የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ ከተደበቁት ሲወጡ በጣም የተለየች አገር ትጠብቃቸዋለች

አገራቸው ከእስራኤል ጋር ትንቅንቅ ላይ በነበረችነበት ጊዜ ለሁለት ሳምንት ኢራን ውስጥ በምስጢራዊ ምሽግ ተቀምጠው የቆዩት የ86 ዓመቱ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ የተኩስ አቁም እድሉን ተጠቅመው ለመውጣት ይፈልጉ ይሆናል።
በእስራኤል እንዳይገደሉ በመፍራት ከሰው ጋር በማይገናኙበት ሁኔታ ከጉድጓድ ውስጥ መደበቃቸው ይታመናል።
የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንኳን ከእሳቸው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳልነበራቸው ግልጽ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የኳታሩ አሚር አሸማጋይ ሆነው የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ምክር ቢጤ ሳይለገሳቸው አልቀረም።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እስራኤል የኢራንን ጠቅላይ መሪ እንዳትገድል ቢነግሯትም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን የመግደሉን ሃሳቡ ከማሰላሰል አልቦዘኑም።
መቼ እንደሆነ ባይታወቅም፣ ከተደበቁበት የሚወጡ ከሆነ ዓይናቸው የሚጋፈጠው ከሞትና የጥፋት መልክዓ ምድር ጋር ነው።
አሁንም በመንግሥት ቲቪ ላይ ብቅ ብለው ጦርነቱን እንዳሸነፉ እንደሚያውጁ ምንም ጥርጥር የለውም።
የጠፋው ስማቸውን፣ የጎደፈ ዝናቸውን ለማደስ ማሴራቸው አይቀርም። ግን አዲስ እውነታዎችን ይጋፈጣሉ፤ ምናልባትም አዲስ ዘመን።
ጦርነቱ አገሪቱን በከፍተኛ ሁኔታ እንድትዳከም አድርጎ እሳቸውን ደግሞ አሳንሶ አልፏል።
ከላይ የሚሰሙ የተቃውሞ ጉርምርምታዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጦርነቱ ወቅት እስራኤል የኢራንን የአየር ክልል በፍጥነት ተቆጣጥራ ወታደራዊ እና የኒውክሌር መሠረተ ልማቷን አጠቃች።
የአብዮታዊ ጥበቃ እና የሠራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች በፍጥነት ተገደሉ።
በጦር ኃይሉ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን አሁንም ግልጽ ያልሆነ እና አከራካሪ ቢሆንም በሠራዊቱ እና በአብዮታዊ የጥበቃ ማዕከሎች እና ተቋሞች ላይ የሚደርሰው ተደጋጋሚ የቦምብ ጥቃት የኢራን ወታደራዊ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆሉን ያሳያል።
ወታደራዊ ኃይሉ ከፍተኛ መጠን ያለው የአገር ሀብት ሲበላ ቆይቷል።
በመቶ ቢሊየን ዶላር የሚገመት ወጪ የወጣባቸው እና አገሪቱን ለሁለት አስርት ዓመታት ለአሜሪካ እና ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች የዳረጓት ግዙፍ የኒውክሌር ተቋማት፤ምንም እንኳን የጉዳቱን መጠን ለመገመት አስቸጋሪ ቢሆንም በአየር ድብደባው ጉዳት ደርሶባቸዋል።
እጅግ በርካታ ኢራናውያን እአአ በ1989 የመሪነቱን መንበር የተቆናጠጡት አያቶላህ ኻሜኒ ኢራንን ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር ግጭት ውስጥ በመክትት በአገሩ እና በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ውድመት አምጥተዋል በሚል ጣታቸውን ይቀስሩባቸዋል።
ብዙ ኢራናውያን የማይደግፉትን፣ እስራኤልን የማጥፋት ርዕዮተ ዓለም በመከተላቸው ይወቅሷቸዋል።
