በመኪና፣ በጋሪ እና በእግር ከመቀለ እስከ ሸገር የተደረገው አንድ ወር የፈጀው ጉዞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
*ይህ ቃለ ምልልስ የተደረገው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንደ አዲስ መልሶ ከመቀስቀሱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ነው።
ሰለሞን (ስሙ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ተቀይሯል) የትግራይ ክልል መዲና መቀለን የሚያውቃት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ነው።
ወደ ሥራ ዓለም ሲገባ እጆቿን ዘርግታ የተቀበለችው ከተማ ናት - መቀለ።
ያለፉትን 'ዘጠኝ ዓመታት' ስትስቅ ስቆ፣ ሲከፋት ተከፍቶ ኖሯል።
"መቀለ በሥራ ጉዳይ የሄድኩት በ2005 ዓ.ም ነው። እዚያ ሥራ ስሠራ ኖሪያለሁ" የሚለው ሰለሞን እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ እዚያው ይኖር እንደነበር ይናገራል።
ከ2005 ዓ.ም በኋላ ምን ያልተፈጠረ ነገር አለ።
ሠላም፣ ጦርነት፣ ተስፋ፣ ጨለምተኝነት. . . ብዙ ብዙ ነገር ተፈጥሯል፣ እየተፈጠረም ነው ይላል።
ከጦርነቱ በፊት የነበረውን ሕይወት 'አሪፍ ነበር' ሲል ይገልጸዋል።
'እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ' ጥሩ የሚባል ሕይወት ነበረው።
በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት ግን ሁሉንም ነገር ቀየረው።
"ጦርነት በጣም አውዳሚ ነው" የሚለው ሰለሞን "ከጦርነት በኋላ ሁሉም ነገር ሲዘጋጋ በተለይም የመንግሥት ሠራተኛው በጣም ተጎጂ ሆነ" ይላል።
እንቅስቃሴ ተቋረጠ። መብራት፣ ስልክ፣ ባንክ. . . የለም። ደሞዝም ማግኘት ቆመ።
ይህ ከጦርነቱ ሰቆቃ ቀጥሎ የመጣ ችግር ሆነ።
እንደ ሰለሞን ላሉ እና ከመሃል አገር ወደ ትግራይ ላቀኑት ደግሞ ችግሩን ከፍ ያለ አደረገው።
"በጣም ተቸግረን ነበር" ሲል ሰለሞን ሁኔታውን ይገልጸዋል።
ከጦርነቱ በኋላ በመቀለ ፈታኝ የሆነው ኑሮ
ሰለሞን በየትኛውም ወቅት ቢሆን አገልግሎት መስጠት ግዴታ በሆነበት ሙያ ውስጥ ነበር ያለው።
ከጦርነት በፊት ሥራውን ይሠራ ነበር። በጦርነቱ ወቅትም ሥራው ላይ ነበር፣ ከጦርነቱ በኋላም ከሥራ ገበታው አልተለየም።
ቀደም ሲል ሥራ ይሠራል ይከፈለዋል። ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ ይሠራል ክፍያ የለም።
ሰለሞን እንደሚለው በዚህ የጦርነት ሁኔታ ውስጥ መስራት ይከብዳል። "ጦርነትም ኖረ አልኖረ ግን በሙያህ ሥራህን አክብረህ መስራት አለብህ። በዚያም መልኩ ነው ስንሠራ የነበረው። በኋላ ላይ ደመወዝ ቆመ። ደመወዝ የሚከፈለን ከፌደራል መንግሥት ነበር።"
ጦርነቱን ተከትሎ መቀለ ውስጥ ኑሮ የማይቀመስ ሆኗል።
ቤት ኪራይ፣ ምግብ እና ሌሎችም ወጪዎች ላሉበት ሰለሞን ደግሞ ነገሮች ይበልጥ ከባድ ሆኑበት።
