በትግራይ እና በአማራ አዋሳኝ አካባቢ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ ነዋሪዎች ተናገሩ

የቆቦ ካርታ

በአንዳንድ የትግራይ እና የአማራ ክልሎች አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች ላይ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ውስጥ በሚገኙና ከትግራይ ክልል ጋር ተዋሳኝ በሆኑ የራያ አላማጣ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ከዛሬ ንጋት ጀምሮ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያናገራቸው በአቅራቢያ የሚኖሩ ሦስት ሰዎች እንዳሉት ቀደም ካሉት ቀናት በተለየ የከባድ መሳሪያ ድምጽ መስማታቸውን፣ ነገር ግን ከየትኛው ወገን እንደሆነ እንዳላወቁ አመልክተዋል።

በተለይም የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች በሚዋሰኑበት ምሥራቃዊ ክፍል፣ ልዩ ስሙ ሰሌን ውሃ በተባለው ስፍራ አካባቢ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በአንጻሩ ከቆቦ ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኙት ዋጃን ጨምሮ በሌሎችም ተዋሳኝ አካባቢዎች ግን የተለየ የሠራዊት እንቅስቃሴ እና የተኩስ ድምጽ አለመስማታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በተመሳሳይም አንድ የቆቦ አካባቢ ነዋሪ “ከዛሬ (ረቡዕ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም.) ንጋት ጀምሮ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ድምጽ እየሰማሁ ነው” ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ነዋሪው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአካባቢው የሠራዊት እንቅስቃሴ እንደነበረ እንደተናገሩ ሮይተርስ ዘግቧል።

“ባለፈው ሳምንት የአማራ ልዩ ኃይል እና ፋኖ በአውቶብስ ተጭነው ወደ ግንባር ሲሄዱ አይቻለሁ” ማለታቸውን ሮይተርስ ስማቸውን ያልጠቀሳቸው ነዋሪ ተናግረዋል።

የትግራይ ኃይሎች ዛሬ ማለዳ ንጋት 11 ሰዓት አካባቢ መንግሥቱ ከአማራ ክልል ኃይሎች ጋር በመሆን “መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍተውብናል” በማለት በክልሉ ቴሌቪዥን ላይ አሳውቋል።

በህወሓት ስለቀረበው ክስ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከሌላ ገለልተኛ ወገን እስካሁን የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ ከቀናት በፊት የፌደራል መንግሥቱ “ህወሓት የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ነው” ብሎ መክሰሱ ይታወሳል።

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) እንዲሁም የመሥሪያ ቤቱ ሚኒስትር ዴዔታዎች ሰማላዊት ካሳ እና ከበደ ዴሲሳ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልክ ስላልተነሳ መልስ አላገኘንም።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ ጠዋት ላይ በትዊተር ገጻቸው “ከሳምንት ትንኮሳ በኋላ የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአማራ ሚሊሻ እና የወሎ ፋኖ እንዲሁም [የመከላከያ] 6ኛ ኮማንድ ጥቃት ከፍተዋል” ብለዋል።

የትግራይ ኃይሎች በመግለጫቸው ጥቃቱ ተከፈተብን ያሉት ጮቢ በር፣ ጃኖራ እና ጉባጋላ ተብለው በሚጠሩ ሦስት አቅጣጫዎች መሆኑን ተናግረዋል።

አካባቢዎች የት ይገኛሉ?

የትግራይ ኃይሎች ጥቃቱ ተከፍቶብናል ያሏቸው አካባቢዎች ጮቢ በር፣ ጃኖራ እና ጉባጋላ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር ላይ ይገኛሉ።

እነዚህ ሦስት ቦታዎች በትግራይ ክልል ራያ አላማጣ ወረዳ እና በአማራ ክልል ራያ ቆቦ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

ጮቢ በር በአማራ ክልል ራያ ቆቦ ወረዳ ውስጥ፣ ከሰሜን የአገሪቱ ክፍል ወደ መሃል አገር በሚወስደው ኤ2 አውራ መንገድ ላይ ይገኛል።

ጃኖራ በተመሳሳይ በራያ ቆቦ ወረዳ ከጮቢ በር በምዕራብ አቅጣጫ ያለ ቀበሌ ነው።

ጉባጋላ በተቃራኒው ከጮቢ በር በስተምስራቅ በትግራይ ራያ አላማጣ የሚገኝ ቀበሌ ነው። እነዚህ ሦስት ቀበሌዎች በትግራይ አላማጣ እንዲሁም በአማራ ቆቦ ከተሞች ይዋሰናሉ።

ባለፉት ሳምንታት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፉት ሳምንታት የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ አመራሮች ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን ጦርነት በድርድር ለመቋጨት ፍላጎት እንዳላቸውና ለዚህም እየተዘጋጁ መሆናቸው ሲነገር ቆይቷል።

ነገር ግን አንደኛው ወገን ሌላኛውን ለጦርነት እየተዘጋጀ ነው በሚል ሲካሰሱ የቆዩ ሲሆን፣ ህወሓት ባለፈው ሳምንት የመንግሥት ኃይሎች የከባድ መሳሪያ ጥቃት ፈጽመውብኛል ሲል ከሶ፣ ለወራት የቆየው የሰብአዊ እርዳታ ተኩስ አቁም መጣሱን አመልክቶ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ተፈጸመ የተባለው ጥቃት ሐሰት መሆኑን በማስተባበል፣ ህወሓት ሊካሄድ ከታሰበው የሰላም ንግግር ለማፈንገጥ ሰበብ እያቀረበ ነው ሲል ከሶ ነበር።

በጥምት ወር ማብቂያ 2013 ዓ.ም. ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው የእርስ በርስ ጦርነት ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ማስከተሉ ይታወቃል።

ከስድስት ወራት በላይ አልፎ አልፎ ከሚከሰቱ ግጭቶች ባሻገር በህወሓት ኃይሎች እና በኢትዮጵያ ሠራዊት መካከል ይህ ነው የሚባል ከባድ ጦርነት ሳይካሄድ ቆይቷል። ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ ወገኖች ሁለቱ ኃይሎች ጦርነቱን በሰላማዊ ንግግር እንዲቋጩ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የአፍሪካኅብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እንዲሁምሌሎች አገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በመንግሥት እና በህወሓት መካከል በአስቸኳይ ድርድር አካሂደው ሰላም እንዲያወርዱ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በተለይየአፍሪካ ሕብረት የቀድሞውንየናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን በመወከል ለወራት መቀለ እና አዲስ አበባ እየተመላለሱ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

መንግሥትለድርድሩ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቅሮ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት እንዲካሄድ እንደሚፈልግ የገለጸ ሲሆን የትግራይ አመራሮች ደግሞ ተደራዳሪዎቹን መሰየሙን አመልክቶ የኬንያው ፕሬዝዳንት አሸማጋይ እንዲሆኑ እንሚፈልግ ገልጿል።

ነገርግን ሁለቱም ወገኖች ለድርድር ፍላጎት እንዳለቸው ይግለጹ እንጂ እስካሁን ውይይት ስለመጀመሩ ወይም ወደዚያው የሚያመራ ተጨባጭ እርምጃ አልታየም።