[ምልከታ] በትግራይ የዘር ጭፍጨፋ ክሶችና የረሃብ ስጋት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
- ፀሐፊ, አሌክስ ደ ዋል*
- የሥራ ድርሻ, የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ
ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በትግራይ የዘር ጭፍጨፋ እየተፈጸመ ነው ማለታቸው ብዙዎችን አነጋግሯል።
የትግራይ ተወላጁ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ ጥቅምት ላይ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ "እንዳልናገር ድምጼ ታፍኖ ነበር። በፍርሃት መናገር አልቻልኩም ነበር" ብለዋል።
በትግራይ ክልል እየተፈጸመ ያለው ሰቆቃ የአቡነ ማቲያስን እንዲሁም የበርካታ የትግራይ ተወላጆችን ልብ ሰብሯል።
በግጭቱ ሳቢያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ዳያስፓራዎች በተለያዩ አገራት መዲናዎች የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል። በተጨማሪም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ንቅናቄ በማድረግ "የዘር ጭፍጨፋ እየተፈጸመ ነው" ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በጅምላ ጥቃት ተፈጽሟል የሚለውን ክስ የተጋነነና ፖለቲካዊ መነሻ ያለው ሲል ያጣጥላል።
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ከተናገሩ በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባልተለመደ መልኩ ቅዱስ ሲኖዶሱ ራሱን ከፓትርያርኩ ንግግር ገሸሽ አድርጓል።
የዘር ጭፍጨፋ ከወንጀሎች ሁሉ የከፋ ነው። በርካቶችን እጅግ ከማስቆጣቱ ባሻገር የዘር ጭፍጨፋ ሲፈጸም በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቁ ተሟጋቾችም አሉ። ይህ ልዩ እርምጃ የዘር ጭፍጨፋን ለማስቆም ወታደር መላክን ይጨምራል።
የዘር ጭፍጨፋ የሚለውን ቃል የፈጠሩት የአይሁድ ተወላጁ ፖላንዳዊ ጠበቃ ራፋኤል ለምኪን ናቸው።
ቃሉን ጥቅም ላይ ያዋሉት አሰቃቂውን የናዚ ጭፍጨፋ ለመግለጽ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት እአአ በ1948 የዘር ጭፍጨፋ ስምምነትን ሲያጸድቅ በዓለም አቀፍ መዛግብት ውስጥ መጠቀስ ጀምሯል።
የጥላቻ ንግግር
የናዚ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኑረንበርግ ለፍርድ ሲቀርቡ ዐቃቤ ሕግ የከሰሳቸው ሰብዓዊ መብትን በገፈፉ ወንጀሎች ነው።
ይህ ማለት በመንግሥት ወይም እንደ መንግሥት ባለ መዋቅር በስልታዊ ሁኔታ የሰዎች መብት ተጥሷል ማለት ነው።
የዘር ጭፍጨፋ ሲተረጎም የጥቃት አድራሹ ኢላማ ከግምት ይገባል። ይህም ጥቃት አድራሹ "የአንድን አገር፣ ብሔር፣ ዘር ወይም ሐይማኖት አባላት በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት ሲነሳ" ማለት ነው።
እስካሁን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በትግራይ ሰብዓዊ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ሪፖርት አድርገዋል። ይህ ሊለወጥ ይችላል።
አንዳንድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን፤ ህወሓት ፈጽሟቸዋል የሚባሉ ወንጀሎችን በሙሉ የትግራይ ሕዝብ ላይ በማላከክ እና የሚያንቋሽሽ ቃል በመጠቀም ለትግራይ ተወላጆች ጥላቻ አሳይተዋል።
"የቀን ጅብ" የመሰሉ ቃላት ሕዝቡ ላይ ጥላቻን ለመፍጠር ውለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ህወሓት በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ሰፊውን ድርሻ ይዞ ዘልቋል። በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የነበረው መካረር ጫፍ የነካው የብሔራዊ ምርጫ ቀን ሲዛወር በትግራይ ክልላዊ ምርጫ ሲካሄድ ነው።
ይህ መካረር ተባብሶ ጥቅምት ላይ ሁለቱ ኃይሎች ወደ ጦርነት አምርተዋል።
የትግራይ ተወላጆች መከላከያ ሠራዊቱን ጨምሮ ከተለያዩ የመንግሥት ሥራ እየተባረሩ እንደተባረሩ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
እንቅስቃሴያቸው፣ መኖሪያቸው እና ንግዳቸው እንደታገደም ተገልጿል።
እነዚህ ክሶች ግድያን፣ መድፈርንና የማስራብን ያህል ባይሆኑም የዘር ጭፍጨፋ እየተካሄደ ነው ለሚል ክስ መነሻ ይሆናሉ።
በትግራይ የጅምላ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል የሚሉ ክሶች ከሁሉም አቅጣጫዎች ተሰምተዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የዘር ጭፍጨፋ ተፈጽሟል የሚል ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው በከፍተኛ ደረጃ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ፍርድ ነው።
