ከወልዲያ ሸሽተው የነበሩ ነዋሪዎች ወደ ከተማዋ እየተመለሱ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, woldia city communication
በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል ባለፈው ሳምንት ጦርነት እንደ አዲስ መቀስቀሱን ተከትሎ ከሰሜን ወሎ ዞን መዲና፣ ወልዲያ ሸሽተው የነበሩ ነዋሪዎች ወደቀያቸው እየተመለሱ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለሦስተኛ ዙር አገርሽቶ የትግራይ ኃይሎች ቆቦ ከተማ መግባታቸው ከተሰማ በኋላ በርካቶች ከሰሜን ወሎ አካባቢዎች ወደ ደቡብ ወሎ ከተሞች ሲሸሹ ነበር።
ወልዲያ የሰሜን ወሎ ዞን መቀመጫ ስትሆን ለትግራይ ክልል በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኙና በርካታ ነዋሪ ከሉባቸው የአማራ ክልል ከተሞች አንዷ ናት።
ባለፈው ረቡዕ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከዚህ በፊት የደረሰውን የሚያስታውሱ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች በተለይም ሴት እና ህጻናት ልጆቻቸውን ይዘው፣ ቤት ንብረታቸውን በመተው ወደ ሌሎች ከተሞች በመጓዝ ላይ ነበሩ።
ጥቂት የማይባሉ ነዋሪዎችም ከቆቦ አካባቢ ወደ ወልዲያ እና ደሴ ከተሞች መግባታቸውን የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፈው ቅዳሜ የቆቦ ከተማ በትግራይ ኃይሎች ከመያዟ ቀደም ብሎ በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች ይደረግ የነበረውን ጦርነት በመሸሽ በርካታ ሰዎች ወደ ወልዲያ አቅንተዋል።
ጦርነቱ ተባብሶ ወልዲያን ጨምሮ ከቆቦ በመቀጠል ወዳሉት አካባቢዎች ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው ነዋሪዎች፣ ከወልዲያ ባሻገር ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻም ለማቅናት መነሳታቸውን አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግው ነበር።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ግን ወደ ደሴ እና ሌሎች ከተሞች ሸሽተው የነበሩት የከተማዋ ነዋሪዎች አሁን ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን እና በከተማዋ መረጋጋት እንደሚታይ አስረድተዋል።
“ወልዲያ ከተማ ተይዛለች ተብሎም ተወርቶ ነበር። ወልዲያ ግን አልተያዘችም። ጦርነት የነበረው በሰሜን (ከወልዲያ በስተሰሜን አቅጣጫ) አካባቢ ነበር። አሁንም ያለ ይመስለኛል። ወልዲያ ግን ከመጨናነቅ (በሰዎች እንቅስቃሴ) ወጪ ሰላም ነው” ሲል አንድ የከተማዋ ነዋሪ ተናግሯል።
ሌላኛው የከተማ ነዋሪ ደግሞ ከወልዲያ በስተሰሜን አቅጣጫ ካሉ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የሚገቡ ሰዎች ስላሉ፤ እንዲሁም ከወልዲያ ወደ ደሴ አቅጣጫ የሚሄዱ ስዎች ስለነበሩ፤ ባንኮች እና በክፍያ የሚታደርባቸው አልጋ ቤቶች ተጨናንቀው እንደነበረ ያስረዳል።
ከወልዲያ ርቀው በሚገኙት እንደ ጎብዬ፤ ሮቢት እና ተኩለሽ አካባቢ ውጊያ እንዳለ እንደሰሙ የሚናገሩት ሌላኛው የከተማ ነዋሪ፤ በዛሬው ዕለት በወልዲያ እና ዙሪያዋ ምንም አይነት ጦርነት እንዳልተካሄደ፤ የተኩስ ድምጽም እንደማይሰማ ይናገራሉ።
“አልፎ አልፎ ፋኖዎች ‘አለንላችሁ’ ለማለት መሳሪያ ይተኩሳሉ እንጂ ምንም የተኩስ ድምጽ በከተማዋ አይሰማም” ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ነዋሪ ይናገራሉ።
የፌደራሉ መንግሥት ሰኔ 2013 ዓ.ም. የተናጠል የተኩስ አቁም አዋጅ አውጆ አብዛኛው የትግራይ ክልልን ለቅቆ ከወጣ በኋላ የትግራይ ኃይሎች በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ከፍተው ወልዲያን ጨምሮ በርካታ የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች ተቆጣጥረው መቆየታቸው ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት ሦስተኛው ዙር ጦርነት ዳግም መቀስቀሱ ሲሰማ ሰዎች ከወልዲያ ከተማ ጥለው የወጡት ከዚህ ቀደም ከነበራቸው መጥፎ ትውስታ የተነሳ ነው ሲሉ ሌላ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ዛሬ ላይ እንደውም [አማጺያኑ] ከነበሩበት ተገፍተው ሄደዋል የሚል መረጃ ነው ያለው። ከባለፉት ቀናት በተሻለም መረጋጋት አለ” ብለዋል ነዋሪው።
መሠረታዊ አገልግሎቶች በወልዲያ
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን የማንጠቅሳቸው ሦስት የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ፤ በሰዎች እንቅስቃሴ መብዛት ምክንያት በወልዲያ አግልግሎቶችን ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።
