5 ቀናት ባስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተከሰቱ 5 ዋነኛ ክስተቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሁለት ዓመት ሊሆነው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ጋብ ብሎ ከቆየ በኋላ ባለፈው ሳምንት እንደ አዲስ ተቀስቅሷል።
ጦርነቱ ረቡዕ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ንጋት ላይ እንደ አዲስ መቀስቀሱ በአገሪቱ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋትን አጭሯል።
ጦርነቱ ከአምስት ቀናት በፊት ካገረሸ በኋላ የተከሰቱ አምስት ዋና ክስተቶችን እንመልከት።
1. ጦርነቱ እንደ አዲስ መቀስቀስ
ለወራት ከዘለቀ ውጥረት በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት ለሦስተኛ ዙር ዳግም መቀስቀሱ የተሰማው የትግራይ ኃይሎች በፌደራል መንግሥት እና በክልል ኃይሎች ጥምር ጥቃት ተከፍቶብኛል ካለ በኋላ ነው።
“የትግራይ ሠራዊት ወታድራዊ ኮማንድ” ባወጠው መግለጫ ረቡዕ፣ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ንጋት 11 ሰዓት ላይ የፌደራል መንግሥቱ ከአማራ ኃይሎች ጋር በመሆን መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍተውብኛል ብሎ ነበር።
የትግራይ ኃይሎች መግለጫን ተከትሎ የፌደራሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ደግሞ ጦርነቱን የጀመረው ህወሓት ነው በማለት የትግራይ ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጓል።
ሁለቱ ኃይሎች ወደ ጦርነት ተመልሰው መግባታቸውን ተከትሎ ተፋላሚ ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች ተቋማት እና አገራት ጥሪ አቅርበዋል።

2. የነዳጅ ስርቆት
ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ የብዙዎችን ቀልብ ስቦ የነበረው ጉዳይ የትግራይ ኃይሎች በመቀለ ከሚገኝ የመንግሥታቱ ድርጅት ቅጥር ግቢ ነዳጅ ሰርቀዋል መባሉ ነው።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጦርነቱ በተጀመረበት ተመሳሳይ ዕለት ረፋድ ላይ የትግራይ ኃይሎች ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ መዝረፋቸውን ግልጾ ነበር።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊ ነዳጁ በኃይል መወሰዱን “አስደንጋጭ እና አሳፋሪ” በማለት ገልጸው ነዳጁ “አሁኑኑ” ይመለስ ሲሉ በአጽንኦት ጠይቀው ነበር።
የፌደራሉ መንግሥት በበኩሉ ሐሙስ ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “ዝርፊያው የጦር ወንጀል ነው” ካለ በኋላ፣ የትግራይ ኃይሎች ነዳጁን መውሰድ ያስፈለጋቸው በቆቦና በአካባቢው ላይ ለተከፈተው ጥቃት ማስፈጸሚያ ለማዋል ነው ብሏል።
ይህ ተሰርቋል የተባለው ነዳጅን በተመለከተ ህወሓት ባወጣው መግለጫ ከወራት በፊት ለዓለም ምግብ ፕሮግራም ያበደርኩትን ነዳጅ መልሼ ወስድኩ እንጂ ዘረፋ አልፈጸምኩም ብሏል።
የትግራይ ኃይሎች በመግለጫቸው ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊን እና የዓለም ምግብ ፕሮግራምን አጥብቀው ተችተው፤ “በነበረን ስምምነት መሠረት ለዓለም ምግብ ፕሮግራም ያበደርነውን ከ600 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተመላሽ እንዲሆን ነው የጠየቅነው” ብለዋል።
3. የአውሮፕላን ተመትቶ መውደቅ
ለትግራይ ኃይሎች የጦር መሳሪያ ሊያደርስ የነበረ ነው የተባለ የጦር አውሮፕላን ተመትቶ ወድቋል መባሉ ሌላኛው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።
የአገሪቱ መከላከያ ኃይል አንቶኖቭ 26 የተባለው ሶቪዬት ሰራሽ የጦር አውሮፕላን ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም. ምሽት አራት ሰዓት በሱዳን በኩል የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሶ ሊገባ ሲል ተመትቶ መውደቁን ገልጿል።