ታዲያ ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዴት አለፈው? ሲባል "አልፎ አልፎ እርዳታ ይሰጥ ነበር፤ ትንሽ ብርም ተሰጥቶናል። ትንሽ ስንዴ እና ዘይትም ተሰጥቶናል። አልፎ አልፎ ነው እሱም። በሦስት ወር በአራት ወር አንዴ ነው የተሰጠን። የግል ሥራ ካላቸው ጓደኞቻችንም ገንዘብ እየተቀበለን እና እየተበደርን ነው የቆየነው" ሲል ይመልሳል።
ዓለም ስለ ኑሮ ውድነት በማውራት ይውል ማደር ከጀመረ ሰነባበተ።
"በመቀለ ያለው ኑሮ ውድነት ግን አይነገርም" ይላል ሰለሞን።
"አብዛኛው ሕዝብ ገንዘብ የለውም። ያላቸው ጥቂቶች ናቸው።"
"ነጋዴ እና በጣም ሀብታም ሆኖ ብር ያስቀመጠ እንጂ፣ ሌሎቹ የመንግሥት ሠራተኛ የሚባሉት እንዴት እንደሚኖሩ እኔ ራሱ ግራ ይገባኛል።"
ኑሮ ቢወደድም ሕይወት ይገፋል።
መቀለ አሁን ሌላ ከተማ ሆናለች። ኑሮም አኗኗርም ተቀይሯል።
"አንድ ሊትር ቤንዚን ከ700 እስከ 800 ብር ነው [የሚሸጠው]። እንቅስቃሴም ብዙም የለም። ያላቸው ነጋዴዎች ካልሆኑ በስተቀር የታችኛው እና የመካከለኛው የኅብረተሰብ ክፍል ምንም እንቅስቃሴ እያደረገ አይደለም። ብር ያለው ብቻ ነው የሚንቀሳቀሰው።"
"ብርም ስለሌለ እንቅስቃሴም ትንሽ የተገታ ነው። ከዚያ ውጪ በደኅንነት እና ፀጥታ ረገድ ምንም የሚያሰጋ ነገር አልነበረም በእኔ በኩል" ይላል።
"ከከተማ ከተማ እንቅስቃሴ አለ። ግን እንደ ድሮው አይደለም። ከመቀለ 45 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኘው ውቅሮ ከተማ ለመሄድ 300 እስከ 400 መክፈል ያስፈልጋል። ዋጋው እንደ ሁኔታው ይቀያየራል። ድሮ 30 ብር ገደማ ነበር። ከዚያ አንጻር ሲታይ ብዙም እንቅስቃሴ የለም። ከተማ ውስጥ ግን ሲታይ መቀለ እንቅስቃሴ አለ። ግን እንደ ቀድሞው አይደለም ድባቡ። እንቅስቃሴውም ቢሆን 75 በመቶ ቀንሷል ማለት ይቻላል።"
ነገር ግን በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ሕይወት እንደምንም ይገፋል።
"ሰዉ የሚበላ ነገር የሚያገኘው አልፎ አልፎ እርዳታ አለ መሰለኝ" ይላል።
ካለው እየተበደረም ሆነ ሃብታም ዘመድ ያለው ከእነሱ እየወሰደ ቀኑ ይገፋል።
ከአዲስ አባባም ከባሕር ማዶም ከ35 - 40 በመቶ እየተቆረጠ በሰዎች በኩል ገንዘብ የሚላክላቸውም አሉ።
"ኑሮ በዚህ መልኩ ይገፋል። ብዙ ሕዝብ (በተለይም ታች ያለው) እየተራበ ነው። ከተማ ውስጥ ‘ርቦኛል’ ብለው ለመናገር ስለሚደብቁ ነው እንጂ ችግር ነበር እኔ እስካየሁት ድረስ" ሲል ያስታውሳል።

ጉዞ ከመቀለ ወደ ሸገር
ሰለሞን ሥራው በሁኔታዎች አይወሰኑም።
ጦርነት ኖረ አልኖረ ይሠራል። ተከፈለውም አልተከፈለውም ለህሊናው ሲል ሠርቷል።
ከወርሃዊ ደሞዝ ጋር ከተለያየ 10 ወር ገደማ ተቆጠረ። ግን ሥራውን እንደቀጠለ ቆየ።
ግን ሁሉም ነገር መጨረሻ አለው።
"ምንም ገቢም የለንም፤ ምንም የለንም። ካላቸው እየተበደርኩም ቢሆን ለመኖር ሞከርኩ። በኋላ ግን ቤተሰቦቼ ድምጼን ስላልሰሙ ይጨነቃሉ ብዬ ነው የወጣሁት። ከሥራዬ አንጻር መውጣትም አልፈለኩም ነበር። የተቸገረውን ሕዝብ ለማገልግል እፈልግ ነበር። ቤተሰቦቼ እንዳይጨነቁ ብዬ ነው ወደ ጥር አካባቢ ለመውጣት የወሰንኩት" ሲል የወሰነበትን አጋጣሚ አጫውቶናል።