የኒውክሌር መሣርያን መታጠቅ አገዛዙን የማይበገር ያደርገዋል ብለው ማመናቸውን በመጥቀስ እንደ ሞኛ ሞኝ ያዩዋቸዋል።
ማዕቀቦች የኢራንን ኢኮኖሚ አሽመድምዶታል፣ ከፍተኛ ነዳጅ አምራች የነበረችውን አገር የቀድሞ ጥላዋን ለመከተል ወደ ምታትር ድሃ አገር ለውጧታል።
በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሊና ካቲብ "የኢራን አገዛዝ በእንደዚህ ዓይነት ከባድ ጫና ውስጥ ምን ያህል ሊቆይ እንደሚችል መገመት ከባድ ነው፤ ግን ይህ የመጨረሻው መጀመሪያ ይመስላል" ብለዋል።
"በሌላ አነጋገር አሊኻሜኒ የእላማዊ ሪፐብሊክ የመጨረሻው 'የበላይ መሪ' ሊሆኑ ይችላሉ እንደ ማለት ነው።"
ከላይ ከላይ የሚሰሙ የተቃውሞ ማጉረምረሞች ነበሩ።
በጦርነቱ ወቅት አንድ ከፊል ኦፊሴላዊ የኢራን የዜና ወኪል እንደዘገበው አንዳንድ የቀድሞ የአገዛዙ ከፍተኛ ባለስልጣናት መቀመጫቸውን እንደ ቅዱስ ስፍራ በምትታየው የቆም ከተማ ያደረጉት እና በጽሞናቸው የሚታወቁ የሃይማኖት ምሁራን ጣልቃ በመግባት የአመራር ለውጥ እንዲያመጡ ሲማጸኑ ቆይተዋል።
በቅዱስ አንድሪውዝ ዩኒቨርሲቲ የኢራን ጥናት ተቋም መስራች ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አሊ አንሳሪ እንዳሉት "ማሰላሰል ይኖራል" ብለዋል።
"በአመራሩ ውስጥ ከፍተኛ አለመግባባቶች እንዳሉ ግልጽ ነው፣ እና በተራ ሰዎች መካከልም ትልቅ ደስታ ማጣት አለ።"
'ቁጣ እና ተስፋ መቁረጥ ሥር ይሰድዳሉ'

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብዙ ኢራናውያን ለገዥው አካል ባላቸው ጥልቅ ጥላቻ እና አገራቸውን ከጥቃት መከላከል አለባቸው ከሚለው ተቃርኗዊ ስሜቶች ጋር ሲታገሉ ቆይተዋል።
ለአገራቸው አደባባይ የወጡት አገዛዙን ለመከላከል ሳይሆን እርስ በርስ ለመተሳሰብ ነው። ሰፊ የመተሳሰብና መቀራረብም ዘገባዎች ሲወጡ ቆይተዋል።
ከከተማ ውጭ ባሉ መንደሮች የሚኖሩ ሰዎች በየከተሞቻቸው የቦምብ ጥቃት ሸሽተው ለተሰደዱት የአገራቸው ልጆች በሮቻቸው ክፍት ነበሩ።
ባለሱቆች የመሠረታዊ ሸቀጦችን ባነሰ ዋጋ ሽጠዋል፤ ሰዎች የሚፈልጉት ነገር እንዳለ ለመጠየቅ የጎረቤቶቻቸውን በራፎች አንኳኩተዋል።
ነገር ግን እስራኤል ምናልባት በኢራን ውስጥ የአገዛዝ ለውጥ ለማድርግ እንደምትፈልግ ብዙ ሰዎች ያውቃሉ።
የስርዓት ለውጥ ብዙ ኢራናውያን የሚመኙት ነው። ያ የሚመኙት የስርዓት ለውጥ ግን በውጭ ኃይሎች የተነደፈ እና የተደገፈ ነው።
ከዓለማችን ረዥም ዓመት ገዢዎች አንዱ የሆኑት አያቶላህ ኻሜኒ ወደ 40 ዓመታት በሚጠጋው የስልጣን ዘመናቸው በአገሪቱ ውስጥ የሚነሱትን ተቃዋሚዎች በሙሉ ማጥፋት ችለዋል።
የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች እስር ቤት ናቸው አልያም ከአገር ተሰድደዋል። በውጭ አገር ያሉ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ የአገዛዙን ተቃዋሚዎች አንድ የሚያደርግ አቋም መቅረጽ አልቻሉም።
ዕድሉ ከተገኘ በአገር ውስጥ ስልጣን ሊረከብ የሚችል ድርጅት ማቋቋም ላይም ምንም ዓይነት ውጤት አላመጡም።
የአገዛዝ መውደቅ እውን ሊሆን በሚችልበት ያለፉት ሁለት ሳምንታት የጦርነት ጊዜ፤ ጦርነቱ ያለማቋረጥ ከቀጠለ፣ በማግስቱ ሊፈጠር የሚችለው ሁኔታ የተቃዋሚዎች ስልጣን መቆናጠጥ ሳይሆን፣ አገሪቱ ወደ ትርምስና ስርዓት አልበኝነት ማውረድ እንደሆነ ብዙዎች ያምኑ ነበር።
"የኢራን አገዛዝ በአገር ውስጥ በተቃውሞ ይወድቃል ተብሎ አይታሰብም።አገዛዙ በአገር ውስጥ ጠንካራ ሆኖ ይቆያል እና የአገር ውስጥ ጭቆናን ያስፋፋል" ይላሉ ፕሮፌሰር ካቲብ።
ኢራናውያን አሁን በአገዛዙ ላይ ሊወሰድ የሚችለውን ተጨማሪ የኃይል እርምጃ እያሳሰባቸው ነው።
