ቴህራን ወደ ቀደመ ሕይወቷ እየተመለሰች ቢሆንም ነዋሪዎቿ ግን አሁንም ፍርሃት ውስጥ ናቸው

በኢራን ዋና ከተማ መሀል የሚገኘው ካፍቴሪያ በሞቃታማው የበጋ ቀን ቀዝቀዝ የሚያደርጉ መጠጦችን ይሸጣል።
በዚህ ከተማ ውስጥ በጣም ልዩ የሆነ አሜሪካኖ በበረዶ የሚገኝበት ስፍራ ነው። ካፍቴሪያው የሚገኘው ከተዘጋ ረዥም ጊዜ ከሆነው የአሜሪካ ኤምባሲ አጠገብ ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ በ1979 በኢራን አብዮት እና የእገታ ቀውስ ምክንያት ዋሽንግተን ከቴህራን ጋር ያላትን ግንኙነት ካቋረጠችበት ጊዜ አንስቶ ረዥም የአርማታ አጥሩ በፀረ አሜሪካዊ መፈክሮች ተሸፍኗል።
ይህ የኤምባሲ አጥር ሁለቱ አገራት ያሉበትን ግንኙነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
የካፌው ባሪስታ፣አሚር በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል እንደሚፈልግ ይናገራል።
ሌላ ቡና በበረዶ ለደንበኞቹ እያዘጋጀ "የአሜሪካ ማዕቀብ ንግዳችንን ይጎዳል እና በዓለም ዙሪያ ለመጓዝ ያስቸግረናል" ሲል ምክንያቱን ያስረዳል።
በእንጨት ላይ የተቀረፀው "ተረጋጉ እና ቡና ጠጡ!" የሚለው ማስታወቂያ በጉልህ ይታያል።
ሁለት ጠረጴዛዎች ብቻ ናቸው እንግዶች የተቀመጡባቸው።
አንደኛዋ ጥቁር ረጅም ቀሚስ የለበሰች ሲሆን ዓይኖቿ ተሸፍነዋል። ሌላኛዋ ሰማያዊ ጂንስ የለበሰች ሲሆን ረዥም ፀጉሯ ተዘናፍሎ ይታያል።
ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ዘና ብላ ተቃቅፋ ስትታይ የኢራንን ደንብ የጣሰች አትመስልም።
ይህ በዋና ከተማዋ ዛሬን፣ አሁን የሚሆነውን የሚያሳይ፣ የሚመጡት ቀናት ምን እንደያዙ እርግጠኛነት የታጣበት ትዕይንት ነው።

ትንሽ መንገድ በመኪና እንደሄዱ የኢራን መንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ (IRIB) ቅጥር ግቢ ይገኛል።
ከዚህ ግቢ ነው ትናንት ሐሙስ የጠቅላዩ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ የተቀዳ ንግግር የተላለፈው።
"አሜሪካኖች የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክን ገና ከጅምሩ ሲቃወሙ ኖረዋል" ብለዋል በንግግራቸው።
የ86 ዓመቱ አያቶላ "በመሠረቱ፣ ሁሌም አንድ ነገር ነው፣ እጅ እንድንሰጥ ይፈልጋሉ" ብለዋል።
እስራኤል በኢራን ላይ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ የአየር ድብደባ እና የሚሳዔል ጥቃት ፈጽማ የኒውክሌር እና ሚሳዔል ጣቢያዎቿን አጥቅታለች፤ ከፍተኛ የጦር አዛዦቿን እና ሳይንቲስቶቿን ገድላለች።
በዚህ ሁሉ ወቅት አያቶላ አሊ ኻሜኒ በምሽግ ውስጥ ተደብቀው ነበር ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በድንገት የተኩስ አቁም ካወጁ በኋላ ማክሰኞ ዕለት የመጀመሪያው ንግግራቸው ተሰምቷል።
ሰኔ 16 የእስራኤል ቦምብ የቴሌቪዥን ጣቢያውን ሲደበድብ ኃይለኛ እሳት የጣቢያውን ዋና ስቱዲዮ አመድ አደረገው።
አሁንም የሚረብሽ ሽታ ይሸታል። ሁሉም የቴሌቪዥን ቁሳቁሶች ካሜራዎች፣ መብራቶች፣ ትራይፖዶች ኮምፒውተሮች ኮምትርትር ብለው ወድመዋል።
ወለሉ በተሰባበረ መስታወት ተሸፍኗል።
እስራኤል የእስላማዊ ሪፐብሊኩን የፕሮፓጋንዳ ልሳን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሟን በመግለጽ በውስጡ ወታደራዊ ዘመቻ የሚመሩትን ደብቋል ስትል የወነጀለች ሲሆን፣ ጋዜጠኞቹ ግን ውድቅ አድርገውታል።
የደረሰው ውድመት ትዕይንት የኢራን የጨለማ ጊዜ የሚያመለክት ይመስላል።
በእስራኤል የ12 ቀናት ጦርነት የተጎዱ ኢራናውያንን እያከሙ በሚገኙ የከተማዋ ሆስፒታሎችም ይህንኑ ማየት ይቻላል።
አሽራፍ ባርጊ በዋና ነርስነት በምትሠራበት በታሌጋኒ አጠቃላይ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ሆና "እንደገና ጥቃት ይፈጸማል ስል እፈራለሁ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
በዚህ ከተማ ውስጥ ከሚኖሩ ከበርካታ ሰዎች የሚሰማውን ጭንቀት በሚያንፀባርቅ መልኩ "ይህ ጦርነት እንዳበቃ አናምንም" ብላለች።
ሰኔ 23 ቀን እስራኤል በሆስፒታሉ አቅራቢያ የሚገኘው የኤቪን እስር ቤት በቦምብ ስትደበድብ፣ የተጎዱት ወታደሮች እና ሰላማዊ ዜጎች ወደ ነርስ ባርጊ የድንገተኛ ክፍል ነው የመጡት።
"ጉዳቱ በነርስነት በሠራሁባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ካከምኳቸው ሁሉ የከፋ ነበር፤ በ80ዎቹ የኢራን እና የኢራቅ ጦርነት ወቅት እንኳ ካየሁት የከፋ ነው" ስትል በመረበሽ ውስጥ ሆና ትገልጻለች።
እስራኤል ኢራን አብዛኞቹን የፖለቲካ እስረኞቿን በምታስርበት በዚህ እስር ቤት ላይ ያካሄደችው ድብደባ "ተምሳሌታዊ" ስትል ጠርታዋለች።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ለኢራናውያን "ለነጻነታቸው ተነሱ" በማለት ደጋግመው ያስተላለፉትን መልዕክት የሚያጠናክር ይመስላል።
ሞርቴዛ ከሆስፒታል አልጋው ላይ ሆኖ "እስራኤል ወታደራዊ እና የኒውክሌር ተቋማትን ብቻ ነው የደበደብኩት ትላለች፤ ግን ዓይን ያወጣ ውሸት ነው" ብሏል።
በእስር ቤቱ የትራንስፖርት ክፍል ውስጥ በሥራ ላይ እያለ ሚሳኤሉ ሕንጻውን መታ።
በሁለቱም እጆቹ እና በጀርባው በኩል ያጋጠመውን ጉዳት ለቢቢሲ ጋዜጠኞች አሳይቷል።
በአቅራቢያው ባለው የሕሙማን ክፍል ውስጥ ወታደሮች ተኝተዋል። ቢቢሲ ወደዚያ ክፍል እንዲገባ አልተፈቀደለትም።

