ከወራት የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ጦርነቱ ለምን አገረሸ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሌክስ ደ ዋል* የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ
በፌደራል መንግሥቱ እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የሚካሄደው ጦርነት ከወራት የተኩስ አቁም በኋላ አገርሽቷል።
ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን በሰላም የሚቋጩበትና ወደ ድርድር የሚመለሱበት ሁኔታንም በተመለከተ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።
የፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ኃይሎች የሚስማሙበት ጉዳይ ቢኖር በትግራይ ደቡባዊ ድንበሮችና በአጎራባች የአማራ ክልል በምትገኘው ከተማ ቆቦ፣ ጦርነቱ የተነሳው ረቡዕ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ማለዳ መሆኑን ነው።
ሁለቱም አካላት የጦርነቱን ጅማሬ አስመልክቶ አንደኛው ወገን ሌላኛውን ይከሳል።
ከምዕራባውያን ዲፕሎማቶች በተገኘው መረጃ መሠረት ግልፅ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና አጋር ኃይል የሆነው ፋኖ በመባል የሚታወቀው የአማራ ሚሊሻን ጨምሮ ከፍተኛ ኃይል በባለፉት ሳምንታት ወደ ስፍራው እንደተላኩ ነው።
በትግራይ በኩል ህወሓት በጅምላ የወታደሮችን ምልመላ ማድረግና ያለውንም ሃብት ለሥልጠናና ለትጥቅ አውሎታል።
በተጨማሪም ባለፈው ዓመት በተደረገው ጦርነት ከፌደራል ሠራዊቱ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ በመማረክ ያከማቹ ሲሆን፣ በተጨማሪም ህወሓት አዳዲስ መሳሪያዎች ከውጭ እንደገዛም እየተነገረ ነው።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል ውጥረት ነግሶ ቆይቷል። ሆኖም ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሰላም ውይይቶች በቅርቡ ሊደረጉ እንደሚችሉ ብሩህ ተስፋ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮንን በሐምሌ ወር ሥራ የጀመረውን የሰላም ኮሚቴ እንዲመሩ ሥልጣን ሰጥተው ነበር።
ከዚያ በፊትም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከህወሓት ጋር በምስጢር እንዲገናኙ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ልከው ነበር ተብሏል።
በሲሸልስ እና በጂቡቲ በተደረጉ ውይይቶች የኢትዮጵያ ኃይል በትግራይ ላይ የጣለውን እገዳ እንዲያነሳ፣ ኤርትራም የኢትዮጵያ መንግሥትን ለመደገፍ የላከችውን ጦር ከትግራይ እንድታስወጣ እና ሁለቱም ወገኖች በፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አስተናጋጅነት በኬንያ መዲና ናይሮቢ ሙሉ ውይይት እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ የተደረሰ ይመስላል።
የመጀመሪያ አጀንዳቸውም ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ እንዲሆን ነበር።
ከትዕይንቱ በስተጀርባም አሜሪካ እነዚህን ውይይቶች በጥብቅ እየደገፈች ከኬንያም ጋር በትብብር እየሰራች ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ልዑካን የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለን ሐምሌ 26/2014 ዓ.ም. በጎበኙበት ወቅት “የመብራት፣ የቴሌኮሚዩኒኬሽን፣ የባንክ እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች በፍጥነት ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንዲመለሱ" እና "ያልተገደበ የሰብአዊ አቅርቦት" እንዲደርስ አፅንኦት ሰጥተው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም መሠረተ ልማትና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለመመለስ መስማማታቸውንም በዚሁ ወቅት ልዑካኑ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ሆኖም የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄኔራል ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ በትግራይ ላይ ስለተጣለው ከበባ ምንም ለማለት አልደፈሩም።
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ ለልዑካኑ አጭር መግለጫ በሰጡበት ወቅት ራሳቸውን እንደ ብቸኛ አደራዳሪ ከማቅረብ በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ አጋር የሆነችውን ኤርትራን ወደ ድርድሩ መድረክ ለመጋበዝ ሃሳብ በማቅረብ ግርምታን ጭረዋል።
ህወሓት መንግሥት የገባውን ቃል አላከበረም ሲል ይከሳል። የፌደራሉ መንግሥት በበኩሉ ውይይቶች መደረጋቸውን አላመነም። ዓለም አቀፍ ልዑካኑም ቢሆን ውይይቶቹ የተፋረሱበት ምክንያት በተመለከተ ዝምታን መርጠዋል።
