“ጦር መሳሪያ ጭኖ ትግራይ ሊገባ የነበረ አውሮፕላን ተመትቶ ወደቀ” መንግሥት

የፎቶው ባለመብት, ENDF/FB
በሱዳን በኩል የጦር መሳሪያዎችን ጭኖ ለህወሓት ሊያደርስ ነበር የተባለ አውሮፕላን በኢትዮጵያ የአየር ክልል ውስጥ ተመትቶ መውደቁን መንግሥት ገለጸ።
አውሮፕላኑ ተመትቶ የወደቀው በትናንትናው ዕለት ሌሊት ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም. ምሽት አራት ሰዓት ላይ መሆኑን በአገር መከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ መድረሻውን የትግራይ ክልል ዋና ከተማ በማድረግ “ህወሓትን በመደገፍ ላይ የሚገኙ ታሪካዊ ጠላቶች ንብረት እንደሆነ የሚታመን አውሮፕላን” በአገሪቱ አየር ኃይል መመታቱን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በትዊተር ገጻቸው “የኢትዮጵያን መዳከም የሚፈልጉ” ያሏቸው "ጠላቶች ንብረት የሆነና የጦር መሳሪያ የጫነ አውሮፕላን መመታቱን አስፍረዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው እና የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አውሮፕላኑ በትክክል ከየትኛው አገር እንደሆነ በግልጽ ያሉት ነገር የለም።
ሜጀር ጀኔራሉ ተስፋዬ አያሌው ለኢዜአ እንደተናገሩት አውሮፕላኑ የተመታው በሱዳን አድርጎ የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሶ በሁመራ በኩል ወደ ትግራይ ሊያልፍ መሆኑን ቢገልጹም፣ ሬድዋን በበኩላቸው አውሮፕላን መሳሪያ ጭኖ መቀለ ሲያራግፍ መሆኑን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
ተመትቶ ወድቋል ስለተባለው አውሮፕላን በተመለከተ በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኩል የተባለውን በተመለከተ ከገለልተኛ ወገን የተረጋገጠ ነገር የለም።
ይህንን አስመልክቶ የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ “አውሮፕላኖች ወደ ትግራይ የጦር መሳሪያ ጭነው መሄዳቸውንና አንደኛው በአየር ኃይላቸው ተመትቶ መውደቁን ታሪክ እየፈጠሩ ነው። ይህ ፍጹም ውሸት ነው” ብለዋል በዛሬው ዕለት ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት።
አውሮፕላኑ ለህወሓት ኃይሎች የጦር መሳሪያ ሊያቀብል የነበረ እንደሆነ የገለጹት ጄነራሉ ተስፋዬ፣ ወደ ኢትዮጵያ አየር ክልል ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም. “ሌሊት አራት ሰዓት” ላይ በአገሪቱ አየር ኃይል ተመትቶ መውደቁን ከመግለጽ ውጪ ስለደረሰ ጉዳት እና ሌሎች ተጨማሪ ዝርዝሮችን አልገለጹም።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ለስድስት ወራት ያህል ጋብ ብሎ የነበረው በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራሉ ሠራዊት መካከል የሚደረገው ጦርነት መልሶ ማገርሸቱን ሁለቱም ወገኖች ዛሬ ባወጡት መግለጫ አመልክተዋል።
የሰላም ድርድር ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቅበት ጊዜ የትግራይ እና የአማራ ክልሎች በሚወሰኑባቸው ምሥራቃዊ አካባቢዎች ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም. ሌሊት 11 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ውጊያ መጀመሩ ተገልጿል።
መንግሥትም የትግራይ ኃይሎች አንዳቸው አንዳቸውን ጦርነቱን በመቀስቀስ የተካሰሱ ሲሆን፣ አስካሁን የደረሰ ጉዳትም ሆነ ሌሎች ስለግጭቱ ከገለልተኛ ወገን የወጣ መረጃ የለም።
ባለፉት ሳምንታት የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ አመራሮች ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን ጦርነት በድርድር ለመቋጨት ፍላጎት እንዳላቸውና ለዚህም እየተዘጋጁ መሆናቸው ሲነገር ቆይቷል።
ነገር ግን አንደኛው ወገን ሌላኛውን ለጦርነት እየተዘጋጀ ነው በሚል ሲካሰሱ የቆዩ ሲሆን፣ ህወሓት ባለፈው ሳምንት የመንግሥት ኃይሎች የከባድ መሳሪያ ጥቃት ፈጽመውብኛል ሲል ከሶ፣ ለወራት የቆየው የሰብአዊ እርዳታ ተኩስ አቁም መጣሱን አመልክቶ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ተፈጸመ የተባለው ጥቃት ሐሰት መሆኑን በማስተባበል፣ ህወሓት ሊካሄድ ከታሰበው የሰላም ንግግር ለማፈንገጥ ሰበብ እያቀረበ ነው ሲል ከሶ ነበር።
በጥምት ወር ማብቂያ 2013 ዓ.ም. ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው የእርስ በርስ ጦርነት ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ማስከተሉ ይታወቃል።
ከስድስት ወራት በላይ አልፎ አልፎ ከሚከሰቱ ግጭቶች ባሻገር በህወሓት ኃይሎች እና በኢትዮጵያ ሠራዊት መካከል ይህ ነው የሚባል ከባድ ጦርነት ሳይካሄድ ቆይቷል።
ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ ወገኖች ሁለቱ ኃይሎች ጦርነቱን በሰላማዊ ንግግር እንዲቋጩ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የአፍሪካኅብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እንዲሁምሌሎች አገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በመንግሥት እና በህወሓት መካከል በአስቸኳይ ድርድር አካሂደው ሰላም እንዲያወርዱ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በተለይ የአፍሪካ ሕብረት የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን በመወከል ለወራት መቀለ እና አዲስ አበባ እየተመላለሱ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
መንግሥትለድርድሩ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቅሮ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት እንዲካሄድ እንደሚፈልግ የገለጸ ሲሆን የትግራይ አመራሮች ደግሞ ተደራዳሪዎቹን መሰየሙን አመልክቶ የኬንያው ፕሬዝዳንት አሸማጋይ እንዲሆኑ እንሚፈልግ ገልጿል።
ነገርግን ሁለቱም ወገኖች ለድርድር ፍላጎት እንዳለቸው ይግለጹ እንጂ እስካሁን ውይይት ስለመጀመሩ ወይም ወደዚያው የሚያመራ ተጨባጭ እርምጃ አልታየም።












