ኢራን ለእስራኤል በመሰለል በጠረጠረቻቸው ግለሰቦች ላይ እስሮች እና የሞት ቅጣቶችን ፈጸመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእስራኤል እና በኢራን መካከል ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ የኢራን ባለሥልጣናት ለእስራኤል በመሰለል ጠረጠርናቸው ባሏቸው በርካታ ሰዎች ላይ እስሮችን እና የሞት ቅጣቶችን ፈፀሙ።
ይህ የሆነው ባለሥልጣናት በኢራን የደኅንነት አገልግሎት ላይ "በእስራኤል ወኪሎች ያልተገባ ሰርጎ ገብነት ተፈፅሟል" ካሉ በኋላ ነው።
ባለሥልጣናቱ በግጭቱ ወቅት በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ላይ ለተፈፀሙ ተከታታይ ግድያዎች ለእስራኤል ተላልፈው የተሰጡ መረጃዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል ብለው ያምናሉ።
ይህም የእስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ዘብ ከፍተኛ የጦር አዛዦች እና የኒውክሌር ተመራማሪዎቿ ላይ የተፈፀመውን ግድያ ያካትታል።
ኢራን ለግድያው በአገሪቷ ውስጥ ይሰራሉ ያለቻቸውን የእስራኤል የደኅንነት ወኪሎች ተጠያቂ አድርጋለች።
በእነዚህ ተከታታይ ግድያዎች የተደናገጡት ባለሥልጣናትም "ለብሔራዊ ደኅንነት" በሚል ለውጭ የስለላ ድርጅት ይሰራሉ ብለው የጠረጠሩትን ማንኛውም ግለሰብ ኢላማ እያደረጉ ነው።
ሆኖም ይህ በርካቶችን ዝም ለማሰኘት እና በሕዝቡ ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር የማጥበቂያ ዘዴ ሊሆን እንደሚችል በርካቶች ይሰጋሉ።
ለ12 ቀን በዘለቀው ግጭት የኢራን ባለሥልጣናት ለእስራኤል በመሰለል የተጠረጠሩ ሦስት ግለሰቦችን በሞት ቀጥተዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሱ ከአንድ ቀን በኋላም በተመሳሳይ ክስ ሌሎች ሦስት ግለሰቦች ተገድለዋል።
በመላ አገሪቱ በስለላ የተጠረጠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸውንም ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። የአገሪቷ የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያም በርካታ እስረኞች ከእስራኤል ደኅንነት ጋር ተባብረው መስራታቸውን ሲገልጹ የሚያሳይ ኑዛዜ አስተላልፏል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እና አንቂዎች " ኢራን ለረጅም ጊዜ እያደረገች ያለውን አስገዳጅ ኑዛዜ እና ፍትሃዊ ያልሆነ ፍርድ" በመጥቀስ፣ አሁን ላይ እየተሰሙ ባሉት ነገሮች ላይ ያላቸውን ስጋት እየገለጹ ነው። ተጨማሪ የሞት ቅጣቶች ሊፈፀሙ እንደሚችሉም ስጋቶች አሉ።
የኢራን የደኅንነት ሚኒስቴር፣አገሪቷ ሲአይኤ፣ ሞሳድ እና ኤምአይ6ን ጨምሮ ከምዕራባውያን እና ከእስራኤል የስለላ ሰንሰለት (ኔትወርክ) ጋር እየታገለች እንደሆነ ገልጿል።
ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ፋርስ የዜና ወኪል እንዳለው ከሆነ ከ12 ቀናት በፊት እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከፈፀመች ጀምሮ "የእስራኤል የስለላ ኔትወርክ በአገሪቷ ውስጥ ንቁ ሆኗል"።
በ12ቱ ቀናት ግጭትም የኢራን የደኅንነት እና የፀጥታ ኃይሎች ከኔትወርኩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ከ700 በላይ ሰዎችን ማሰራቸውንም የዜና ወኪሉ ዘግቧል።
ኢራናውያንም ከእስራኤል ጋር በተያያዙ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የስልክ ቁጥራቸው መውጣቱን የሚያሳውቅ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መልዕክት ከአገሪቱ የደኅንነት ሚኒስቴር እንደደረሳቸው ለቢቢሲ የፐርሽያ [ፋርስ] አገልግሎት ተናግረዋል።እነዚህን ገጾች ለቀው እንዲወጡ ካልሆነ ግን ክስ እንደሚጠብቃቸው ተነግሯቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የኢራን መንግሥት ቢቢሲ ፐርሺያን፣ በለንደን ተቀማጭነቱን ያደረገውን ኢራን ኢንተርናሽናል እና ማኖቶ ቴሌቪዥንን ጨምሮ በፋርስ ቋንቋ በሚዘግቡ ሚዲያዎች ውስጥ በሚሰሩ ጋዜጠኞች ላይ ጫናዎችን እያሳደረ ነው።