በባንኮች ሰዎች ገንዘብ ለማውጣው ረዥም ሰዓታት ለመጠበቅ ይገደዱ እንደነበረ ገልጸው፤ ዛሬ ላይ ደግሞ ባንኮች ዝግ ሆነው መቆየታቸውን ገልጸዋል።
“ዛሬ ባንኮች ዝግ ናቸው። ነገ ይከፈታል የሚል መረጃ አለ። መብራት፣ ኢንተርኔት እንደተለመው ይቆራረጣል እንጂ አሁንም አለ። ሱቆች ክፍት ናቸው። ሰው ይንቀሳቀሳል። ሻይ እና ምግብ ቤቶችም ክፍት ናቸው” ብለዋል አንዱ ነዋሪ።
ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የመንግሥት ኃይሎች “በአንድ ቦታ ተሰባስቦ የመዳረጀት ነገር አለ፤ አሁን ላይ ብዙ ሠራዊት እየገባ ነው” ሲሉ ሌላኛው ነዋሪ ተናግረዋል።
ጨምረውም ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ሰላም መሆኑን እና የተኩስ ድምጽ እምባዛም እንደማይሰማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተፈናቃዮች እና ደሴ
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተመሳሳይ ባለፈው ዓመትም ወደ ሰሜን ወሎ ዞን ተዛምቶ የነበረ ሲሆን ነዋሪዎችም ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ወጥተው ለመሄድ ተገደው ነበር።
በርካታ ተፈናቃዮችን በማስተናገድ ቀዳሚ የነበረችው የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ ደሴ አሁንም ከቆቦ እና ከወልዲያ የሸሹ በርካታ ሰዎች እየተቀበለች ነው።
ከወልዲያ ከተማ በእግራቸው ጉዞ ጀምረው የነበሩ ነዋሪዎች ከተማዋ በመረጋጋቷ እየተመለሱ መሆናቸው ቢገለጽም፣ በደሴ ጦርነቱን በመሸሽ ከሰሜን ወሎ ዞን የመጡ ሰዎች በስፋት ይታያሉ።
አብዱ የተባሉ የደሴ ከተማ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደገለጹት ባለፉት ቀናት ብዙ ሰዎች ወደ ደሴ ገብተዋል፣ በዚህም ምክንያት በከተመዋ ከፍተኛ መጨናነቅ እንዳለ ተናግረዋል።
“መጨናነቅ አለ። በተለይ መናኽሪያ አካባቢ ብዙ ሰው አለ። ሰዉ መሄድ ይፈልጋል የትራንስፖርት አገልግሎት ደግሞ የለም። ወደ አዲስ አበባ መሄድም አይቻልም፤ ክልክል ነው። ምግብ ቤቶች፣ ሆቴሎች በተፈናቃይ ተሞልተዋል” ብሏል ይህ ነዋሪ።
በአሁኑ ወቅት በደሴ ከተማ በርካታ ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎች ቢኖሩም በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት በቂ ድጋፍ ባለመኖሩ ሰዎች በረንዳ ለማደር እየተገደዱ እንደሆነ ይህ ነዋሪ ይናገራል።
“ዘመድ ያለው ዘምድ ቤት ገብቷል፤ ሌላው ተሸከርካሪዎች ውስጥ እያደረ ነው። በረንዳ ላይ እያደሩ ያሉ ሰዎችም አሉ። ከመናፈሻ እስከ መላኩ፤ ከመናኽሪያ እስከ ፒያሳ ባሉት አካባቢዎች ሰዎች በረንዳ ላይ ሲተኙ አይቻለሁ” በማለት የደሴ ተከማ ነዋሪው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሰዓት እላፊ በወልዲያ
ጦርነቱ ከትግራይ ጋር በሚዋሰኑት የአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች ከተቀሰቀሰ በኋላ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን በነዋሪዎች ላይ የደኅንነት ስጋት ፈጥሯል።
በዚህም ሳቢያ ጥቂት ያመይባሉ ሰዎች ከቆቦ አካባቢ በመውጣት ወደ ወልዲያ እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሄዳቸውን ዕሁድ ዕለት ቢቢሲ ያናገራት አንዲት የቆቦ ነዋሪ ለቢቢሲ መግለጿ ይታወሳል።
ነዋሪዋ እንዳለችው የትራንስፖርት አገልግሎት ስለሌለ ሰዎች በእግር መጓዛቸውን እንዲሁም በአካባቢው ገልጻ፣ በጉዞው ላይ ወንዝ ከሚያቋርጡ ሰዎች መካከል አንዲት እናት ከነልጇ በጎርፍ መወሰዷን ተናግራለች።
የአማራ ክልል መስተዳደር ተከፈተብኝ ያለውን ወረራ ለመከላከል ለሕዝቡን ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ በክልሉ ምሥራቃዊ አካባቢዎች ባሉ ከተሞች ውስጥ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል።
በዚህም የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ከነሐሴ 22/2014 ዓ.ም. ጀምሮ የሰዓት እላፊ ገደብ በአስተዳደሩ ተጥሏል።
ከመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላት በስተቀር ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ ማንኛውም ሰው መንቀሳቀስ ተከልክሏል።
ለተርሸከርካሪዎችም ለፀጥታ ሥራ ስምሪት ከተሰጠው ተሽከርካሪ ውጪ የትኛወም ተሽከርካሪ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ መንቀሳቀስ የማይችል መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።
ይህ የሰዓት እላፊ ገደብ ካለፉት ቀናት ጀምሮ ከወልዲያ በተጨማሪ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ውስጥ ተጥሏል።