በሐምሌ እና በነሐሴ ወራትም ቢሆን ለዘንድሮው ሰብል የሚውል ማዳበሪያና ጠብ ጠብ የሚል መድኃኒትና ምግብ ወደ ትግራይ ከመፈቀዱ በስተቀር የፌደራል መንግሥቱ መሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ የጣለውን እገዳ አላነሳም።
የዓለም ፕሮግራም ፕሮግራም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በትግራይ ሥራ እንዲጀምር ያስቻለውና አምስት ወራት ያስቆጠረው “የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስምምነት” ዓለም አቀፍ ሙገሳን ማግኘቱ በህወሓት በኩል አስደሳች ሆኖ አልተገኘም፥።
ህወሓት፣ የፌደራሉ መንግሥት እገዳውን ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም እና አናሳ የሆነ እርዳታ እየገባ እንደሆነ በመጥቀስ ይህም ባለበት ቀጥሏል ሲል አጥብቆ ይከራከራል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን መድረስ እንደቻለ ያስታወቀ ሲሆን፣ ነገር ግን እርዳታ የሚያስፈልገው 4.8 ሚሊዮን ሕዝብ አንጻር ሲታይ በእጅጉ ያነሰ ነው።
የህወሓት መሪ ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ግጭቱ ባገረሸበት ዋዜማ ለዓለም አቀፍ መሪዎች በፃፉት ግልፅ ደብዳቤ ላይ “ወደየትኛውም ብንዞር ሞትን የምንጋፈጥበት ደረጃ ላይ ወደምንደርስበት መንገድ በፍጥነት እየተቃረብን ነው። ያለን ብቸኛ አማራጭ በረሃብ መጥፋት ወይንም ለመብታችንና ለክብራችን እየታገልን መሞት ነው” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የጅምላ ረሃብ የትግራይ ተወላጆችን እየቀጠፋቸው ነው። ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ባይታወቅም ነገር ግን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በቤልጂየም የሚመራ የአካዳሚክ ቡድን ባደረገው ምርምራ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ጀምሮ በረሃብ እና በተያያዙ ምክንያቶች እስከ 500 ሺህ የትግራይ ተወላጆች መሞታቸውን ግምቱን አስቀምጧል።
'አርቴ' ከተሰኘው የፈረንሣይ የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋዜጠኞች በስተቀር ህወሓት አብዛኛውን የትግራይ ክልል በሰኔ ወር መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ የውጭ ዜና ማዕከላት ተገኝተው መዘገብ አልቻሉም።
እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ጥቂት የረድዔት ሠራተኞችም ቢሆኑ የህጻናትን ሞት በተመለከተ መሠረታዊ መረጃዎችን መሰብሰብ አልቻሉም። የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃለ አቀባይ ቢሆኑ “ረሃብ መኖሩን አለመኖሩን እኛ አናውቅም” ሲሉ በደፈናው ምላሽ ሰጥተዋል።
ያገረሸው ጦርነት በአጭር ጊዜ የሰብዓዊ ቀውሱን ያባብሰዋል። የተጀመሩ ውስን የእርዳታ አቅርቦት ሥራዎች በአሁኑ ወቅት ቆመዋል። የመጀመሪያዎቹ አነስተኛ ሰብሎች ከአንድ ወር በላይ መሰብሰብ አይችሉም እናም ውጊያው የበለጠ ውድመት ያስከትላል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባለፈው ሳምንት መቀለ ከተማ ውስጥ በመዋዕለ ህፃናት ላይ የአየር ጥቃት ያደረሰ ሲሆን፣ በዚህም ሦስት ህጻናትን ጨምሮ ሰባት ነዋሪዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ የህክምና ባልደረቦች ተናግዋል።
መንግሥት ይህንን ውድቅ በማድረግ የአየር ጥቃቱ በወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ ነው ብሏል። በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ምሽትም በመቀለ ከተማ ሁለተኛ የአየር ድብደባ መፈጸሙ ታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Tigray Tv/ Reuters
የትግራይ አመራሮች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም 12 የነዳጅ ታንከሮችን የወሰዱ ሲሆን ይህም በከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ባለሥልጣናት ከፍተኛ ውግዘት አስከትሎባቸዋል።
ህወሓት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነዳጅ በብድር ከወራት በፊት የወሰደውን እያስመለሰ እንደሆነ ምላሽ የሰጠ ሲሆን፣ ሁኔታውና ወቅቱ ቃለ አቀባዩ እንደሚሉት መደበኛ አገልግሎትን ለመስጠት እንዳልሆነ ይጠቁማል።
ሌላኛው ከሰሞኑ የተሰማው ጉዳይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ወደ ትግራይ የሚገባ ከሱዳን አየር ክልል የተነሳ የጦር መሳሪያ የጫነ አውሮፕላን መትቼ ጥያለሁ ብሏል። ህወሓት ሐሰት ነው በማለት ምላሽ ሰጥቷል።
