መንግሥት የትግራይ ኃይሎች ወልቃይትን ጨምሮ በተጨማሪ ግንባሮች ጦርነት ከፍተዋል ሲል ከሰሰ

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ምዕራባዊ አካባቢን ጨምሮ የትግራይ ኃይሎች ጦርነቱን ወደ ተለያዩ ግንባሮች እያስፋፉ ነው ሲል ኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሰ።
ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 25/2014 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ባወጣው መግለጫ ላይ የትግራይ ኃይሎች አዳዲስ የጦርነት ግንባሮች በምዕራብ በኩል የከፈቱት በምሥራቅ በኩል በቆቦ አካባቢ የከፈቱት ጥቃት እንዳቀዱት ስላልተሳካ ነው ብሏል።
የትግራይ ኃይሎች ጦርነት ከፍተውበታል ከተባሉት አካባቢዎች መካከል አንዱ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳበት የምዕራብ ትግራይ/ ወልቃይት ጠገዴ አካባቢ ነው።
ይህ አካባቢ ከጦርነቱ መቀስቀስ በፊት ምዕራብ ትግራይ ተብሎ በትግራይ ክልል ሥር የነበረ ሲሆን፤ ከጦርነቱ በኋላ ግን በአማራ ኃይሎች ይዞታ ሥር ገብቶ ይገኛል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ “ያለ ጦርነት መኖር የማይችለው ህወሓት በዋግ፣ በወልቃይት አቅጣጫ እና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ ከፍቷል” ብሏል።
በተጨማሪ ግንባሮች ጦርነት መከፈቱን በተመለከተ የትግራይ ኃይሎች እስካሁን ያሉት ነገር ባይኖርም፤ ዛሬ ጥዋት የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በርካታ ወታደሮችን ወደ ጎረቤት “ኤርትራ በመላክ ግጭቱን የበለጠ ዓለም አቀፍ” እያደረገው ነው ሲሉ ከሰዋል።
ቢቢሲ ያነጋገረው የሁመራ ከተማ ነዋሪ ከዛሬ ረቡዕ ንጋት ጀምሮ በሱዳን አቅጣጫ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበረ ተናግሯል።
የአማራ ኃይሎች ወልቃይት ጠገዴ፤ የትግራይ ኃይሎች ደግሞ ምዕራብ ትግራይ ብለው በሚጠሩት አካባቢ ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች የተደራጀ ኃይላቸውን አስቀምጠው ተፋጠው እንደሚገኙ ይታመናል።
የፌደራሉ መንግሥት ተከፍቶብኛል ባላቸው ተጨማሪ ጦር ግንባሮች “የመከላከያ ሠራዊት በተሟላ ዝግጅትና በጽኑ ቁመና እየተከላከለ ይገኛል” ብሏል በመግለጫው።
ቢቢሲ ከሁለቱም ወገን የቀረቡ ክሶችን በገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ ያልቻለ ሲሆን ፣ ነገር ግን ይህ ሁኔታ ባለፈው ሳምንት ተቀስቅሶ ለወራት የቆየውን የተኩስ አቁም ያፈረሰው ጦርነት የበለጠ እየተስፋፋ መሆኑን ያመለክታል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ለወራት ከዘለቀ ውጥረት በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያው የርስ በርስ ጦርነት ለሦስተኛ ዙር ዳግም መቀስቀሱ የተሰማው የትግራይ ኃይሎች ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ንጋት 11 ሰዓት ላይ ጥቃት ተከፍቶብኛል ካሉ በኋላ ነው።
የፌደራሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ደግሞ ጦርነቱን የጀመረው ህወሓት ነው በማለት የትግራይ ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጓል።
የርስ በርስ ጦርነቱ ባለፉት 7 ቀናት በምሥራቅ አማራ ከትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆኑ የሰሜን ወሎ ዞን እና በአፋር ክልል አካባቢዎች ተወስኖ የቆየ ሲሆን፤ በተደረጉ ውጊያዎች የትግራይ ኃይሎች የቆቦ ከተማን ተቆጣጥረዋል።
የፌደራሉ መንግሥት ‘የከተማ ውስጥ ውጊያ ላለማድረግና የህዝብ ፍጅትን ለማስወገድ’ ሲል ቆቦን ለቅቆ መውጣቱን ቀደም ሲል መግለጹ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት ዳግም ማገርሸትን ተከትሎ ተፋላሚ ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች ተቋማት እና አገራት ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ይህ የፌደራሉ መንግሥት በተጨማሪ አቅጣጫዎች ጦርነት ተከፍቶብኛል ማለቱም፤ ጦርነቱ ከአዋሳኝ የሰሜን ወሎ ዞኖች ባለፈ ወደ ምዕራብ ትግራይ እና ሱዳን ዳንበር አቅጣጫ መስፋፋቱን ያመላከተ ሆኗል።
“የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አቅጣጫዎች የተከፈቱበትን ጥቃቶች በጽናት እየተከላከለ አሁንም ለሰላም አማራጮች የዘረጋቸውን እጆች ዛሬም ድረስ አላጠፈም” ብሏል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ነሐሴ 25/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ
በተጨማሪም የፌደራሉ መንግሥት "የትግራይ ኃይሎች በምሥራቅ አማራ በቆቦና አካባቢው የከፈቱት ወረራ ጠንካራ መከላከል ስላጋጠማቸው ባሰቡት ልክ አልሄደም "ብሏል።
በመንግሥት እና በትግራይ አመራሮች መካከል ይደረጋል ተብሎ ለነበረው ድርድር እንቅፋት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል የአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ የሚለው የትግራይ ክልል ደግሞ ምዕራብ ትግራይ የሚለው አካባቢ ወቅታዊ ሁኔታ ቀዳሚው እንደሆነ ይነገራል።
የትግራይ መሪዎች ንግግር ከመጀመሩ በፊት በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የሚገኘው አካባቢ ወደ ትግራይ ወደቀደመበት ክልል እንዲመለስ ሲጠይቁ፣ በአማራ በኩል ግን አካባቢው ህወሓት የአገሪቱ ሥልጣን ላይ በቆየበት ወቅት ያላግባብ ወደ ትግራይ የተካተተ ነው በማለት ጥያቄውን አይቀበሉትም።