ጊዜው ደረሰና የዘጠኝ ዓመት ቤቱን ጥሎ ወጣ።
ጉዞ ከመቀሌ አላማጣ።
መቀሌ - ማይጨው - ኮረም - አላማጣ።
በመኪና ለነበረው ጉዞ 700 ብር ከፍሏል።
አላማጣ ሁለት ቀናት አሳለፈ።
ቀጣይ ጉዞ ወደ ዋጃ።
ዋጃ የደረሰውም በመኪና ነበር።
ከዋጃ እስከ ቆቦ በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች በዐይነ ቁራኛ የሚተያዩበት አካባቢ ነው።
ከትግራይ ለመውጣት የሚያግዙ ደላሎች አሉ ቢባልም፣ ሰለሞን ደላሎች አላጋጠሙትም።
ከዋጃ እስከ ቆቦ ያለው መንገድ ግን አስቸጋሪ ነው።
ባለው የፀጥታ ሁኔታ ትራንስፖርት የለም።
"ከዋጃ እስከ ቆቦ ያለውን በእግር እና በጋሪ ነው የደረስኩት። ኬላ ላይም የመሃል አገር መታወቂያ ስላለኝ እሱን አሳይቼ 'በሥራ ምክንያት መቀለ መኖሬን እና ጦርነት ስላለ ፈርቼ ነው' ብዬ ነግሬያቸው ለመከላከያ እጅ ሰጠሁ፤ ቆቦ ሳልደርስ ማለት ነው።"
"ኬላ ላይም የትግራይ ኃይል የሚባል አለ። እነሱም አዩኝ መታወቂዬን አዩ ትውልድ ቦታዬን አይተው ጠየቁኝ። 'ለራስህ ኃላፊነቱን ውሰድ እና እልፍ' አሉኝ። ከዚያ ለመከላከያ እጄን ሰጠሁ።"
በእነዚህ ቦታዎች በሙሉ ፍተሻ አለ።
መከላከያ ተቀብሎት ፍተሻ ከተደረገለት በኋላ ቆቦ ላይ ፖሊስ ጣቢያ ላይ አሳደሩት።
ቀጥሎ ከትግራይ የሚወጡ ተፈናቃዮች ያሉበት መጠለያ ስፍራ አለ።
ይህ መጠለያ ስፍራ ‘ጃሬ’ የሚባል ሲሆን ሐይቅ ሳይደርስ የሚገኝ ነው።
“እዚያ ለደኅንነት እና ለማጣራት ተብሎ ሁላችንም (የትግራይ ተወላጅም ሆነ ሌሎችንም) ከትግራይ ወደ መሃል አገር የምንመጣ ቢያንስ 24 ቀን አቆዩን" ይላል ሰለሞን።
"ካምፑ ውስጥ ምንም የለም። በጣም አሰልቺ ነው። እንዲያውም እሱ ነው የጎዳን። ምግብ በእርዳታ የሚሰጥ አለ። ግን ምንም አልተመቸንም ነበር። መኝታውም፣ ውሃም፣ መጸዳጃ ቤትም አልተመቸንም ነበር። ከዚያ የመንግሥት ሠራተኛ እና ባለሙያ መሆናችንን አስረድተን ነው ያስወጡን" ይላል።
ቀጣዩ ጉዞ ወደ መዳረሻው ሸገር - አዲስ አበባ ሆነ።
ከመቀለ አዲስ አበባ ለመድረስ አንድ ወር ገደማ ፈጅቶበታል።
ከመነሻው እስከ መድረሻው ባደረሰው ጉዞ መኪና፣ ጋሪ እና የእግር ጉዞ ማድረግ አስፈልጎታል።
የእግር ጉዞው ‘አጭር ነበር’ ይላል።
"አንድ 20 ኪሎ ሜትር ያህል ነው። ከዋጃ እስከ ቆቦ ድረስ መሀል ላይ መከላከያ ጋር እስክንደርስ ነው። ትንሽ በጋሪ ሄድን ከዚያ ከጋሪ ወርድን በእግር አንደ ሰዓት ያህል ተጓዝን" ይላል።
የማይገመተውን ጉዞ ሲጀምር ከውሃ ውጪ ምንም አልያዘም ነበር።
ለምግብ ይሆነኛል ብሎ የተወሰነ ብር ቋጥሮ ይዟል።
"ምግብ አልያዝንም። ፖሊስ ጣቢያ ከገባን በኋላ እንደ ታሳሪ ሳይሆን እንደተፈናቃይ አንድ ላይ አድርገውን ነበር። ምግብም ትንሽም ብር ሰለያዝኩኝ እሱን ተጠቀምኩኝ። ከዚያ በኋላ ካምፕ ስንገባ እርዳታ ነበር። ዱቄት እና ሩዝ ተሰጠን። የሃይማኖት ተቋማት የማብሰያ ዕቃ ሰጥተው ነበር። ከእኛ ቀድመው ስለሰጡ አልደረሰም ነበር። ቀድመው የደረሱት ስላገኙ ከእነሱ ጋር ገንፎም ምንም እየሠራን እንበላ ነበር።"
ሰለሞን ከመቀለ እስከ አላማጣ ብቻውን ነው ጉዞ የጀመረው።
