ተመድ፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ ያገረሸው ጦርነት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለአምስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው የኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደገና መቀስቀሱ እንዳሳሰባቸውና ተፋላሚ ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ ጥሪ አቀረቡ።
ሁለት አመት የተጠጋው ደም አፋሳሽ ጦርነት መቀስቀሱ እንዳስደነገጣቸው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በትናንትናው ዕለት ነሐሴ 18፣ 2014 ዓ.ም ገልጸዋል።
በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ አመራሮች መካከል ተደርሶ የነበረው የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሶ በትናንትናው ዕለት የተጀመረው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።
“በኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት የመቀስቀሱን ዜና ስሰማ በጣም ደንግጫለሁ፤ እንዲሁም አዝኛለሁ” ያሉት ዋና ጸሐፊው ተፋላሚ ወገኖችም ጦርነቱን በሰላም እንዲቋጩት ጥሪ አቅርበዋል።
“በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የተጀመረው የሰላም ድርድር እንዲቀል ጥሪዬን አቀርባለሁ። በተጨማሪም ለተቸገሩ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታ የሚደርስበት ዋስትና እንዲመቻችና የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችና አገልግሎቶች እንዲመለሱ እጠይቃለሁ” ብለዋል ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ በትናንትናው ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት።
“ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድሩ ተመለሱ” የአፍሪካ ኅብረት
ተመድ ብቻ ሳይሆን፣ የጦርነቱ እንደገና መቀስቀስ እንዳሳሳበው የኢትዮጵያ መንግሥትንና የትግራይ ክልልን ለማደራደር ጥረት እያደረገ መሆኑን ሲያስታውቅ የነበረው የአፍሪካ ኅብረትም አስታውቋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በትናንትናው ዕለት ነሐሴ 18፣ 2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ ወታደራዊ ግጭቱን አስመልክቶ በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነ ገልጸው፣ ጦርነቱ እንዲቆም እንዲሁም ተፋላሚ ወገኖች ሰላማዊ መፍትሄን በመሻት ወደ ድርድሩ እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
ሊቀ መንበሩ የአገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ የጋራ ስምምነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሂደትን ለመደገፍ ከተፋላሚ ወገኖች ጋር አብሮ ለመሥራት የአፍሪካ ኅብረት ቁርጠኛ ነው በማለት አቋሙን አስታውቀዋል።
ለዚህም ሁለቱ አካላት ከአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይና ከቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባንጆ ጋር እንዲገናኙ ሙሳ ፋኪ ጥሪ አቅርበዋል።
“ወቅቱ ለሰላም ውይይት የሚደረግበት ጊዜ ነው” የአውሮፓ ኅብረት
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ እና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ያገረሸው ግጭት የሰላም ተስፋ ላይ ጥላ ጥሏል በማለት በትናንትናው ዕለት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
ጆሴፍ ቦሬል ለኢትዮጵያ መንግሥትና ለትግራይ አመራሮችም ሁኔታው ይበልጥ ከመባባሱ በፊት ግጭቱን እንዲቀለብሱት ጠይቀዋል።
“ወቅቱ ለሰላም ውይይት የሚደረግበት ጊዜ ነው” ብለዋል።
“የሰዎችን መጠነ ሰፊ ስቃይ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ እና ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ያስከትላል” አሜሪካ
አሜሪካም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በኩል የተቀሰቀሰው ግጭት ስጋት እንዳጫረባት ገልጻለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እና በመጨረሻም ግጭቱን በዘላቂነት ለማስቆም ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፉት አምስት ወራት በኢትዮጵያ መንግሥት የታወጀው እና ህወሓት የተቀበለው የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ግጭቱን በመቀነስ በትግራይ፣ በአፋር እና አማራ ክልሎች ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ መንገዱን እንዳበጀም በትናንትናው ዕለት በወጣው መግለጫ ተጠቅሷል።
