ማኬንዚ፡ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ወሮበላ እና ባንክ ዘራፊ፤ የዛሬው የአገሪቱ ስፖርት ሚኒስትር

ጋይተን ማኬንዚ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጋይተን ማኬንዚ

በቅርቡ ደቡብ አፍሪካ ጋይተን ማኬንዚን የስፖርት፣ የጥበብ እና የባህል ሚኒስትር አድርጋ ሾማለች።

ጋይተን በአንድ ወቅት ወሮበላ እና የባንክ ዘራፊ ነበሩ።

በወሮበላነት ዘመናቸው ለዓመታት እስር ቤት የቆዩት ጋይተን፣ ኋላም የምሽት ክበብ ባለቤት ሆነው ከፍተኛ ገንዘብ አፍርተዋል። ከዚያም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሥርተው አሁኑ በሚኒስትርነት ተሾመዋል።

ደቡብ አፍሪካን በበላይነት ለአስርት ዓመታት የመራው ገዢው ፓርቲ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ብቻውን መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን አብላጫ ድምጽ ካጣ በኋላ በተመሠረተው የመድብለ ፓርቲ መንግሥት ውስጥ ነው ሚኒስትሩ የተሾሙት።

ጋይተን ማኬንዚ ፓትሪየቲክ አሊያንስ (ፒኤ) የተሰኘ ፓርቲ መሪ ናቸው።

በርካታ ትዊቶችን በመለጠፍ የሚታወቁት የ50 ዓመቱ ፖለቲከኛ ሹመታቸውን በተመለከተ የደስታ መግለጫ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የእግር ኳስ ማሊያ ለብሰው ለጨዋታ ዝግጁ በሚመስሉበት ሁኔታ ነው።

የጋይተን ሹመት ለአድናቂዎቻቸው ፓለቲከኛው ያንን ሁሉ ውጣ ውረድ አልፈው ስኬት ላይ መድረሳቸውን የሚያሳይ ነው።

ጋይተን ለመጀመሪያ ጊዜ ባንክ የዘረፉት ገና 16 ዓመት ሳይሞላቸው እንደሆነ ከአንድ የአገር ውስጥ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

ከዚያም ሕይወታቸው ወደተሳሳተ አቅጣጫ አምርቶ በወሮበላነት ድርጊት ውስጥ ይሳተፉ እንደነበር እና ሰባት ዓመታትን በእስር እንዳሳለፉ ገልጸዋል። ከእስር ከተፈቱ በኋላ ግን ሕይወታቸውን ለመቀየር ለራሳቸው ቃል ገቡ።

“ኪሴ ውስጥ ያለችኝ ምናልባት 12 ራንድ (የደቡብ አፍሪካ ገንዘብ) ይሆናል ነገር ግን በጭንቅላቴ ውስጥ ቢሊዮን ራንድ አለኝ። ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚያተኩሩት በሌላቸው ነገር ላይ ነው፤ እንዴት ያንን ማግኘት እንደሚችሉ ብዙም አያስቡትም” ሲሉም በአውሮፓውያኑ 2013 ከኤስኤቢሲ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸው ነበር።

ከፍተኛ ደሞዝ የሚከፈላቸው አነቃቃቂ ንግግሮችን አቅራቢ ሆኑ። ስለ ሕይወታቸው ውጣ ውረድ የሚገልጽ “ኤ ሃስለርስ ባይብል” የሚል መጽሐፍን አሳትመዋል፣ በዚምባብዌ ማዕድን ቁፋሮ እንዲሁም ከእስር ቤት አጋራቸው ኬኒ ኩኔኔ ጋር በደቡብ አፍሪካ የምሽት ክለቦችን ከፍተው በተለያዩ ንግዶች ላይ ተሰማርተውም ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሆኖም ባልተከፈለ የቤት ኪራይ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክንያት በተገባ የሕግ እሰጣገባ ምክንያት የምሽት ክለቦቹ መዘጋታቸው ተዘግቧል።

እሳቸውም በወቅቱ በሌሎች ፕሮጀክቶች እንደተጠመዱ እና በምሸት ክለቦች ላይ ፍላጎት የለኝም ሲሉ ተደምጠዋል። ጋይተን የፖለቲካ ፓርቲያቸውን ፒኤ በአውሮፓውያኑ 2013 ያቋቋሙ ሲሆን፣ ምክትላቸውም የእስር ቤት አጋራቸው ኩኔኔ ሆኑ።

ፓርቲው ከአስር ዓመት በኋላም በዘንድሮው ምርጫ 2 በመቶ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በምዕራብ ኬፕ የአካባቢያዊ አስተዳደር 8 በመቶ ድምጽ ማግኘት ችሏል።

በአብዛኛው የመረጣቸው ማኅበረሰብም የደቡብ አፍሪካ 8 በመቶውን ቁጥር የያዙት ከነጭ እና ከጥቁር የተቀላቀሉት (ከለርድ) የሚባሉት ዜጎች ናቸው።

በምርጫው የተፎካከሩትም “አንፈራም” በሚል የመሪ ቃል ነው።

የምርጫው ውጤት ከታወጀም በኋላ “ሁሉንም ዘሮች የወከለው ፓርቲ ፓርላማ ገብቷል” ሲሉ ፖለቲከኛው ተናግረዋል።

የጋይተንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በድፍረት የተሞላ አካሄድ እንዳላቸው እና ይህም ለወከሉት ማኅበረሰብ ከፍተኛ ትርጉም እንዳለው የፖለቲካ ተንታኙ ካጊሶ ፖኦ ይናገራሉ።