ፍርድ ቤቱ ይህንን ጉዳይ ሊመለከት የሚችለው በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ነው።
ምክር ቤቱ ላይ አፍሪካ ያሳደረችውን ጥርጣሬ እንዲሁም የቻይና እና የሩሲያን ተቃውሞ ከግምት በማስገባት ግን ይህ ውሳኔ የሚተላለፍ አይመስልም።
በዘር ጭፍጨፋ የተፈረደበት የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪ
የሌላ አገር ዜግነት ያለው አንድ ኢትዮጵያዊ በወንጀል ሊከሰስ፣ ሊፈረድበትም ይችላል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የማሰር መብት ባላቸው እንደ ፈረንሳይ እና ቤልጅየም ባሉ አገራት የእስር ማዘዣ ሊወጣበትም ይችላል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በዘር ጭፍጨፋ ተጠያቂን ወንጅላለች። የአገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ከ"ፖለቲካ ቡድኖች" ውጪ ያሉትን በዘር ጭፍጨፋ ያካትታል።
ይህ ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም። ኢትዮጵያ የተጠቀመችው ራፋኤል ለምኪን ለተባበሩት መንግሥታት የጻፋቸውን ቆየት ያሉ ማጣቀሻቆች ናቸው።
ይህም ሶቭየት ሕብረት የፖለቲካ ቡድኖችን ኢላማ ማድረግ በተባበሩት መንግሥታት የዘር ጭፍጨፋ ስምምነት መካተት የለበትም በሚል የተከራከረችበት ወቅት ነው።
ምግብ መከልከል አንድ የዘር ጭፍጨፋ መንገድ ነው ይላሉ።
'አክሲስ ሩል' በተባለው መጽሐፋቸው ከናዚዎች የጋዝ ቻምበርና ገዳይ ቡድን በበለጠ የምግብ መጠን ከመቀነስ ምግብ ወደ መከልከል ስለተሻገረው የናዚ እርምጃ ጽፈዋል።
በእንግሊዘኛው 'ስታርቬሽን ክራይምስ' የሚባለው ሆነ ብሎ ሰውን የማስራብ ወንጀልን ይገልጻል። ቃሉን መጀመሪያ ላይ የተጠቀሙት ብሪጅት ኮንሊይ ይባላሉ።
ቃሉ የሚገልጸው፤ ረሀብን እንደ ጦርነት መሣሪያ፣ እንደ ጭቆና መንገድ ወይም ሰዎችን ለመቅጣት መጠቀምን ነው።
የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ባለፈው ሳምንት ባወጡት መግለጫ፤ በትግራይ አስጊ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ይህ ቀውስ የዝርፊያ፣ በግዳጅ የማፈናቀል እንዲሁም ምግብ፣ ውሃ እና የጤና አገልግሎትን የመግታት ውጤት ነው።
በተጨማሪም መደፈር የደረሰባቸው ሴቶች ራሳቸውን እና ልጆቻቸውን መንከባከብ ያለመቻላቸው እና ሰብዓዊ እርዳታ የመገታቱም ማሳያ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከ30 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ የመንግሥቱ ኃይለማርያም ዘመን ባለሥልጣናትን በልዩ ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ አቅርባለች። የፖለቲካ ግድያ ክስ በዘር ጭፍጨፋ እንዲታይ ተወስኖም ነበር።
ዋነኛ ትኩረቱ አገዛዙ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በፖለቲካ አቋማቸው የረሸነበት "ቀይ ሽብር" ነበር።
መንግሥቱ ኃይለማርያም በሌሉበት በዘር ጭፍጨፋ የተፈረደባቸው ይህ አሰቃቂ ወንጀል ከተፈጸመ ከ40 ዓመታት በኋላ ነበር።
የመብት ተሟጋቾች ፍርድ ቤት ውሳኔ እስከሚሰጥ መጠበቅ አይሹም። ለዘር ጭፍጨፋ ማስረጃ ተጠናቅሮ እስከሚቀርብ ድረስ የሰዎች ሕይወት ይቀጠፋል።
ይህንን ከግምት በማስገባት የመብት ተሟጋቾች እና ዲፕሎማቶች ብሔር ተኮር ግድያ የሚገለጽበት መንገድ ፈጥረዋል።
እአአ በ1990 ዩጎዝላቪያ ስትበተን ዘር ማጥፋት የሚል ቃል ጥቅም ላይ ውሎ ነበር።
ይህ ቃል በሕግ የተደነገገ አይደለም። የዘር ጭፍጨፋ ውስጥ ያሉና ዘር ማጥፋትንም የሚገልጹ ድርጊቶች አሉ። እነዚህም ቡድን ለይቶ መግደል፣ መድፈር እና ማፈናቀል ናቸው።
ከወራት በፊት በአሜሪካ የወጣ ሪፖርት በትግራይ "ዘር ማጥፋት እየተፈጸመ ነው" ብሏል።
ከዩጎዝላቪያ ጦርነት አሥር ዓመታት በኋላ የአሜሪካ የጦር ወንጀሎች ልዩ ቃል አቀባይ ዴቪድ ሸፈር በእንግሊዘኛ 'አትሮሲቲ ክራይምስ' የሚል ቃል መስርተዋል።
ይህን ያደረጉት አንድ ቡድን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት የዘር ጭፍጨፋ ነው ወይስ አይደለም? ከሚለው የሕግ ክርክር ለመውጣት ነው።
"መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የዘር ጭፍጨፋ ተፈጽሟል ወይም እየተፈጸመ ነው የሚል የሕግ ውሳኔ እስከሚተላለፍ ድረስ እርምጃ ከመውሰድ መታቀብ የለባቸውም" ሲሉ ያስረዳሉ።
በአንድ አገር አውድ ትርጉም የሚሰጥና አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት የሚሰነዘርበትም ጊዜ አለ። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋል ነው።
