ከአሜሪካ ሰማይ ተመትታ የወደቀችው የቻይናዋ ሰላይ ፊኛ መረጃ አልሰበሰበችም ተባለ

የፎቶው ባለመብት, US NAVY
በአሜሪካ ሰማይ ላይ ከታየች በኋላ ተመትታ እንድትወድቅ የተደረገችው የቻይናዋ ሰላይ ፊኛ ምንም አይነት መረጃ አለመሰብሰቧን ፔንታጎን አስታወቀ።
የስለላ ተግባር ስትፈጽም ነበር የተባለችው ፊኛ የሰበሰበችው መረጃ መኖሩን ለማረጋገጥ የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት ስብርባሪውን በቅርበት ሲመረምሩ ቆይተዋል።
የቻይና የስለላ ፊኛ በአሜሪካ ሰማይ መታየቷ እንዲሁም በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተመትታ እንድትወድቅ መደረጓ በቤይጂንግ እና በዋሽንግተን መካከል ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ቅራኔን ፈጥሮ ነበር።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ብርጋዲዬር ጀነራል ፓትሪክ ራይደር ትናንት ሐሙስ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ፤ “ፊኛዋ የደኅንነት መረጃዎችን መሰብሰብ እንደምትችል እናውቃለን” ብለዋል።
“ይሁን እንጂ አሁን ባደረግነው ማጣራት አሜሪካን እያቋረጠች ወይም በአሜሪካ ሰማይ ላይ እየበረረች (ፊኛዋ) ምንም አይነት መረጃ አልሰበሰበችም” ብለዋል ቃል አቀባይ ብርጋዲዬር ጀነራል ፓትሪክ ራይደር።
ዎል ስትሪት ጆርናል በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ይህ የቻይና በራሪ አካል የተሰራው አሜሪካ ሰራሽ ከሆነ ቁስ ጨምር ነው ብሏል። የፔንታጎን ቃል አቀባይ ግን በዚህ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የቻይናዋ ፊኛ ተመትታ ከመውደቋ በፊት የካቲት ወር ላይ ለአንድ ሳምንት ያክል በአሜሪካ እና ካናዳ የአየር ክልሎች ላይ ስትበር ቆይታለች።
ፊኛዋ በመንገዷ በአሜሪካ የጦር ካምፖች በላይ በመብረሯ የደኅንነት መረጃዎችን ሳትሰበስብ አትቀርም የሚል ሰፊ ግምት ነበር።
ቻይና ግን ፊኛዋ የደኅንነት መረጃዎችን የምትሰብሰብ ሳትሆን ለአየር ትንበያ የምርምር ሥራ የምትሰራ መሆኗን እንዲሁም ወደ ሰሜን አሜሪካ የሄደችው በንፋስ ኃይል ተገፍታ መሆኑን ስትገልጽ ቆይታለች።
ቻይና ይህን ትበል እንጂ አሁንም የቻይና ናቸው የተባሉ ሌሎች የስለላ ፊኛዎች በእስያ ሰማዮች ላይ ታይተዋል።
ጃፓን ፊኛዎች በግዛቷ ሲበሩ መመልከቷን ያረጋገጠች ሲሆን፣ ወደፊትም ፊኛዎቹን መትታ ለመጣል መዘጋጀቷን ገልጻለች።
ከጃፓን በተጨማሪ የቻይና ፊኛ በታይዋን ሰማይ መብረሯን የቢቢሲ ፓናሮማ ምርመራ አረጋግጧል።
ጃፓን የአሜሪካ የቅርብ አጋር ስትሆን ከሌሎች የውጭ አገራት በበለጠ በርካታ የአሜሪካ ኃይሎች በጃፓን ሰፍረው ይገኛሉ።












