ተመትቶ ወድቋል በተባለው አውሮፕላን ጉዳይ ሱዳን የኢትዮጵያን አምባሳደር ጠርታ አናገረች

የፎቶው ባለመብት, ETHIOPIAN EMBASSY - SUDAN
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአገሪቱን የአየር ክልል ጥሶ ገብቷል ያለውን የጦር አውሮፕላን መትቶ መጣሉን ከገለጸ ከሳምንት በኋላ ሱዳን በካርቱም የሚገኙትን የኢትዮጵያን አምባሳደር ጠርታ አነጋገረች።
ከፍተኛ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ አንቶኖቭ 26 አውሮፕላን በሱዳን በኩል የአገሪቱን የአየር ክልል ጥሶ ገብቷል ብለው ነበር።
በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደርም ከሱዳን ተሻግሮ የኢትዮጵያ የአየር ክልልን ጥሶ የገባው አውሮፕላን ተመትቶ መውደቁን በመግለጽ ነሐሴ 23/2014 ዓ.ም. መግለጫ መስጠታቸውን መንግሥታዊው የዜና ወኪል ሱና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ጉዳዩን በሚመለከት በአምባሳደር ይበልጣል አእምሮ መግለጫ ደስተኛ ያልሆነው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደሩን ጠርቶ፤ የሰጡን አስተያየት እንዲያስባብሉ ተጠይቀዋል ብሏል የሱዳን ዜና ወኪል።
የሱዳን የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ፋደለ አብዱላህ ፋደለ የኢትዮጵያው አምባሳደር ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አገራቸው ሱዳንን እንዳላስደሰተ ግልጽ አድርገውላቸዋል ብሏል - ሱና።
የአገሪቱ መከላከያ ኃይል አንቶኖቭ 26 የተባለው ሶቪዬት ሰራሽ የጦር አውሮፕላን ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም. ምሽት አራት ሰዓት በሱዳን በኩል የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሶ ሊገባ ሲል ተመትቶ መውደቁን መግለጹ ይታወሳል።
አውሮፕላኑ ለህወሓት ኃይሎች የጦር መሳሪያ ሊያቀብል የነበረ እንደሆነ በአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ለልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የጦር አውሮፕላኑ ባለቤት የትኛው አገር እንደሆነ በስም ባይጠቅስም፤ “ህወሓትን በመደገፍ ላይ የሚገኙ ታሪካዊ ጠላቶች ንብረት እንደሆነ የሚታመን አውሮፕላን” ነው ብሏል።
ይህ የጦር አውሮፕላን ተመትቶ ወድቋል መባሉን ሱዳን እና የትግራይ ኃይሎች ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል።
አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ ለሱዳን መገናኛ ብዙኃን ሰጥተዋል በተባለው መግለጫ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እንዳለው፤ ከሱዳን የተሻገረ የጦር አውሮፕላን የጦር መሳሪያ ጭኖ ለትግራይ ኃይሎች ሊያደርስ ሲል ተምትቷል ማለታቸውን የሱዳን ዜና አገለግሎት ዘግቧል።
የሱዳን የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ፋደለ አብዱላህ ፋደለ፤ አምባሳደሩ የሰጡት “መሠረት ቢስ ክስ” ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚሹት ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳደራል ሲሉ ለአምባሳደር ይበልጣል አእምሮ ተናግረዋል ብሏል ሱና።
ፈቃድ ሳያገኝ የኢትዮጵያ ድንበርን ተሻግሮ በመግባቱ ተመትቶ መውደቁ ከተነገረ በኋላ፣ ተመሳሳይ በረራዎች ወደ ትግራይ ሲደረጉ መቆየታቸው የተለያዩ ወገኖች እየገለጹ ነው።
ያለፈው ሳምንት ክስተት ይፋ ከመደረጉ ከቀናት በፊት አዲስ አበባ ላይ ከወጣቶች ጋር ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከየት እንደሚነሱ ባይገልጹም ድብቅ በረራዎች ወደ ትግራይ ሲደረጉ እንደነበረ መንግሥት እንደሚያውቅ መናገራቸውን ብሔራዊው ቴሌቪዥን ዘግቧል።