ከእስራኤል ጋር ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ለእስራኤል በመሰለል የተከሰሱ ቢያንስ ስድስት ሰዎች ተገድለዋል።
ባለስልጣናት በዚህ ክስ ወደ 700 የሚጠጉ ሰዎችን ማሰራቸውን ተናግረዋል።
አንዲት ኢራናዊት ለቢቢሲ ፋርሲ ከጦርነቱ ሞትና ውድመት የበለጠ የምትፈራው ቁጣውን በወገኖቹ ላይ የሚያዞር የተዋረደ እና የተጎዳ አገዛዝን እንደሆነ ተናግራለች።
"ገዥው አካል መሠረታዊ እቃዎችን እና አገልግሎቶችን ማቅረብ ካልቻለ ቁጣ እና ብስጭት ይኖራል" ይላሉ ፕሮፌሰር አንሳሪ።
በኢራን ውስጥ ጥቂት ሰዎች ሰኞ ላይ የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት የሚዘልቅ ነው ብለው ያስባሉ፤ ብዙዎች እስራኤል በኢራን ላይ የአየር ኃይል የበላይነት ስላላት ገና ጉዳይዋን አልጨረሰች ብለው ያምናሉ።
የኢራን ባለስቲክ ሚሳኤል ማከማቻዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል ማግኘት ያልቻለቻቸው በመላ አገሪቱ በተራሮች ስር ባሉ ዋሻዎች ውስጥ የተቀመጡት የኢራን ባሊስቲክ ሚሳኤል ማከማቻዎች ከጥፋት ተርፈዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ዋና ኢታማዦር ሹም ኢያል ዛሚር እንዳሉት እስራኤል ኢራን ላይ ጥቃትዋን የከፈተችው "ኢራን ወደ 2,500 የሚጠጉ ከምድር ወይም ከባህር ሊተኮሱ የሚችሉ ሚሳኤሎች" እንዳላት እያወቀች ነው።
ኢራን የተኮሰቻቸው ሚሳኤሎች በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ሞት እና ውድመት አድርሰዋል።
እስራኤል አሁንም በኢራን እጅ ያሉት 1,500 የሚሆኑት ሚሳኤሎች ያስጨንቋታል።
በቴል አቪቭ፣ዋሽንግተን እና ሌሎች የምዕራባውያን አገራት ምንም እንኳን በተደጋጋሚ ብትክድም ኢራን አሁንም የኒውክሌር ቦምብ ለመስራት ልትጣደፍ ትችላለች የሚል ስጋት አለ።
ምንም እንኳን የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ከሞላ ጎደል ወደ ኋላ ተመልሰዋል።
ምናልባትም በእስራኤል እና በአሜሪካ የቦምብ ጥቃት ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ቢደረጉም ኢራን በከፍተኛ ደረጃ የበለጸገውን የዩራኒየም ክምችት ወደ ሚስጥራዊ ቦታ እንዳዛወረችው ተናግራለች።
የ 60 በመቶ የዩራኒየም ክምችትን ወደ 90 በመቶ ማበልጸግ ቀላል እርምጃ ነው፤ ይህ ከሆነ እንደ ባለሙያዎች ገለጻ ለዘጠኝ ቦምቦች በቂ ነው።
ጦርነቱ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ኢራን ሌላ አዲስ ሚስጥራዊ የማበልጸጊያ ተቋም መገንባቷን አስታወቃለች።
የኢራን ፓርላማ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር ያለውን ትብብር በእጅጉ እንዲቀንስ ድምጽ ሰጥቷል።
ይህ አሁንም ይሁንታን ይጠይቃል፣ ነገር ግን ኢራንን ካለፈች ከኒውክሌር አልባ ስምምነት፣ለመውጣት አንድ እርምጃ ብቻ ይቀራታል።
አያቶላህ ኻሜኒ አሁን ለጊዜው አገዛዙ እንደተረፈ እርግጠኛ ሊሆን ይችላሉ።
ነገር ግን በ86 ዓመታቸው እና በሕመም ላይ እያሉ የቀራቸው ጥቂት ጊዜ ሊሆን እንደሚችል ስለሚያውቁ፤ ወደ ሌላ ከፍተኛ የሃይማኖት መሪ ስልጣን በማሸጋገር የአመራር ምክር ቤቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ ይፈልጉ ይሆናል።
ያም ሆነ ይህ፣ እስካሁን ለጠቅላይ መሪው ታማኝ ሆነው የቆዩት የተቀሩት የአብዮታዊ ጥበቃ ከፍተኛ አዛዦች ከጀርባቸው ሥልጣን ለመያዝ ያደቡ ይሆናል።