ቆቦ የሚያውቃቸውን አራት ሰዎች አግኝቷል።
አራቱም ቀድመውት ቆቦ የደረሱ ናቸው።
መንገዱ ላይ ከትግራይ አትወጡም የሚል አልገጠመውም።
የመከላከያ አባላትም ለምን መጣችሁ? በሚል አንቀበላችሁም አላሏቸውም።
ሰለሞን ለዓመታት መቀለ ሲኖር አነሰም በዛም ንብረት አፍርቷል።
ግን ምንም ንብረት ይዞ አልወጣም።
"ልብስ ራሱ ሁለት ሸሚዝ፣ ሁለት ቲሸርት እና ሁለት ሱሪ ነው ይዤ የወጣሁት። ሌላውን እዚያው ተወልደው ላደጉት ጓደኞቼ ነው ሰጥቼ የወጣሁት" በማለት ያስረዳል።
ከቃለ መጠይቁ በፊት ከሰለሞን ጋር በነበረን ቆይታ ንብረታቸውን ሸጠው የወጡ ሰዎችን እንደሚያውቅ አጫውቶናል።
እነዚህ ሰዎች ገንዘባቸው እዚያው መቀለ ላለ ሰው ይሰጣሉ።
አዲስ አበባ ሲደርሱ ብሩን የተቀበሉት ሰዎች ዘመዶች ብሩን ይሰጧቸዋል።
ለገንዘብ አሸጋጋሪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ብር በመክፈል ገንዘብ ትግራይ የሚልኩ ቤተሰቦች በአነስተኛ ወጪ ገንዘብ በዚህ ዘዴ ለቤተሰተሰቦቻቸው እንዲደርስ ያደርጋሉ።
ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ከትግራይ እንደሚወጡ ሁሉ ወደ ትግራይ የሚገቡ ሰዎች ስለመኖራቸው "ወደ ትግራይ የሚገቡ ሰዎች እንዳሉ በወሬ ሰምቻለሁ ግን እኔ አላጋጠሙኝም" ሲል ሰለሞን ይናገራል።
ሰለሞን አሁን ቤተሰቦቹን አግኝቷል።
"ቤተሰቦቼ በሕይወት ያለሁ አልመሰላቸውም እና የሞትኩ ነው የመሰላቸው። ስመለስ አላመኑም። የሚነገረው ታሪክ እና እዚያ ያለው ታሪክ የተለያየ ይመስለኛል። እዚያ (ትግራይ) ትግራዋይ ያልሆነ በሙሉ የሚጨፈጨፍ ይመስላቸው ነበረና ለዚያ ነው የሞትኩ የመሰላቸው። ስመለስ በጣም ተደስተዋል" ይላል።
ሰለሞን ሥራውን የሚጀመርበት ዕድል ተመቻችቶለት ወደሚወደው ሙያው ተመልሷል።
አሁንም ግን መቀለ ከአእምሮው አልወጣችም።
"እኔ ሥራዬን እወዳለሁ። አገሩንም [መቀሌን] ስለወደድኩት አሁን ራሱ ሠላም ተፈጥሮ ወደዛ ተመልሼ ወደ ነባር ሥራዬ ብንመለስ ደስተኛ እሆናለሁ። ብዙ ነገር አስታውሳለሁ። ሥራ የጀመርኩት መቀሌ ነው" ይህን ሁሉ መልካም ኑሮውን ያደናቀፈበትን ጦርነት ሰለሞን በጣሙን ይጠላዋል።
ወደፊት ግጭቱ ቆሞ ሰላም ተፈጥሮ ወደ መቀለ ተመልሶ የነበረበት ሥራውን ለመቀጠል ከፍ ያለ ፍላጎት አለው።
አዲስ አበባም ከገባ በኋላ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና የእርዳታ ተቋማት ውስጥ ያለውን ኢንተር ቤት በመጠቀም ትግራይ ከሚገኙ ጓደኞቹ ጋር በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ይገናኛል።
"በሠላም እንደደረስኩ እና በጊዜያዊነት ሥራ እንደጀመርኩ ነግሪያቸዋለሁ። እነሱም ብዙም ለውጥ እንደሌለ እና የኑሮ ውድነት ከበፊቱ እንደጨመረ ነው ነግረውኛል። በሕይወት አለን ሠላም ነን ብለው አጫውተውኛል።"
"በመጨረሻ ማለት የምፈልገው ለሁሉም ልቦና ይስጥና ሠላም ወደ ነበረበት ተመልሶ አገራችን ሰላም ሆና ሁላችንም በቅንነት ሕዝባችንን እንድናገለግል ነው። ሰላም ቢፈጠር ለሁሉም ወገን። ሰላም ማየት ነው የናፈቀን።"