በኤርትራ ውስጥ እንዲሁም ለትግራይ ድንበር ቅርብ በሆኑ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ የሠራዊት እንቅስቃሴ መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህ ሁሉ መካከል የኤርትራ መንግሥት እንደተለመደው ዝም ብሏል። በያዝነው ሳምንት ረቡዕ በምዕራብ ትግራይ ጦርነቱ መቀስቀሱ ሪፖርት ተደርጓል።
ጦርነቱ በመረጃዎች የጨለመ ቢሆንም በቆቦ የነበረው ጦርነት መጠነ ሰፊ እንደሆነ ዜናዎች እየወጡ ነው። የትግራይ ምንጮች እንደዘገቡት ከፍተኛ ቁጥር ባለው በ20 ክፍለ ጦር ላይ ከፍተኛ ድል መቀዳጀታቸውንና በዚህም ከፍተኛ የጦር መሳሪያ መማረካቸውን ተናግረዋል። ለዚህ ግን ምንም ገለልተኛ ማረጋገጫ የለም።
የኢትዮጵያ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን “በቀውስ ወቅት የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በሚያንጸባርቅ መልኩ ዘገባቸውንና መረጃቸውን በጥንቃቄ እንዲከታተሉ” ከማለት ውጪ ምንም አላለም።
መንግሥት የመከላከያ ኃይል ቆቦን ለቆ መውጣቱን የገለጸ ሲሆን፣ በደቡብ በኩል 50 ርቀት ላይ በምትገኘው ወልዲያ ከተማ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ሠራዊቱ በዚያ አካባቢም አይታይም።
ባለፈው ዓመት ከመዲናዋ አዲስ አበባ በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የደረሱበትን ግስጋሴ ለመድገም ምንም ፍላጎት የለንም ያሉት የትግራይ ኃይሎች ሠራዊታቸውን ወደ ደቡብ በኩል እያንቀሳቀሱ አይደለም። እንዲያውም የህወሓት ቃለ አቀባይ ወልዲያን ተቆጣጥረዋል የሚሉ ዘገባዎችን አስተባብለዋል።
ህወሓት የያዘው አቋም አስቸኳይ የሰላም ድርድር እንደሚፈልግ ነው። በደቡብ እና በምዕራብ ኢትዮጵያ ከፌደራሉ ጦር ጋር ከፍተኛ ጦርነት ላይ ካለው ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር መደበኛ ጥምረት ቢፈጥሩም ህወሓት አገሪቱን ማስተዳዳር የሚችል ግንባር/ጥምረት የለውም።
በአሁኑ ወቅት ያለው አብዛኛው የትግራይ ተወላጆች ስሜትም ለክልላቸው ብቻ መታገል የሚለው ነው።
በአደራዳሪነት ከተሾሙ አንድ ዓመት ያለፋቸው ጄኔራል ኦባሳንጆ ምንም አይነት ለውጥ ባለማምጣታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ ቢኖራቸውም አንዳንድ የአፍሪካ እና ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ያላቸው እምነት ተሸርሽሯል።
እስካሁን ድረስ ተዓማኒነት ያለው የሰላም ሂደትም አልተጀመረም።
በተጨማሪም በአሜሪካ እና ኬንያ የተጀመረው የሰላም ሂደትም ኡሁሩ ኬንያታ ያጯቸው ራይላ ኦዲንጋ ሳይሆኑ ዊሊያም ሩቶ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ማሸነፋቸውም ሳንካ ገጥሞታል።
የሰላም እቅዱ የተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የግል ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ነበር። ከዚህም ጋር ተያይዞ ዊሊያም ሩቶ የሰላም ድርድሩን እንዲመሩ ኡሁሩ ኬንያታን ሊመርጡ የሚችሉ ቢሆንም፣ ይህ ከመሆኑ በፊት በኬንያ ፖለቲካ ውስጥ ብዙ እርግጠኛ ያልሆኑ ጉዳዮች አሉ።
አሜሪካውያኖቹም ሌላ አማራጭ ዕቅድ ያላቸው አይመስሉም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ተፋላሚ ወገኖች “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” ወደ ውይይቱ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ሆኖም ሁለቱም ወገኖች ንግግራቸውን ሰምተው ተግባራዊ የሚያደርጉ አይመስሉም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጦር ሜዳ የገጠማቸውን ሽንፈትን ተከትሎ በመደራደር ደካማ ለመምሰል አይፈልጉም። አዲስ አበባ ህወሓትን “አሸባሪዎች” በማለት ወደሚያወግዘው ቋንቋ ተመልሳለች።
ህወሓት ለማንኛውም ድርድር እንደ ቅድመ ሁኔታ በጦር ወንጀልነት የሚቆጥረው በትግራይ የተጣለው ከበባ እንዲነሳ አጥብቆ ይጠይቃል።
በተጨማሪም የፌደራል መንግሥቱ ቀደም ሲል የገባውን ቃሎች ለማጠፍ እንደፈለገው ነጻነት መሰጠት የለበትም ይላል።
ጦርነቱ ማገርሸቱን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት የደረሰው ስቃይ እና ሞት ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያውቀውን ነገር አረጋግጦለታል። ይህም በትግራይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ወታደራዊ መፍትሄ እንደሌለው ነው።
*****
*የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አሌክስ ደ ዋል በአሜሪካው ተፍትስ ዩኒቨርስቲ በሚገኘው የፍሌቸር የሕግ እና ዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት ውስጥ የወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ናቸው። ኢትዮጵያን እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ አገራትን የሚዳስሱ የትንተና ጽሑፎቻቸው ያዘጋጃሉ።












