ኪር ስታርመር ቀጣዩ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ

የሌበር ፓርቲ መሪ ሰር ኪር ስታርመር የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ምርጫን በማሸነፍ ቀጣዩ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ።
ስታርመር ለደጋፊዎቻቸው “አሳክተነዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በበኩላቸው ምርጫውን ሌበር ፓርቲ ማሸነፉን አምነው ከጽህፈት ቤታቸው ፊት ለፊት የመጨረሻ ንግግራቸውን አድርገዋል።
በንግግራቸው "የሕዝቡን ቁጣ ሰምቻለሁ" ካሉ በኋላ ለአገሪቱ ንጉሥ የመልቀቂያ ደብዳቤያቸውን እንደሚያስገቡ ተናግረዋል።
“ለዚህ ሥራ ያለኝን ሁሉ ሰጥቻለሁ። ይሁን እንጂ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት መለወጥ እንዳለበት ግልጽ የሆነ መልዕክት አስተላልፋችኋል” ያሉት ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የሚተካቸው ሲገኝ ከፓርቲ መሪነታቸውም እንደሙለቁ ተናግረዋል።
የወግ አጥባቂው (ኮንሰርቫቲቭ) ፓርቲ ከአጠቃላይ 650 ወንበር በታሪኩ አነስተኛ የሆነ 121 ወንበር ብቻ አግኝቷል።
ሌበር ፓርቲ በበኩሉ 412 የምክር ቤቱ ወንበሮችን በማግኘት በከፍተኛ አብላጫ ምርጫውን አሸንፏል።
የወግ አጥባቂ ፓርቲ አባል ሆነው የምክር ቤት ወንበራቸውን ካጡት መካከል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ግራንት ሻፕስ ይገኙበታል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ምርጫውን በሰፊ ልዩነት ያሸነፈው የሌበር ፓርቲ መሪ ስታርመር “ለውጥ አሁን ይጀምራል” ካሉ በኋላ ፓርቲያቸው ድል መጎናጸፉን “አስደሳች ስሜት አለው” ሲሉ ተናግረዋል።
የተሸናፊው ወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ሪሺ ሱናክ “ሌበር ፓርቲ ይህን አጠቃላይ ምርጫ አሸንፏል” ያሉ ሲሆን፣ ፓርቲያቸው ለገጠመው ሽንፈት “ሙሉ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ለስታርመር ደውለው እንኳን ደስ ያልዎት ማለታቸውንም ተናግረዋል።
የቀድሞ የሌበር ፓርቲ መሪ ጄሬሚ ኮርቤይ በግል ተወዳድረው የፓርላማ ወንበር አሸነፈዋል።
በዚህ ምርጫ ተሳታፊ የነበሩት ሌላኛው ፖለቲከኛ የሪፎርም ዩኬ መሪ ናይጀል ፋራጅ በስምተኛ ሙከራቸው የፓርላማ ወንበር ማሸነፍ ችለዋል።
ፓርቲው እስካሁን አራት ወንበሮችን ማሸነፉ ተረጋግጧል።
በዚህ ምርጫ ሳይጠበቅ ብዙ ወንበር ያጣው የስኮቲሸ ናሽናል ፓርቲ ነው። ኤስኤንፒ የሚኖረው የምክር ቤት ወንበር ከስምንት እንደማይዘል ተገምቷል።
በስኮትላንድ ጭምር ሌበር ፓርቲ የበላይነትን ይዟል።
ወግ አጥባቂው ፓርቲ ዩናይትድ ኪንግደምን ላለፉት 14 ዓመታት ሲያስተዳድር ቆይቷል።
እስካሁን ባለው ግምት ከአጠቃላይ 650 የምክር ቤት ወንበር ሌበር ፓርቲ 412 ወንበር ማሸነፉ ተረጋግጧል።
ስታርመር ባለፉት ሁለት ዓመታት አራተኛው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ።












