“በፆታዋ ምክንያት” በማኅበራዊ ሚድያ መነጋገሪያ የሆነችው ቦክሰኛ ኢማን ኼሊፍ ተጋጣሚዋን በ46 ሰከንድ አሸነፈች

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
ጣሊያናዊቷ ቦክሰኛ አንጅላ ካሪኒ ከአልጄሪያዊቷ ተጋጣሚዋ ኢምና ኼሌፍ ጋር በነበራት ግጥሚያ “ሕይወቴን መጠበቅ አለብኝ” በሚል ምክንያት በ46 ሰከንድ ሽንፈቷን ተቀብላ ግጥሚያዋን አቋርጣ ወጣች።
ኼሊፍ ባለፈው ዓመት የዓለም ሻምፒዮና መስፈርት አያሟሉም ተብለው ከተሰረዙ ቦክሰኞች መካከል ስትሆን በዘንድሮው የፓሪስ ኦሊምፒክ እንዲሳተፉ ከተፈቀደላቸው ሁለት አትሌቶች አንዷ ሆናለች።
ኼሊፍ ሕንድ በተዘጋጀው የዓለም ሻምፒዮና እንዳትሳተፍ የተደረገው የቴስቴስትሮን መጠኗ ከፍ ያለ ነው በሚል ነው።
ነገር ግን በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክስ ኮሚቴ በሚያዘጋጀው የፓሪስ ኦሊምፒክ የቦክስ ውድድር ላይ እንድትሳተፍ ተፈቅዶላታል።
የ25 ዓመቷ አልጄሪያዊት ባለፈው የቶኪዮ ኦሊምፒክስ መሳተፏ ይታወሳል።
የተፈጠረው ምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በመጀመሪያዎቹ 30 ሰከንዶች ከኼሊፍ ቡጢ የቀመሰችው ካሪኒ ወደ ማዕዘኑ በመሄድ ከአሠልጣኟ ጋር ማውራት ጀመረች። ወደ መጋጠሚያው መድረክ ከተመለሰች ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ ወደ ማዕዘኑ ዳግም ተመልሳ ቡጢውን እንደማትቀጥል አሳወቀች።
ዳኛው የኼሊፍን እጅ አንስተው አሸናፊ መሆኗን ከማወጃቸው በፊት ካሪኒ “ይሄ ትክክል አይደለም” ስትል ትሰማለች።
ጣሊያናዊቷ ቦክሰኛ በመድረኩ ላይ ሳለችም ሆነ ከውድድሩ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ስትሰጥ እያነባች ነበር።
“ግጥሚያውን ማጠናቀቅ አልቻልኩም። አፍንጫዬ ላይ ከፍተኛ ህመም ሲሰማኝ አገሬ እንዳይከፋት፣ አባቴ እንዳይከፋው እያልኩ ለራሴ ስናገር ነበር። ነገር ግን አቆምኩ” ስትል ካሪኒ ለቢቢሲ ስፖርት ተናግራለች።
“በሕይወቴ ትልቁ ግጥሚያ ሊሆን ይችል ነበር። ቢሆንም ሕይወቴን መጠበቅ አለብኝ። ፍርሀት የለብኝም። መጋጠሚያውን ሜዳ አልፈራውም። ነገር ግን መቀጠል ስላልቻልኩ ማቋረጥ ነበረብኝ።”
የጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ “ሁሉም በዕኩል ሜዳ መወዳደር አለበት። እኔ በበኩሌ ይህ ግጥሚያ በዕኩል ሜዳ ተደርጓል ብዬ አላስብም” ሲሉ ለአገራቸው መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ስለኼሊፍ የተጠየቀችው ካሪኒ “እስከመጨረሻው እንድትቀጥል መልካም ምኞቴ ነው። ደስተኛ እንድትሆን እፈልጋለሁ። እኔ እዚህ የመጣሁት ሰዎችን ለመኮነን አይደለም” ብላለች።
በቦክሰኝነት ሕይወት 50 ውድድሮች አድርጋ በ9 ግጥሚያዎች የተሸነፈችው ኼሊፍ “እኔ እዚህ የመጣሁት ወርቅ ለመወሰድ ነው። ማንንም እገጥማለሁ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
የአልጄሪያ ኦሊምፒክ ኮሚቲ ኼሊፍን በተመለከተ እየተነዙ ያሉ ወሬዎች “እርባና ቢሶች” ናቸው የሚል መግለጫ ባወጣ በማግስቱ ነው ይህ የተፈጠረው።
የኦሊምፒክ ኮሚቴ ቃል አቀባይ ማርክ አደምስ ግልጽ መሆን ያለበት የአትሌቷ ጉዳይ ከፆታ መቀየር ጋር የተያያዘ አይደለም ብለዋል።
“የተሳሳቱ ሪፖርቶች እየተመለከትን ነው። ግልጽ መሆን ያለበት ወሳኝ ነገር የአትሌቷ ፆታ የመቀየር ሪፖርት ስህተት ነው” ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና የፆታ መስፈርት አላሟላችም ተብላ ያገኘችውን የነሐስ ሜዳሊያ የተነጠቀችው የታይዋኗ ሊን ዩ-ቲንግ ዛሬ አርብ በፓሪስ ኦሊምፒክ ትጋጠማለች።
ዓለም አቀፍ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በፓሪስ የሚወዳደሩ ሁሉም ቦክሰኞች “ውድድሩ የሚጠይቀውን መስፈርት ሁሉ ያሟላሉ፤ መመሪያንም ተከትለው ነው የሚወዳደሩት” ብሏል።
ዓለም አቀፉ የቦክስ ማኅበር
በአውሮፓውያኑ 2023 የዓለም ሻምፒዮና ያዘጋጀው ዓለም አቀፉ የቦክስ ማኅበር ሁለቱን አትሌቶች አግዶ ነበር። ነገር ግን በኦሊምፒክ የሚዘጋጀውን የቦክስ ውድድር የሚያሰናዳው የኦሊምፒክ ኮሚቴ ነው።
ረቡዕ ዕለት መግለጫ ያወጣው የቦክስ ማኅበር “ሁለቱ ተወዳዳሪዎች የታገዱት ስፖርቱ የሚጠይቀውን ፍትሐዊነትን እና ክብርን ለመጠበቅ ነው” ብሏል።
የኦሊምፒክ ኮሚቲ ደግሞ ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ ዓለም አቀፍ የቦክስ ማኅበርን ወቅሶ ኼሊፍ እና ሊን “የማኅበሩ ድንገተኛ ውሳኔ ሰለባዎች ናቸው” ብሏል።
“በ2023 የዓለም ሻምፒዮና መጠናቀቂያ አካባቢ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ከውድድሩ እንዲታገዱ ተደርጓል” ብሏል ኦሊምፒክ ኮሚቴ።
ኼሊፍ ቅዳሜ ዕለት በ66 ኪሎ ግራም የሩብ ፍፃሜ ውድድር ሃንጋሪያዊቷ አና ሉካ ሀሞሪን ትገጥማለች።
“የፆታዋ ጉዳይ” በማኅበራዊ ሚድያ መነጋጋሪያ የሆነው ኼሊፍ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ግጥሚያ ካሸነፈች በቦክስ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ትሆናለች።












