አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የ89 ስደተኞች አስከሬን ተገኘ

ስደተኞች አውሮፓ ለመግባት በተጨናነቁ ጀልባዎች ይጓዛሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሞሪታኒያ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች ሰኞ ዕለት በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ተገልብጣ ከነበረች ጀልባ የ89 ስደተኞችን አስከሬን ማግኘታቸውን አስታወቁ።

የአምስት ዓመት ሴት ልጅን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ከሞት ሲተርፉ በርካቶች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።

ከሞት የተረፉ ሰዎች ባሕላዊ የሆነችው የአሳ ማስገሪያ ጀልባ ባለፈው ሳምንት ከሴኔጋል እና ጋምቢያ ድንበር አቅራቢያ 170 ሰዎችን አሳፍራ መነሳቷን ተናግረዋል።

በኋላም ከሞሪታኒያ ደቡብ-ምዕራብ የባህር ዳርቻ ተገልብጣለች።

ሞሪታንያ ከምዕራብ አፍሪካ ወደ አውሮፓ ለመግባት ለሚሞክሩ ስደተኞች ቁልፍ መሸጋገሪያ ሆና ታገለግላለች። ባለፈው ዓመት በሺህዎች የሚቆጠሩ ጀልባዎች መዳረሻቸውን አውሮፓ አድርገው ከአገሪቱ ተነስተዋል።

የአብዛኛዎቹ መድረሻ ደግሞ የስፔን የካናሪ ደሴቶች ነው።

ባለፈው ዓመት ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በደሴቲቷ መድረሳቸውን የስፔን መንግሥት ተናግሯል። ይህ ቁጥር ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ የጨመረ ሆኗል።

ወደ አውሮፓ ለመድረስ ተስፋ የሚያደርጉ ስደተኞች ጀልባዎች ላይ ከአቅም በላይ ተጭነው ይጓዛሉ።

በ2024 የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ብቻ ከአምስት ሺህ በላይ ስደተኞች በባህር ወደ ስፔን ለመድረስ ሲሞክሩ መሞታቸውን የካ-ሚናዶ ፍሮንቴራስ የተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ግምቱን አስቀምጧል።

በሚያዝያ ወር የአውሮፓ ኅብረት ለሞሪታኒያ 210 ሚሊዮን ዩሮ ዕርዳታ የሰጠ ሲሆን 60 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋው ሰነድ አልባ ሆነው ወደ አውሮፓ የሚሰደዱትን ለመከላከል ይውላል።