ላለፉት አምስት ወራት የነበረው የተኩስ አቁም የበርካቶችን ሕይወት መታደጉን እንዲሁም እርዳታ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች እንዲደርስ ማስቻሉንም አንቶኒ ብሊንከን ጠቅሰዋል።
በቅርብ ጊዜ የተቀሰቀው ጦርነት፣ ትንኮሳ የተሞላባቸው ትርክቶችና እንዲሁም ዘላቂ የተኩስ አቁም እጦት እየታዬ የነበረውን መሻሻል አደጋ ውስጥ መክተቱንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ለጋራ ደኅንነት እና ለመላው ኢትዮጵያውያን ብልጽግናና እድገት ለማምጣት ሁሉንም ያሳተፈ የፖለቲካ ሂደት እንዲፈጠር የሚደረገውን ጥረት እንደሚያዘገየውም ነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጠቀሰው።
እንደገና ወደ ጦርነት መግባት የኢትዮጵያን ሰላም እና ደኅንነት ለማደፍረስ በሚጥሩት ላይ ሚና እንደሚጫወት አንቶኒ ብሊንከን ጠቅሰው፣ የሰዎችን መጠነ ሰፊ ስቃይ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ እና ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ያስከትላል ብለዋል።
አንቶኒ ብሊንከን በዚህ መግለጫቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ተደራዳሪ ቡድን ማቋቋሙን እና ለሰላም ውይይት ያለውን ፍላጎት መግለጹን መገንዘባቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም ወቅት ሁሉም ወገኖች የሰብአዊ እርዳታ ምግብ እና የነዳጅ አቅርቦትን እንዲያስቀጥሉ፣ ከወታደራዊ ኃይል እንዲታቀቡ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
“አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ እንዲሁም ለአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ቁርጠኛ አቋም አላት። አገሪቷ ያጋጠሟትን ሁለንተናዊ ተግዳሮቶች ታሪካዊ ድርቅን ማሸነፍ እና ክልላዊ ደኅንነትን ማስፈንን ጨምሮ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነን" ብሏል መግለጫው።
የፌደራል መንግሥቱና የትግራይ አመራሮች ሰብአዊ የተኩስ አቁም አዋጅ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ጦርነት ጋብ ብሎ የውይይትና የድርድር ሁኔታዎች ለወራት ያህል ሲነገሩ ቆይተዋል።
ነገር ግን ከሰሞኑ ይህ ሁኔታ ተቀይሮ በትናንትናው ዕለት በአማራ እና ትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጦርነት መቀስቀሱ ተነግሯል።
ሁለቱም አካላት የጦርነቱን ጀማሪ በተመለከተ አንዳቸው ሌላኛውን በመግለጫቸው ተጠያቂ አድርገዋል።
የትግራይ ሠራዊት ወታደራዊ ኮማንድ ነሐሴ 18፣ 2014 ዓ.ም ንጋት 11 ሰዓት ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በፌደራል መንግሥቱ እና በአማራ ኃይሎች ጥምር ኃይል ተከፍቷል በሚል መግለጫ አውጥቷል።
ከሰዓታት በኋላ የፌደራል መንግሥት ኮሚኒኬሽን በበኩሉ ጥቃት የከፈተው ህወሓት ነው ያለ ሲሆን “ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ንጋት ላይ በምሥራቅ ግንባር በቢሶበር፣ በዞብል እና በተኩለሽ አቅጣጫዎች ከለሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ጥቃት ፈጽሟል” ብሏል።
አሁን ከተከሰተው ግጭት በፊት የትግራይ ኃይሎች ነሐሴ 11፣ 2014 ዓ.ም የመከላከያ ሠራዊት በምዕራብ ትግራይ በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጥቃት ፈፅሟል በሚል ከሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል መባሉ ሐሰት ነው በማለት ምላሽ ሰጥቷል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት የአስር ሺዎችን ሕይወት በመቅጠፍ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ አድርሷል።
በሁለቱም ወገኖች በኩል የሰብአዊ ተኩስ አቁም አዋጅ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ጦርነቱ ጋብ ቢልም በትግራይ ያለው የምግብና ነዳጅ ዕጥረት እንዲሁም ስልክ፣ ውሃ፣ መብራት፣ ባንክ የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች ተቋርጠው መቀጠላቸው ሕዝቡን ለፈተና እንዳረጉት የረድዔት ድርጅቶች ይገልጻሉ።
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የእርስ በእርስ ጦርነት በድርድር ለመቋጨት የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል።
ሁለቱም ወገኖች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውና ተደራዳሪ ኮሚቴም አዋቅረናል ቢሉም በአሁኑ ወቅት ጦርነት እንደ አዲስ መቀስቀሱ የሰላም ሂደቱን አደጋ ላይ ጥሎታል።