በክልሎች መካከል የሚገኝ ድንበር እንዲሁም በየክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች ጉዳይ ለዚህ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሞ፣ አማራ፣ ሶማሊ እና ጉምዝ ማኅበረሰቦች ዘንድ ይህ ግጭት በስፋት እየታየ ነው። የእነዚህ ማኅበረሰቦች ቃል አቀባዮች የዘር ጭፍጨፋ እየተፈጸመ ነው ሲሉ ይከሳሉ።
የዘር ጭፍጨፋ እየተፈጸመ ነው ማለት አንቂ ደውል ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ ይወሰድ አይልም።
በ2004 ዳርፉር ውስጥ የዘር ጭፍጨፋ ተፈጽሟል የሚል ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ነበር።
የመብት ተሟጋቾቹ ያሰቡት የዘር ጭፍጨፋ መፈጸሙን መንግሥት ካመነ ወታደሮች እንደሚላኩ ነው። አንድ ተቃዋሚ በዋሽንግተን ዲሲ ሰልፍ ላይ "ከኢራቅ ውጡ፤ ዳርፉር ግቡ!" የሚል መፈክር አስነብቧል።
ነገር ግን ይህንን ማድረግ ግዴታ አይደለም። የአሜሪካ ምርመራ የሱዳን መከላከያ እና የጃንጃዊድ ሚሊሻ የዘር ጭፍጨፋ መፈጸማቸውን ግን ያሳያል።
የያኔው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የምርመራውን ውጤት ቢቀበሉም ግኝቱ የአሜሪካን ፖሊሲ እንደማይለውጥ አስታውቀዋል።
ይህ ፖሊሲ ሰብዓዊ እርዳታ እና ሰላም የማስጠበቅ ተልዕኮ ላይ ያተኮረ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዘር ጭፍጨፋ ክርክሮች
ዳርፉር ውስጥ የዘር ጭፍጨፋ ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም የሚለው ክርክር፤ እልቂቱን ለማስቆም መወሰድ የሚገባውን እርምጃ አጓቷል።
አሜሪካ የተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ ነው ስትል የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ መርማሪ ግን የዘር ጭፍጨፋ አላለውም።
የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ የሱዳንን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አስደስቷል።
የተባበሩት መንግሥታት "ከዘር ጭፍጨፋ ያልተናነሰ ወንጀል ተፈጽሟል" ቢልም እንኳን ለዚህ ገለጻ እምብዛም ትኩረት አልተሰጠውም።
ኋላ ላይ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዘዳንት ኦማር አልበሽር ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል።
አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በሱዳን አመራሮች ታስረዋል። ለፍርድ ቤቱ ተላልፈው ግን አልተሰጡም።
የሚሊሻ መሪው አሊ አብደል ራህማን "ኩሻይብ" ላይ በ31 የጦር ወንጀል እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክሶች የፍርድ ሂደት ቢከፈትም በዘር ጭፍጨፋ አልተከሰሰም።
አልበሽር በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ከሆነ ዐቃቤ ሕግ በዘር ጭፍጨፋ ለመክሰስ መወሰን አለበት።
አሁን በዋሽንግተን ዲሲ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያሉት በዳርፉር እና በዩጎዝላቪያ የዘር ጭፍጨፋ ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም የሚለውና ጠባሳ ትቶ ያለፈውን ክርክር ያራመዱ ሰዎች ናቸው።
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ትግራይ ከዳርፉር ጋር እየተነጻጸረች ነበር።
አንድ ባለሥልጣን እንዳሉት፤ ቀውሱን ማስቆም ባልቻሉ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ የፋይናንስ ማዕቀብ ለመጣል እቅድ አለ።
ቀውሱ፤ ሰብዓዊ ወንጀል ስለመሆኑ ለማጣራት ምርመራ እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።
ሆኖም ግን የዘር ጭፍጨፋ ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም የሚለውን ለመፈተሽ እምብዛም ፍላጎት የለም። ይህም ለችግሩ መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ ነገሮችን ወደማባባስ ላለመውሰድ በመፍራት ይሆናል።
*የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አሌክስ ደዋል በአሜሪካው ተፍትስ ዩኒቨርስቲ በሚገኘው የፍሌቸር የሕግ እና ዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት ውስጥ የወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ናቸው። ኢትዮጵያን እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ አገራትን የሚዳስሱ የትንተና ጽሑፎቻቸው ያዘጋጃሉ።