ኢራን ኢንተርናሽናል እንዳለው በቴህራን የሚገኘው የቴሌቪዥን አቅራቢ ሥራዋን እንድታቆም ጫና ለመፍጠር እናቷ፣ አባቷ እና ወንድሟ በእስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ዘብ ታስረዋል።
አቅራቢዋ በፀጥታ ኃይሎች አማካኝነት ከአባቷ ስልክ እንደተደወለላት እና ሌላ አደጋ ከመከሰቱ በፊት ሥራዋን እንድታቆም እንዳስጠነቀቋትም ገልጿል።
ግጭቱ ከጀመረ አንስቶ በቢቢሲ ፐርሺያ አገልግሎት ጋዜጠኞች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰው ማስፈራሪያም እየከፋ መጥቷል።
በቅርቡ ይህ የደረሰበት ጋዜጠኛ እንዳለው የኢራን የፀጥታ ባለሥልጣናት ቤተሰቦቹን ያነጋገሩ ሲሆን በጦርነት አውድ ውስጥ ቤተሰቦቹን ኢላማ ማድረግ ሕጉ እንደሚፈቅድላቸው ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኞቹን 'ሞሃረብ' ወይም ከፈጣሪው ጋር ጦርነት የገጠመ ሲሉ የገለጿቸው ሲሆን ይህም በኢራን ሕግ መሠረት የሞት ቅጣትን ሊያስከትል ይችላል።
ማኖቶ ቴሌቪዥንም በሠራተኞቹ ቤተሰቦች ላይ የሚደርስ ማስፈራሪያ እና ከጣቢያው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቆሙ ማድረግን ጨምሮ ተመሳሳይ ድርጊቶች እንደተፈፀሙበት ገልጿል።
አንዳንድ የቤተሰብ አባላትንም "የፈጣሪ ጠላት" በማለት በስለላ እንደሚከሰሱ ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል።
እነዚህ ድርጊቶች ድምጽን ለማፈን እና በስደት ላይ የሚገኙ የሚዲያ ባለሙያዎች ለማስፈራራት የተወሰዱ የሰፊ እርምጃዎች አካል እንደሆኑ ተንታኞች ገልጸዋል።
የፀጥታ ኃይሎችም በርካታ የማኅበረሰብ አንቂዎችን ፣ፀሐፊዎችን እና የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ያለምንም ክስ አስረዋል።
ከዚህም ባሻገር በኢራን እንደ አውሮፓውያኑ 2022 " ሴቶች፣ ሕይወት፣ ነጻነት" በሚል በተካሄደው የፀረ መንግሥት ተቃውሞ የተገደሉ ሰዎች የቤተሰብ አባላት መታሰራቸው ተነግሯል።
ይህም እስሮች እየተፈፀሙ ያሉት አሁን ላይ ባሉ የማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ከቀደመው ፀረ - መንግሥት ተቃውሞ ጋር ግንኙነት ባላቸው ላይ መሆኑን ያመለክታል።
በጦርነቱ ወቅት የኢራን መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎትን ያቋረጠ ሲሆን ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላም ሙሉ የኢንተርኔት አግልግሎት አልተመለሰም።
በእንዲህ ዓይነት ቀውሶች በተለይም በመላ አገሪቷ በሚካሄዱ ፀረ መንግሥት ተቃውሞዎች ወቅት የኢንተርኔት አገልግሎትን ውስን ማድረግ በኢራን የተለመደ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ እንደ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራም፣ ኤክስ እና ዩቲዩብ ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች እንዲሁም ሌሎች እንደ ቢቢሲ ፐርሺያ ያሉ የዜና ገጾች በኢራን እንዲዘጉ የተደረጉ ሲሆን ገጾቹን ያለ ቪፒኤን መክፈት አይቻልም።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የፖለቲካ ታዛቢዎችም ይህ ክስተት በ1980ዎቹ በኢራን እና ኢራቅ መካከል ጦርነት ሲካሄድ የኢራን ባለሥልጣናት ፖለቲካዊ ተቃውሞን ለማፈን ከተጠቀሙበት ስልት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢራን ከእስራኤል ጋር ግጭት ውስጥ ከገባች በኋላም ባለሥልጣናት በድጋሜ ወደ የጅምላ እስር፣ የሞት ቅጣት እና ከፍተኛ ጭቆና ሊመለሱ ይችላሉ የሚልም ስጋት አላቸው።
በአውሮፓውያኑ 1988 ያጋጠሙ ክስተቶችም በሺዎች የሚቆጠሩና አብዛኞቹ የተፈረደባቸው የፖለቲካ እስረኞች 'ደዝ ኮሚሽን' በተባለው ተቋም በስውር ችሎትና በአጭር ጊዜ በተላለፈ ፍርድ በሞት መቀጣታቸውን የሰብዓዊ መብት ቡድኖች ገልጸዋል።አብዛኞቹም በማይታወቅ የጅምላ መቃብር ተቀብረዋል።