በዚህች ሰፊ ከተማ ውስጥ ኢራናውያን ግጭቱ ያደረሰውን ውድመት እየቆጠሩ ነው። የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በእስራኤል የሚሳዔል ድብደባ 627 ሰዎች ሲሞቱ ወደ 5,000 የሚጠጉ ደግሞ ቆስለዋል።
ቴህራን ቀስ በቀስ ወደ መደበኛ ሕይወቷ እየተመለሰች፣ የቀድሞ ገጽታዋ እየመጣ ነው።
መንገዶች እንደ ቀድሞው በመኪኖች መሞላት ጀምረዋል።
የእስራኤልን የቦምብ ድብደባ ሸሽተው ከተማዋን ለቅቀው የወጡ መመለስ ሲጀምሩ ሱቆች ዳግም መከፈት እና በሰው መሞላት ጀምረዋል።
የእስራኤል የ12 ቀናት ወታደራዊ ዘመቻ፣ የአሜሪካ አየር ኃይል በኢራን ዋና ዋና የኒውክሌር ተቋማት ላይ ካደረሰው ጥቃት ጋር ተዳምሮ በርካቶችን ረብሿል።
ሚና "ጥሩ ቀናት አልነበሩም" በማለት መናገር እንደ ጀመረች ወዲያው እንባ ፊቷ ላይ ክልብስ አለ።
"በጣም ልብ የሚሰብር ነው" አለች እያለቀሰች። "የተሻለ ሕይወት እንዲኖረን አጥብቀን ጣርን ነገር ግን ዘንድሮ ምንም ዓይነት ብሩህ ነገር ማየት አልቻልንም።"
በቴህራን በጣም ታዋቂ ከሆኑ ስፍራዎች መካከል በአዛዲ ሕንጻ ላይ ነው የቢቢሲ ባልደረቦችን ያገኘችው።
በሞቃታማው የበጋ ምሽት ብዙ ሕዝብ ወጥቶ የቴህራን ሲምፎኒ ኦርኬስትራ ያዘጋጀውን የሙዚቃ ድግስ እያጣጣመ ነው።
ኦርኬስትራው የአገር ፍቅርን፣ አንድነትን እና ጀግንነትን የሚሰብኩ ሙዚቃዎችን ነው የሚጫወተው።
በጦርነት ፍርሃት ለተናጠችው ከተማ መረጋጋትን ለማምጣት ታስቦ የተዘጋጀ ነበር።
የኢራን የሃይማኖት መሪዎችን የሚደግፉ እና የሚተቹ ተቀላቅለው ስለአገራቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጋራ ለመጨነቅ ተሰባስበዋል።
አሊ ረዛ ለመንግሥት የሚያስተላልፈው መልዕክት እንዳለው ቢቢሲ ሲጠይቀው "ዜጎች የሚሉትን መስማት አለባቸው" ካለ በኋላ "የበለጠ ነፃነት እንፈልጋለን፤ እኔ የምለው ይህን ብቻ ነው።"
የኢራናውያንን ሕይወት ለረጅም ጊዜ ሲመሩ የቆዩ ሕጎች እና ገደቦች ቢኖሩም፣ መሪዎቻቸው ዋሽንግተን እና ሌሎች የሚወስዱትን ቀጣዩን እርምጃ እየጠበቁ የሚሰማቸውን ይናገራሉ።