“በርካቶች በእነሱ አስተዳደግ ያለፈ እና ማንነቴ ይህ ነው ብለው ግልጽ አድርገው ለመናገር የማይፈሩ ሰዎችን ያምናሉ። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዙማ እና ትራምፕ እንዲህ ዓይነት አካሄድ አላቸው” ይላሉ ተንታኙ።

ፖለቲከኛው በምርጫው ስኬታማ ያደረጋቸው ሕጋዊ ሰነድ በሌላቸው ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ ዘመቻቸው እንደሆነ ተንታኙ ይናገራሉ። የደቡብ አፍሪካ ታዋቂ ፖለቲከኞችም ሆነ ፓርቲዎች የስደተኞችን ጉዳይ ወደ ጎን ገፋ ቢያደርጉትም እሳቸው ግን ይህንን አላደረጉም።

ፖለቲከኛው ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ ዘመቻቸውን “መጤ ጠል” በሚል አውግዘውታል።

ጋይተን “አባሃምቤ” (ልቀቋቸው) የሚለውን የዙሉ ቋንቋ መፈክር “በመጠቀም ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት የሚሞክሩ ሰዎችን ለማባረር ባለመ መልኩ የዚምባብዌን ድንበር ጎብኝተዋል።

ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2013 ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ዚምባብዌን ጨምሮ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የመጡ ስደተኞችን የደቡብ አፍሪካ ምጣኔ ሀብት መሠረታዊ አካል አድርገው በመግልጽ እና “ችግሩ ያለው በእኛ ጥቁሮች ላይ ነው” ማለታቸውን በማስታወስ በግብዝነት ተችተዋቸዋል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ጥምር መንግሥት ለመመሥረት ድርድር በጀመሩበት ወቅት ፖለቲከኛው ምክትላቸው ስደተኞችን የሚመለከተውን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን እንዲመሩ እንደሚፈልጉ በይፋ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የነበራቸውን የወሮበላነት ሕይወት በመጥቀስ ከፍተኛ ወንጀሎችን ለመከላከል ከሳቸው በላይ ሰው እንደማይኖር በመግለጽ የፖሊስ ሚኒስትር ሆነው እንዲሾሙ ጠይቀው ነበር።

ሆኖም የስፖርት ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ ብዙም ያልተደናገጡ ሲሆን፣ ይፋዊ ባልሆኑ ድርድሮች ይህንን ሹመት እንደጠየቁም ገልጸዋል።

የመኪና ማሽከርከር ትርዒት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የመኪና ማሽከርከር ትርዒት

“ስፖርት የሕጻናትን ሕይወት መቀየሪያ መንገድ መሆን ይችላል። ስፖርተኛ ልጅ ከእነዚህ ወንጀሎች ውጪ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

በአገሪቱ ውስጥ ታዋቂ የሆነውን በክብ ቅርጽ መኪና የማሽከርከር እና አሽከርካሪው ዘሎ የመውጣት ትርዒትን (ካር ስፒኒኒንግ) ታዋቂ ለማድረግ እንደሚሠሩም ቃል ገብተዋል።

ሆኖም በርካታ የጥቁር፣ የሕንድ እና የከለርድ ማኅበረሰብ አባላት በጎዳናዎች ላይ በሚያደርጓቸው ትርዒቶች ምክንያት ከቁጥጥር ውጪ እንደሆኑ እና እንደ አደገኛም እንደሚታዩ የስፖርት ጋዜጠኛ የሆነው ጆን ጎልያድ ያስረዳል።

የመኪና ማሽከርከር ትርዒት የተጀመረው በጨቋኙ የአፓርታይድ ዘመን የወደቁ ጀግኖችን ለማስታወስ እንደሆነ ይነገራል።

እሳቸውም የመኪና ማሽከርከር ትርዒትን ደኅንነቱ በተጠበቀ አካባቢ እንዲካሄድ ለማድረግ እና ወጣቶችን ከወሮበላ ቡድኖች እና ከአደንዛዥ ዕጽ ለመታደግ ቃል ገብተዋል።

ፖለቲከኛው በዌስተርን ኬፕ አስተዳደር በተሰጠ ትዕዛዝ ምርመራ እየተደረገባቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዚህም ወቅት መሾማቸው ጥያቄ አስነስቶባቸዋል።

እስካለፈው ዓመት ድረስ ሴንትራል ካሮ የተሰኘችው ከተማ ከንቲባ የነበሩት ጋይተን፣ ከሁለት ዓመት በፊት የመዋኛ ገንዳዎችን መጠገን እና የተንቀሳቃሽ መጸዳኛ ቤቶችን መተካትን ጨምሮ ሕዝባዊ መሠረተ ልማትን ለማሳካት በተዘጋጀ የእራት ፕሮግራም ላይ የተሰበሰበው 161 ሺህ ዶላር ጋር በተገናኘ ጥያቄ ቀርቦባቸዋል።

ፖለቲከኛው በሚኒስትርነት ከመሾማቸው በፊት የተሰበሰበውን ገንዘብ በተመለከተ ለመርማሪዎች እንዲያሳውቁ ባለፈው ወር ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መስጠቱን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ፓርቲያቸው ይህንን ውሳኔ ስህተት የተሞላበት ሲል የገለጸው ሲሆን፣ ፖለቲከኛውም መልስ ለመስጠት “አካባቢውን እንደሚጎበኙ” በቅርቡ ተናግረዋል። “እውነት ትወጣለች፤ የምደብቀው ነገር የለም። ሐሰት ዕድሜዋ አጭር ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።