ይህ አውሮፕላን ተመትቶ መውደቅን በተመለከተ ሱዳን እና የትግራይ ኃይሎች ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል።
አውሮፕላኑ ለህወሓት ኃይሎች የጦር መሳሪያ ሊያቀብል የነበረ እንደሆነ በአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ለልጸዋል።
ጄነራል ተስፋዬ፣ አውሮፕላኑ “ሌሊት አራት ሰዓት” ላይ በአገሪቱ አየር ኃይል ተመትቶ መውደቁን ከገለጹ በኋላ፣ የአየር ኃይል አዛዥ ሌተናንት ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ስለሁኔታው በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, ENDF/FB
4. የአየር ድበደባ በመቀለ
የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ መዲና መቀለ ነሐሴ 20/2014 ዓ.ም የአየር ጥቃት መፈጸሙና ሕጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል መባሉ ሌላኛው ትልቁ ክስተት ሆኖ አልፏል።
በዚህ ጥቃት ቢያንስ 7 ሰዎች መገደላቸውን እና ከእነዚህም መካከል 3ቱ ሕጻናት መሆናቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (ኤኤፍፒ) እና ሮይተርስ የዜና ወኪል የጤና ባለሥልጣናት ዋቢ አድርገው ዘግበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል በጥቃቱ “በርካታ ሕጻናትን” ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል በማለት የፌደራሉን መንግሥት እርምጃ አጥብቀው ኮንነዋል።
ከጥቃቱ በኋላ የተቀረጹ ናቸው የተባሉ ስሜትን የሚረብሹ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተጋርተዋል።
የትግራይ ክልል ኃይሎችም የፌደራል መንግሥቱ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ አድርገዋል ብለው የከሰሱ ሲሆን፣ የፌደራል መንግሥቱ በበኩሉ ሰላማዊ ሰዎች ዒላማ ተደርጓል መባሉ “ሐሰት” ብሏል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ ጥቃቱ “ሐሰት እና የፈጠራ ድራማ ነው” ካሉ በኋላ፤ የትግራይ ባለሥልጣናት የተጎዱ ሰዎችን በማስመሰል “አስከሬን መያዣ ቦርሳዎችን ጥለው እያሳዩ ነው” ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
5. የቆቦ በትግራይ ኃይሎች እጅ መግባቷ
ጦርነቱ ዳግም ባገረሸበት በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ የምትገኘው ቆቦ ከተማ በትግራይ ኃይሎች እጅ መግባቷ የተሰማው ቅዳሜ ነሐሴ 21/2014 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ነበር።
የቆቦ ከተማ በትግራይ ኃይሎች እጅ መውደቋን የታወቀው አገር መከላከያ ሠራዊት ከተማዋን ለቅቆ መውጣቱን የፌደራሉ መንግሥት ካስታወቀ በኋላ ነው።
የመንግሥት ኮሙኑኬሽን ጽህፈት ቤት መግለጫ ህወሓት የቆቦ ከተማን ከውጪ “በብዙ አቅጣጫ” እያጠቃ እንደሆነ ገልጾ “የሕዝቡን ደኅንነት አደጋ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ የከተማ ውስጥ ውጊያ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል” ብሏል።
የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው ከተማዋን የያዙት “በፀረ ማጥቃት ዘመቻ” መሆኑን አስታውቀዋል።
የትግራይ ኃይሎች ከተማዋን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የቆቦን ከተማ ለቅቆ መውጣቱ ተገልጿል።
አሁንም በቆቦ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች በመንግሥት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ከባድ ውጊያ እየተደረገ መሆኑን ከአካባቢው የወጡ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።












