በመቀለው የአየር ጥቃት ሆስፒታል ኢላማ ተደርጓል ሲሉ የትግራይ ኃይሎች ከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሰሜን ኢትዮጵያ የምትገኘውን የትግራይ ክልልን የሚቆጣጠሩት የህወሓት አመራሮች መንግሥት በመቀለ ከተማ ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን የአየር ጥቃት ፈጽሟል ሲሉ ከሰሱ።
ከትግራይ ኃይሎች ለቀረበው ለዚህ ክስ የኢትዮጵያ መንግሥት አስካሁን የሰጠው ምላሽ ባይኖርም፣ ባለፈው ሳምንት የክልሉ ነዋሪዎች ከወታደራዊ ኢላማዎች እንዲርቁ አስጠንቅቆ ነበር።
የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ማክሰኞ ሌሊት ተፈጽሟል ስለተባለው የአየር ጥቃት በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳስፈሩት፣ ቢያነስ ሦስት ቦምቦች በከተማዋ ላይ መጣላቸውን ጠቅሰዋል። ጨምረውም ከጥቃቱ ኢላማዎች መካከል በመቀለ ያለ ሆስፒታል አንዱ ነው ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመቀለ ከተማ ነዋሪዎች አየር ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጠው፣ የጥቃቱ ኢላማዎች ምን እንደሆኑ ግን እንደማያውቁ ገልጸዋል።
የትግራይ የውጭ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአየር ጥቃቱ ከመቀለ ሆስፒታል አቅራቢያ መፈጸሙንና በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
“ጥቃቱ በሆስፒታል አቅራቢያ ደርሷል። እዚያም ወታደራዊ ኢላማ የለም። በዚህም ሰዎች ቆስለዋል ንብረትም ተጎድቷል” ብለዋል።
ፕሮፌሰር ክንደያ ጨምረውም በአየር ጥቃቱ የተፈናቃዮች ጣቢያ ላይ ቦምብ መጣሉን ገልጸዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በክልሉ ውስጥ ያለው የመገናኛ መስመሮች መቋረጥ ተፈጸመ ስለተባለው የአየር ጥቃት ዝርዝር እና አስተማማኝ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ አድርጎታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለአምስት ወራት የቆየውን የተኩስ አቁም ያፈረሰው ጦርነት የዛሬ ሳምንት ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. መጀመሩን ተከትሎ ጦርነት እየተካሄደ ነው።
በዚህም በመንግሥት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ተባብሶ መቀጠሉን በሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳለው እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው በዚህ ጦርነት ከትግራይ ጋር በሚዋሰኑት የአማራ እና የአፋር ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዲፈናቀሉ አድርጓል።
ማክሰኞ እኩለ ሌሊት ገደማ በመቀለ ከተማ ላይ ተፈጽሟል የተባለው የአየር ጥቃት በመንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከል ወታደረዊ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የተፈጸመ ሁለተኛው ጥቃት ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ሳምንት በመቀለ ከተማ ላይ በተፈጸመው የአየር ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
ከጦርነቱ ማገርሸት በኋላ የመጀመሪያው የአየር ጥቃት መቀለ የተፈጸመው ነሐሴ 20/2014 ዓ.ም. የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ጥቃት ቢያንስ 7 ሰዎች መገደላቸውን እና ከእነዚህም መካከል 3ቱ ሕጻናት መሆናቸውን ኤኤፍፒ እና ሮይተርስ የዜና ወኪል የጤና ባለሥልጣናት ዋቢ አድርገው ዘግበው ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል በጥቃቱ “በርካታ ሕጻናትን” ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል በማለት የፌደራሉን መንግሥት እርምጃ አጥብቀው ኮንነዋል።
የትግራይ ክልል ኃይሎችም መንግሥት ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ አድርጓል ሲሉ፣ የፌደራል መንግሥቱ ግን ሰላማዊ ሰዎችን ሳይሆን ወታደራዊ ኢላማዎች ዒላማ እንደሆኑ ገልጿል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል መባሉን “ሐሰት እና የፈጠራ ድራማ ነው” በማለት ማጣጣላቸው ይታወሳል።












