የትግራይ ኃይሎች የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦር በአራት አቅጣጫ ጥቃት እንደከፈቱባቸው ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትግራይ ኃይሎች የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ጦር በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በኩል አድያቦ አካባቢ ዛሬ ነሐሴ 26/2014 ዓ.ም. ማለዳ በአራት አቅጣጫ ጥቃት እንደከፈቱባቸው ተናገሩ።
የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ጥምር ኃይሎቹ ከፈቱ ያሏቸውን የአራት አቅጣጫ ጥቃቶች በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
ከፍቅያ ገብረ እስከ አደመይቲ፣ ከሰላሞ እስከ ሽራሮ፣ ከጎቦ ፅንዓት ወደ እርዲ ማቲዎስና አዲ አሰር ጥቃት እንደተከፈተባቸው እንዲሁም አዲ ጎሹ በከባድ መሳሪያ ጥቃት እየተፈጸመበት ነው ብለዋል።
ይህንን ክስ በተመለከተ ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ በኩል የተባለ ነገር የሌለ ሲሆን፣ ከገለልተኛ ወገን ለማጣራትም ባለው የግንኙነት መስመሮች መቋረጥ ምክንያት አዳጋች ነው።
አቶ ጌታቸው በዚሁ የትዊተር መልዕክታቸው ላይ ጨምረውም የትግራይ ኃይሎች ተከፈተባቸው የተባለውን ጥቃቶች እየተከላከሉ ነው ብለዋል።
ትናንት ረቡዕ የኢትዮጵያ መንግሥት አገሪቱ ከጎረቤት ሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ምዕራባዊ ክፍል አካካቢን ጨምሮ “የትግራይ ኃይሎች ጦርነቱን ወደ ተለያዩ ግንባሮች እያስፋፉ ነው” ሲል ከስሶ ነበር።
ረቡዕ ነሐሴ 25/2014ዓ ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ባወጣው መግለጫ የትግራይ ኃይሎች “አዳዲስ የጦርነት ግንባሮች በምዕራብ በኩል የከፈቱት በቆቦ በኩል የተከፈተው ጥቃት በዕቅዳቸው መሰረት ስላልተሳካ ነው” ብሏል።
ይህንንም አስመልክቶ አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገፃቸው በሰጡት ምላሽ የትግራይ ኃይሎች በሰቆጣ፣ በሃምዳይት እና ደደቢትን ጨምሮ በተለያዩ ግንባሮች ጥቃት ከፍተዋል መባሉን “ታሪክ እየተፈጠረ ነው” ብለውታል።
በተጨማሪም ከሰሞኑ አቶ ጌታቸው ረዳ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ጎረቤት ኤርትራ “በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን” በመላክ “ግጭቱን የበለጠ ዓለም አቀፋዊ የማድረግ ፍላጎት አለው” ሲሉ ከሰዋል።
በሽረ ከተማ የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኛ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ከአካባቢው የመጡ አሽከርካሪዎች ረቡዕ እለት ድንበር ተሻግረው የተኩስ ልውውጥ መደረጉን እንዲሁም በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ሽራሮ ከተማ ሐሙስ ከ10፡ 30 ጥዋት ጀምሮ የከባድ መሳሪያ ድብደባ ተጀምሯል ብለዋል።
ከጦር ግንባር ጋር ግንኙነት ያላቸውና በጎንደር የሚሊሻ አመራር በሽራሮ አካባቢ የትግራይ ኃይሎች ላይ ያነጣጠረ “የከባድ መሳሪያ ጥቃት” እያደረሱባቸው እንደሆነ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ጦር ከትግራይ ኃይሎች ጋር በትናንትናው ዕለት ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን የገለጹት ሚሊሻው ከመንግሥት በኩል የቆሰሉ ወታደሮች በሁመራ በህክምና ላይ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ሆስፒታሉ ሲቪል ታማሚዎችን እንዲያስወጣም ትዕዛዝ ተላልፎለታል ሲሉም ለሮይተርሰ ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና ያገረሸው ጦርነት ከፍተኛ ስጋት እንዳጨረባት አሜሪካ ገልጻለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ዛሬ ነሐሴ 26/2014 ዓ.ም. ባወጡት በትዊተር መልዕክታቸው ጠይዋል።
ተፋላሚ ወገኖቹ ግጭቱን በዘላቂነት ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ኃላፊው “ጦርነቱ እንደገና መቀስቀሱ እና አደጋ ላይ የሚጥለው የሰው ሕይወት በእጅጉ ያሳስበናል” ብለዋል።
ዘጠኝ ቀናትን ባስቆጠረው ባገረሸው ጦርነት የሰሜን ወሎ ከተማዋ ቆቦ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የምትገኝ ሲሆን፣ በሌሎች ግንባሮችም ጦርነቶች ተፋፍመዋል።
መከላከያ “የሕዝብ ፍጅትን” ለማስወገድ ከተማውን እንደለቀቀ የገለጸ ሲሆን የትግራይ ኃይሎች ደግሞ “በፀረ-ማጥቃት” ዘመቻ ተቆጣጥረናል ብለዋል።
ለአምስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት ነሐሴ 18/2014 እንደገና የተቀሰቀሰ ሲሆን ወደ ከፋ ደም አፋሳሽ ግጭት እንዳይገባ ስጋት ፈጥሯል።
ግጭቱን በመጀመር አንደኛው ወገን ሌላኛውን እየከሰሰ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች ግጭቱን አቁመው ለድርድር እንዲቀመጡ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት የአስር ሺዎችን ሕይወት በመቅጠፍ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ አድርሷል።
በሁለቱም ወገኖች በኩል የሰብአዊ ተኩስ አቁም አዋጅ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ጦርነቱ ጋብ ቢልም በትግራይ ያለው የምግብና ነዳጅ ዕጥረት እንዲሁም ስልክ፣ ውሃ፣ መብራት፣ ባንክ የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች ተቋርጠው መቀጠላቸው ሕዝቡን ለፈተና እንዳረጉት ነዋሪዎችና የረድዔት ድርጅቶች ይገልጻሉ።
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የርስ በርስ ጦርነት በድርድር ለመቋጨት የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጥረት እያደረጉ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው።
ሁለቱም ወገኖች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውና ተደራዳሪ ኮሚቴም ማዋቀራቸውን ቢገልጹም በአሁኑ ወቅት የርስ በርስ ጦርነቱ ማገርሸቱ የተባለውን የሰላም ሂደት አደጋ ላይ ጥሎታል።












