ ኃይሎች ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ነዳጅ በኃይል መውሰዳቸው በክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ ሥራን አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጦርነቱ በተጀመረበት ተመሳሳይ ዕለት ረፋድ ላይ የትግራይ ኃይሎች ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ መዝረፋቸውን መግለጹ ይታወሳል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊ ነዳጁ በኃይል መወሰዱን “አስደንጋጭ እና አሳፋሪ” በማለት ገልጸው ነዳጁ “አሁኑኑ” ይመለስ ሲሉ በአጽንኦት ጠይቀው ነበር።

ህወሓት በበኩሉ ለዓለም ምግብ ፕሮግራም “ያበደርኩትን ነዳጅ መልሼ ወስድኩ እንጂ ዘረፋ አልፈጸምኩም” ብሎ ነበር።

ለሦስተኛ ዙር የተጀመረው ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ ተፋላሚ ወገኖች የሰብዓዊ እርዳታ ያለ አንዳች ክልከላ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ቪኪ ፎርድ ጠይቀዋል።

ምንም እንኳ የዩኬ የአፍሪካ ሚንስትሯ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ቢጠይቁም፤ የጦርነቱ ዳግም ማገርሸትን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥት ወደ ትግራይ የሚያደርገውን የሰብዓዊ እርዳታ ማቋረጡን ከቀናት ገልጾ ነበር።

የመንግሥታቱ ድርጅት እጅግ አስፈላጊ ነው ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ ማጓጓዝ ያቆመው የሰሜን ኢትዮጽያ ጦርነት ዳግም ማገርሸቱን ተከትሎ መሆኑን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) እንዳለው፣ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ጀምሮ በየብስ ወደ ትግራይ ይገባ የነበረው ሰብዓዊ እርዳታ እንዲሁም ሰብዓዊ በረራዎች ተቋርጠዋል።

የሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ

የዩናይትድ ኪንግደም የአፍሪካ ጉዳዮች ሚንስትር ቪኪ ፎርድ በዚህ የእርስ በእርስ ጦርነት ሰላማዊ ሰዎች ዒላማ ከመሆን እንዲጠበቁ ተፋላሚ ወገኖቹን አሳስበዋል።

ሚንስትሯ ባለፉት ቀናት የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ባካሄዳቸው የአየር ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ስለመገደላቸው እና ሰዎች በማንነታቸውን መሠረት ለእስር እየተዳረጉ ስለመሆኑ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ ብለዋል።

“ተፋላሚ ወገኖች ለሰላማዊ ሰዎች ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት፣ ሰብዓዊ መብቶችን መጠበቅ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግጋቶችን ማክበር ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ኃላፊነት ነው” ብለዋል።

ቪኪ ፎርድ በዛሬው መግለጫቸው ጦርነቱን ማስቆም የሚቻለው ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠት ሲቻል ብቻ ነው ያሉ ሲሆን፤ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ለሚደረገው ድርድር መንግሥታቸው ድጋፍ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ጦርነቱን በድርድር ለማብቃት ለወራት ያደረገው ጥረት ተፋላሚቹን ወደ ጠረጴዛ ሊያመራ ይችላል ተብሎ ሲጠበቅ ነው አዲስ ዙር ጦርነት የተቀሰቀሰው።