በአልጄሪያዊቷ ቦክሰኛ የፆታ ውዝግብ የፑቲን እጅ አለበት?

ታይዋናዊቷ ሊን ዩ እና አልጄሪያዊቷ ኢማኔ ኸሊፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ታይዋናዊቷ ሊን ዩ እና አልጄሪያዊቷ ኢማኔ ኸሊፍ

የፓሪስ ኦሊምፒክ ከተከፈተ በሳምንቱ ውዝግብ ገጥሞታል።

የአልጄሪያዊቷ ኢማኔ ኸሊፍ የፆታ ጉዳይ ከዶናልድ ትራምፕ እስከ ዝነኛዋ ደራሲ ጄ ኬ ሮሊንግ ድረስ ዓለምን አንጫጭቷል።

ከአልጄሪያዊቷ ኢማኔ ሌላ ታይዋናዊቷ ሊን ዩ ቲንግ እና የፆታቸው ጉዳይ አብሮ ይነሳል።

ለመሆኑ ይህ ውዝግብ ከሩሲያ ጋር ምን አገናኘው? የፑቲንስ ስም ለምን ተነሳ?

የቦክስ ማኅበሩና የሩሲያ ተጽእኖ

አልጄሪያዊቷ ኢማኔ እና ታይዋናዊቷ ሊን ለጊዜው የነሐስ ሜዳሊያ እንደሚያገኙ አረጋግጠዋል። መጪዎቹን ውድድሮች ካሸነፉ ደግሞ ወደ ወርቅ ወይም ብር ሜዳሊያ ያመሩ ይሆናል።

ሁለቱን አትሌቶች ባለፈው ዓመት ከዓለም የቦክስ ሻምፒዮና ውድድር ያገዳቸው ማን ነው? የሚለው ቁልፍ ነጥብ ነው።

በሁለቱ አትሌቶች ላይ እገዳ ጥሎ የነበረው የዓለም አቀፉ ቦክስ ማኅበር ወይም በእንግሊዝኛ ምሕጻሩ አይቢኤ (IBA) ነው።

አይቢኤ ለምን እነዚህን ሴት አትሌቶች ባለፈው ዓመት ከውድድር አገድካቸው ሲባል “የፆታ ምርመራ ማለፍ ስላልቻሉ” የሚል ድፍን ያለ መልስ ሰጠ።

ማስረጃ ቢባል ተቁለጨለጨ።

ሰኞ ዕለት ትርምስምሱ የወጣ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠውአይቢኤ “በቅርቡ ዝርዝር ማስረጃ አቀርባለሁ” ሲል ቃል ገብቶ ጋዜጣዊ መግለጫውን ዘጋው።

ይህ የአይቢኤ ጋዜጣዊ መግለጫ ብዙ ጥያቄዎችን ለኮሰ።

የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ወይም (አይኦሲ) በበኩሉ በዓለም ቦክስ ማኅበር ላይ እምነት እንደሌለው ገለጸ።

ከዚያ ባለፈ የዓለም ቦክስ ማኅበር (አይቢኤ) “በፖለቲካ የተተበተበ ነው” ሲል ወረፈው።

ይህ ወቀሳ ምናልባት የዓለም ቦክስ ማኅበርን የሚመሩት ሰው ዜግነት ጉዳይ ጋር መያያዝ ጀመረ።

የዓለም ቦክስ ማኅበርን የሚመሩት ሰው ሩሲያዊ ናቸው።

ይህ ብቻም አይደለም። የዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የዓለም ቦክስ ማኅበርን ካለፈው ዓመት ሰኔ ጀምሮ በከፊል እውቅና ነስቶታል።

ይህም የሆነው አይቢኤ የሚተዳደርበት መንገድ ግልጽ እና ተጠያቂነት ያልሰፈነበት ስለሆነ ነው ብሏል።

በሁለቱ የስፖርት አስተዳዳሪ ተቋማት መካከል ያለው ውዝግብ መነሻ ምንድነው?

ምናልባት ፖለቲካዊ አንድምታ ይኖረው ይሆን?

አይቢኤ (IBA) ማን ነው?

አይቢኤ በአውሮፓውያኑ 1946 ነው የተመሠረተው። በቀድሞ ስሙ ኤአይቢኤ (AIBA) ይባላል።

የዓለም አማተር ቦክስ ውድድርን የሚያስተዳድረው ይኸው አካል ነው።

ዓለም አቀፍ የኦሊምፒክ ኮሚቴ እስከ አውሮፓውያኑ 2019 ድረስ ሙሉ እውቅና ለአይቢኤ ይሰጥ ነበር።

ከዚያ ወዲያ ለምን እውቅና ነፈገው?

ዋናው ምክንያት አይቢኤ በሙስና በመጨማለቁ ነው። ነገሩ እየባሰ ከሄደ የዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቦክስን በ2028 ከኦሊምፒክ ላስወግደው እችላለሁ ሲልም እስከመዛት ደርሷል።

የአይቢኤ (IBA) መሪዎች እነማን ናቸው?

በ2018 አይቢኤ በቀድሞው የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ሲኬ ዉ እና በቀድሞው የማኅበሩ ዳይሬክተር ሆ ኪም ላይ የዕድሜ ልክ ዕግድ አውጥቶባቸዋል።

ሲኬ ዉን የተኩት ሰው ጋፉር ራኪሞቭ ይባላሉ። የአሜሪካ ግምጃ ቤት እኚህን ሰው “የወንበዴዎች ቡድን መሪ” በሚል መግለጫ አውጥቶባቸው ነበር።

ከዚያ በኋላ በ2020 ሩሲያዊው ኡማር ክሬምሌቭ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ።

ኡማር ክሬምሌቭ እና ፑቲን

የአይቢኤ ፕሬዝዳንት ክሬምሌቭ ከፑቲን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአይቢኤ ፕሬዝዳንት ክሬምሌቭ ከፑቲን ጋር

ክሬምሌቭ ለክሬምሊን ቤተ መንግሥት ቅርብ እንደሆኑ ይነገራል።

በእርሳቸው ጊዜ አይቢኤ ከሩሲያ ከፍተኛ ድጋፍ ይደረግለት ጀመረ።

የሩሲያ ነዳጅ ድርጅት ጋዝፕሮም የቦክስ ማኅበሩን ስፖንሰር ያደርጋል።

ይህ ምዕራባውያንን ሊያስደስት አልቻለም።

በግንቦት 2022 ክሬምሌቭ በድጋሚ ተመረጡ።

ተቀናቃኛቸው የደች ዜጋ የነበሩት ቦሪስ ቫን ደር ለውድድሩ ብቁ አይደሉም ተባሉ።

በኋላ ላይ ፍርድ ቤት የቦሪስ ቫን ደር እግድ ልክ አልነበረም ሲል ብይን ሰጠ።

ከዚህ በኋላ የዓለም ኦሊምፒክ ኮሜቴ የአይቢኤ ነገር አሳስቦኛል አለ። ቫን ደር በበኩላቸው በዚህ አካሄድ ቦክስ ከኦሊምፒክ ሊታገድ ይችላል አሉ።

ባለፈው ዓመት የዓለም ቦክስ ሻምፒዮን ተካሄደ።

የሴቶች በሕንድ፣ የወንዶች ደግሞ በኡዝቤኪስታን።

ዩናይትድ ኪንግደምን እና አሜሪካንን ጨምሮ 19 አገራት አንሳተፍም አሉ።

ለምን ሲባሉ አይቢኤ የሩሲያ እና የቤላሩስ ተወዳዳሪዎች አገራቸውን ወክለው ባንዲራቸውን ይዘው መወዳደር እንደሚችሉ በመፍቀዱ ተከፍተናል አሉ።

የአይቢኤ ፕሬዝዳንት ይህን ሲሰሙ በእነ አሜሪካ ላይ ተሳለቁ።

“ውድድሩን አንካፈልም ያሉ አገራት ከጀብ ለይቼ አላያቸውም” አሉ። ለምን ሲባሉ “ስፖርትን ከፖለቲካ መለየት ስላልቻሉ” ብለው መለሱ።

ይህ ክስተት በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና በዓለም የቦክስ ማኅበር (አይቢኤ) መካከል ስንጥቅ ፈጠረ።

የአልጄሪያዊቷ ቦክሰኛ ጉዳይ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፈው ዓመት በተደረገው የዓለም ሻምፒዮና አልጄሪያዊቷ ኢማኔ ኸሊፍ ተሳታፊ ነበረች።

ለወርቅ ሜዳሊያ ከቻይናዊቷ ያንግ ሊዩ ጋር ውድድር ለማድረግ አንድ ሰዓት ሲቀራት ያልተጠበቀ መርዶ ተነገራት።

አይቢኤ “የፆታ ምርመራ አላለፍሽም” አላት።

ለወርቅ ሜዳሊያ ውድድር ከማለፏ ቀደም ብሎ የታይላንድን፣ የኡዝቤክን እና የሩሲያን ተወዳዳሪዎች ረታለች።

ስለ ፆታ ምመርመራው አንጀት የሚያርስ መረጃ የለም።

ቢቢሲ ይህን ዘገባ እስካጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በፆታ ምርመራ ሂደት ዙርያ መረጃ ለማግኘት ሞክሮ አልተሳካለትም። ምርመራው ምን ምን ያካትታል የሚለውን የሚያውቅ የለም።

የስፖርት አርታኢው ዳን ሮን ከኤይቢኤ ከፍተኛ ኃላፊ ክሪስ ሮበርትስ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር። በአማኒ ኸሊፍ ምርመራ ወቅት የኤክስዋይ ክሮሞዞም [ፆታን አመልካች] መገኘቱን ተናግረዋል።

ነገር ግን ይህ ማለት ኢማኔ ወንድ ናት ማለት አይደለም።

ከዚያ ቀደም በኢንታንቡል ምርመራ ያደረገችው ኢማኔ ከውድድር አልታገደችም።

የኤቢኤ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ምርመራው የተወዳዳሪዎችን ቴስቶስትሮን መጠንን የሚለካ ነው ብለዋል።

ቴስቴስትሮን የሆርሞን ዓይነት ሲሆን የጡንቻን መጠን እና ጥንካሬን የመጨመር አቅም አለው። ክሮሞዞም በበኩሉ ፆታን ይወስናል።

የአይቢኤ ፕሬዝዳንት ኢማኔ ከፍ ያለ መጠን ያለው ቴስቶስቴሮን እንዳላት በምርመራ ተረጋግጧል ነው የሚሉት።

ጨምረውም ተወዳዳሪዎች ሴት ሆነን ነው የተወለድነው ካሉ በራሳቸው ምርመራ አድርገው ማረጋገጥ አለባቸው አሉ። ይህ ምን ማለት እንደሆነ አወዛገበ።

አይቢኤ የምርመራ ናሙናውን ወደ ሁለት ላቦራቶሪዎች ልኬ ነው የተረጋገጠው አለ።

ላቦራቶሪዎቹ ደግሞ በዓለም ፀረ-አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ የተመሠከረላቸው ናቸው ሲል ጨምሮ ገለጸ።

የዓለም የፀረ አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ በበኩሉ ስለ ላቦራቶሪዎቹ አላውቅም አለ። “የእኛ ሥራ ከፆታ ልየታ ጋር አይያያዝም” ሲል መሰከረ።

ይህን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ስለ ምርመራው ጥርጣሬ ገብቶኛል አለ።

“ምን ዓይነት የምርመራ ፕሮቶኮል እንደሚከተሉ አናውቅም። ምርመራው ትክክለኛ ይሁን አናውቅም” ሲሉ ቃል ቀባዩ ማርክ አዳምስ ተናገሩ።

ባለፈው ሐሙስ ደግሞ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ኢማኔ ኸሊፍ እና ሊ “የአይቢኤ ዝርክርክነት ተጠቂዎች ሆነዋል” ሲል አትሌቶቹን ተከላክሎ ማኅበሩን በይፋ ወቀሰ።

በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ዋነኛ መነጋገሪያ የሆነው እና በ46 ሰከንዶች በአልጄሪያዊቷ ኢማኔ አሸናፊነት የተጠናቀቀው ውድድር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ዋነኛ መነጋገሪያ የሆነው እና በ46 ሰከንዶች በአልጄሪያዊቷ ኢማኔ አሸናፊነት የተጠናቀቀው ውድድር

የአይቢኤ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?

በሰኔ 2023 ከዓለም 70 የኦሊምፒክ ፌዴሬሽኖች 69 የሚሆኑት አይቢኤ እውቅናው ይነጠቅ ሲሉ ድምጽ ሰጡ።

ከድምጽ መስጠቱ በፊት ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ቶማስ ባህ እንዲህ አሉ። “እኛ ከቦክስ ስፖርት ጋር ጸብ የለንም። ከቦክሰኞችም ጋር ችግር የለብንም፤ ችግራችን ከማኀበሩ ነው።”

አይቢኤ በበኩሉ የኦሊምፒክ ኮሚቴን ውሳኔ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጀርመን ድርጊት ጋር አመሳሰለው።

አዲስ የቦክስ ማኅበር?

አይቢኤ በዚህ ቀውስ ውስጥ ሳለ፣ ዎርልድ ቦክሲንግ የሚባል አዲስ ማኅበር በሚያዝያ 2023 (እአአ) ተመሠረተ።

አዲሱ ማኅበር ቦክስ ከኦሊምፒክ እንዳይገለል እንደሚሠራ አስታወቀ።

አዲሱ ማኅበር ከታላቋ ብሪታኒያ፣ ከጀርመን፣ ከኔዘርላንድስ፣ ከኒውዚላንድ፣ ከፊሊፒንስ፣ ከስዊድ እና ከአሜሪካ እውቅና እና ድጋፍ ተችሮታል።

አይቢኤ የዚህን አዲስ ማኅበር መቋቋም ክፉኛ ኮንኗል።

አሁን ቦክስ ስፖርትን የሚያስተዳድረው ማን ነው?

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ቦክስን የመራው የዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ ነው። ይህ ከዚያ ቀደም ሆኖ አያውቅም።

በ2019 ኮሚቴው የምርመራ ጉዳዮችን በሙሉ ለዓለም አቀፉ ቴስቲንግ ኤጀንሲ (አይቲኤ) አስተላለፈ።

የኦሊምፒክ ኮሚቴው ከአበረታች መድኃኒት ጋር ምንም ርህራሄ የለኝም ሲል አሰታወቀ።

አይቲኤ የጤና ምርመራ ሲያደርግ የቴስቶስትሮን መጠንም ይመረምራል።

የኦሊምፒክ ኮሚቴ በፆታ ለውጥ ላይ ያለው አቋም ምንድነው?

በ2021 ኮሚቴው አዲስ ደንብ አርቅቋል።

የሴቶች ውድድርን በተመለከተ ፆታ የቀይሩ አትሌቶች መወዳደር ይችላሉ ወይስ አይችሉም? የሚለውን የመወሰን ሥልጣኑን ለየአገራት ፌዴሬሽኖች አስተላልፏል።

ይህ ማለት አገራቱ ስለሚያሰልፏቸው አትሌቶች ኃላፊነት ይወስዳሉ።

ይህ ውሳኔ የመጣው በቶኪዮ ኦሊምፒክ የመጀመርያዋ ፆታውን ወደ ሴት የቀየረ የክብደት ማንሳት ተወዳዳሪ በሴቶች ውድድር መሳተፉን/መሳተፏን ተከትሎ ነው።

የኦሊምፒክ ኮሚቴው ፆታ ቀይሮ መወዳደር ፍትሐዊ ያልሆነ ዕድል ለተወዳዳሪው (ዋ) ይሰጣል በሚለው ጉዳይ ላይ ቁርጥ ያለ አቋም ባይዝም፤ ጉዳዩን የተመለከተ 10 ነጥቦችን የያዘ ሰነድ ከፓሪስ ኦሊምፒክ በፊት ለፌዴሬሽኖች ልኳል።

ከዚያ ወዲህ በርካታ ስፖርቶች ከወንድ ወደ ሴት ፆታ የቀየሩ ተወዳዳሪዎችን ከራግቢ፣ ከአትሌቲክስ ወዘተ ውድድሮች ክልከላ ተደርጎባቸዋል።

ይሁንና ደንቡ በተለያየ መንገድ ስለሚተረጎም አሁንም ከወንድ ወደ ሴት ፆታ የቀየሩ ተወዳዳሪዎች ተሳትፎ ያደርጋሉ።

ቦክስ ከእነዚህ አንዱ ነው።

ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ወዲህ በቦክስ ስፖርት ፆታ የቀየረ መሳተፍ ይችላል ወይ? የሚለው ደንብ ላይ ማሻሻያ አልተደረገም።

ቦክስን በተመለከተ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚለው ተወዳዳሪዎች ፓስፖርታቸው ሴት የሚል ከሆነ በሴት ቦክስ ውድድር መሳተፍ ይችላሉ።

የኮሚቴው ደንብ እንዲህ ይነበባል።

“የዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቅድመ ሁኔታን ያሟላ ማንኛውም አትሌት በውድድሮች እንዲሳተፍ ይፈቅዳል፤ በኢንተርናሽናል ፌዴሬሽኖቻቸው እስከተፈቀደላቸው ድረስ ይሳተፋሉ። የዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ አትሌቶች በፆታ ማንነት ላይ መድሎ አያደርግም።”

አልጄሪያዊቷ ኢማኔ የተወለደችው ሴት ሆና ነው። ያደገችውም እንደዚያው ነው። ፓስፖርቷም የሚለው የሚያመለክተው ፆታዋ “ሴት” የሚል ነው።

ምናልባት ቁርጥ ያልሆነው የቴስቴስትሮኗ መጠን ብቻ ነው።

ኢማኔ በሁለት ኃያላን የስፖርት ተቋማት የፖለቲካ፣ የባሕል እና የአስተሳብ ፍትጊያ ሰለባ ሆና ይሆን?