በኮንጎ ከውጊያ የሸሹ 25 የሠራዊት አባላት ሞት ተፈረደባቸው

ሞት ከተፈረደባቸው ወታደሮች መካከል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሞት ከተፈረደባቸው ወታደሮች መካከል

ከውጊያ የሸሹ 25 የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሠራዊት አባላት የሞት ቅጣት ተፈረደባቸው።

ወታደሮቹ የአገሪቱ ሠራዊት ኤም23 ከተባለው ታጣቂ ቡድን ጋር እየተዋጋ ሳለ መሸሻቸው ተገልጿል።

ወታደራዊ ፍርድ ቤት የቀረቡት ወታደሮች ከግዳጅ ከሸሹ በኋላ በመንገዳቸው ካገኙት መንደር ዘረፋ ፈጽመዋል ሲል ተጨማሪ ክስ አቅርቦባቸዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት የአገሪቱ መንግሥት የሞት ቅጣትን ተግባራዊ ማድረግ የሚከለክለውን ሕግ በጊዜያዊነት አንስቷል። የአገሪቱ ፍትሕ ሚኒስቴር በጦሩ ውስጥ ያሉትን “ከሃዲዎች” ለመቅጣት ሲባል ከ20 ዓመታት በኋላ የሞት ቅጣት ተግባራዊ እንዲደረግ አዟል።

የወታደሮቹ ጠበቃ በወታደራዊ ፍርድ ቤት የተላለፈውን ውሳኔ ለመቀልበስ ይግባኝ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል።

በወታደራዊ ፍርድ ቤት ከቀረቡት 25 ሰዎች በተጨማሪ አንድ ወታደር የ10 ዓመት እስር ሲፈረድበት ሌላ ወታደር በነጻ ተለቋል።

ከባሎቻቸው የተዘረፈ ንብረት ተቀብለዋል የተባሉ ሦስት ሴቶች እንዲሁ በነጻ ተሰናብተዋል።

ወታደራዊ ፍርድ ቤት የአገሪቱ ሠራዊት አባላት ላይ ሞት ሲፈርድ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ኅዳር ወር 2016 ዓ.ም. ስምነት ወታደሮች ከአውደ ውጊያ “በመሸሸ” እንዲሁም “በድፍረት ባለመዋጋት” በሞት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል። ወታደሮቹ ይግባኝ ጠይቀው ጉዳያቸው በወታደራዊ ፍርድ ቤት እየታየ ነው።

ኤም23 የተባለው ርህራሄ የሌለው አማጺ ቡድን ባለፉት ቀናት በአገሪቱ ጦር ላይ የበላይነትን በመጎናጸፍ ኪቩ በተባለችው ሰሜናዊ ግዛት በርካታ አነስተኛ ከተሞችን ተቆጣጥሯል።

የዲ አር ኮንጎ ጎረቤት የሆነችው ሩዋንዳ ይህን አማጺ ቡድን ትደግፋለች በሚል ክስ ይቀርብበታል። የኪጋሊ መንግሥት ግን ከቡድኑ ጋር ግንኙነት የለኝም ይላል።

በኪቩ ባለፉት ሳምንታት ከ150ሺህ በላይ ነዋሪዎች ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል። የተባበሩት መንግሥታት በኪቩ በአጠቃላይ 2.8 ሚሊዮኝ ሕዝብ ተፈናቅሏል ይላል።

የኮንጎ ሠራዊት ከኤም23 እና በአገሪቱ ምስራቃዊ ግዛት ከሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ጋር ሲዋጋ ቆይቷል። ይሁን እንጂ የአገሪቱ ጦር ወታደራዊ ስነ-ምግባር የሌላው እና ሠርዓት አለበኛ ነው ይባላል።

የሠራዊቱ አባላት የሚከፈላቸው ክፍያ አነስተኛ መሆን እንዲሁም የጦር መሳሪያ አቅርቦቱ ደካማ መሆኑን ይገልጻሉ።

በሌላ በኩል የኤም 23 ተዋጊዎች በኃይል የታጠቁ እና ወታደራዊ ዲሲፕሊን ያላቸው ናቸው ይባላል።

ታጣቂዎቹ በምስራቅ ኮንጎ የሚገኙት የቱትሲ ማኅብረሰብ ከሚደርስባቸው መገለል ለመጠበቅ ሲሉ እአአ 2012 ጀምሮ በአካባቢው የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል።