በታንዛኒያ አንዲት ሴት በደቦ ስትደፈር የሚያሳየው ቪዲዮ ቁጣን ቀሰቀሰ

ፖሊስ፣ ኅብረተሰቡ ቪዲዮን ከማጋራት እንዲቆጠብ ተማጽኗል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኅብረተሰቡ ቪዲዮን ከማጋራት እንዲቆጠብ ፖሊስ ተማጽኗል

አንዲት ሴት በቡድን ስትደፈር የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ በታንዛኒያ ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ነው።

ተንቀሳቃሽ ምሥሉ በሕዝብ ዘንድ ብስጭትና ቁጣን ፈጥሯል።

ወጣቷን ሴት በደቦ የሚደፍሩት ወታደሮች ስለመሆን አለመሆናቸው የታንዛኒያ ፖሊስ ለጊዜው አስተያየት አልተሰጠም።

ለሕዝብ ቁጣ ምላሽ የሰጠው ፖሊስ ምርመራው ‘በመልካም ሁኔታ’ እየቀጠለ ስለመሆኑ ተናግሯል። ነገር ግን በቁጥጥር ሥር የዋለ ተጠርጣሪ ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም።

በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች 'ተጠቂዋ በደቦ ከተደፈረች በኋላ ወዲያውኑ ሕይወቷ አልፏል' የሚል መረጃ ሲስተጋባ ነበር።

ይሁንና ፖሊስ የሞቷ ዜና ሐሰት ነው፤ ወጣቷ ሴት በመልካም ጤንነት ላይ ትገኛለች ሲል በኤክስ ገጹ ይፋ አድርጓል።

ጨምሮም፣ ታንዛኒያዊያን ልጅቱ ስትደፈር የሚያሳየውን ቪዲዮ ኅብረተሰቡ ለቤተሰቧና ለርሷ ሲል ከማጋራት እንዲቆጠብ ተማጽኗል።

ይህ አንዲት ወጣት ሴት በደቦ ስትደፈር የሚያሳየው ቪዲዮ በኢንተርኔት መሰራጨት የጀመረው ከእሑድ ጀምሮ ነው።

ከዚያ ወዲህ ባሉ ቀናት፣ ወግ አጥባቂ በሚባለው የታንዛኒያ ማኅበረሰብ፣ ክስተቱ ከፍተኛ ድንጋጤና ቁጣን ፈጥሯል።

በታንዛኒያ ከቅርብ ጊዜ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት እየተባባሰ መጥቷል። ከጥቃቶቹ ብዙዎቹ ለፖሊስ ሪፖርት አይደረጉም።

ይህ የደቦ ወሲባዊ ጥቃት ቪዲዮ በማን እንደተቀረጸ ባይታወቅም ተጠቂዋ የዮምቦ ዶያ ሰፈር ልጅ እንደሆነች ታውቋል። ዮምቦ ዶያ ከዳሬሰላም ወጣ ብላ የምትገኝ ቦታ ናት።

ፖሊስ በጉዳዩ ላይ የያዘው ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ማኅበረሰቡ በትእግስት እንዲጠብቅ ተማጽኗል።

የመብት ተሟጋቾችና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች የታንዛኒያ ባለሥልጣናት ምርመራው በፍጥነት ተካሄዶ በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ ግፊት እያደረጉ ነው።

የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሐማድ ማሳውኒ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቁመው፣ ነገር ግን ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።