በኢትዮጵያ እያጋጠሙ ያሉት ግጭቶች ወዴት ሊያመሩ ይችላሉ?

የፎቶው ባለመብት, EPA
ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ ግጭቶች፣ ግድያዎች እና መፈናቀሎች በየአካባቢው ሲፈነዱ ቆይተዋል።
አንዳንዴ በተመሳሳይ ሰዓት በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ይከሰታሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ አንደኛው የአገሪቱ አካባቢ በግጭት ሲታመስ ሌላው አካባቢ በአንጻራዊ ሁኔታ የተረጋጋ ይሆናል።
ሁለት ዓመታት የፈጀው ደም አፋሳሽ ጦርነት ተጠናቀቀ ሲባል ደግሞ ሌላ ግጭት ዓይነቱን እና መልኩን ቀይሮ ይከሰታል።
ለእነዚህ ግጭቶች እና ጥቃቶች የተለያዩ ምክንያቶች ሲነገሩ ይሰማል።
አንድ ቦታ የተለያየ ማንነት ያላቸው ወገኖች በትንሽ አለመግባባት ወደ ግጭት ሲገቡ፣ ሌላ ቦታ በፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ግጭቶች ይፈጠራሉ።
መረጋጋት ተገኘ ሲባል ደግሞ ሕግ በማስከበር እና በትጥቅ መፍታት አለመፍታት ሰበብ ሌላ ግጭት ሌላ ቦታ ይጠነሰሳል።
እነዚህ ባለፉት ዓመታት የተከሰቱት ግጭቶች ባስከተሏቸው ከፍተኛ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና ንብረት ውድመት ምክንያት ስጋት ተፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ለሆኑት አቶ ያሬድ ኃይለማርያም የእነዚህ ግጭቶች ምክንያቶች መልከ ብዙ ናቸው።
በመንግሥት ተቋማት እና በመንግሥት አካላት ጭምር ስህተት ነው የሚሏቸው ሥራዎች ተከናውነዋል። የብሔር ማንነትን አግዝፎ ከማየት ባለፈ፣ አንዳንዴም የፖሊሲያቸው አካል ማድረጋቸውን ያነሳሉ።
“ሕገ መንግሥቱን መነሻ በማድረግ ልዩነትን የሚያገዝፍ የፖለቲካ ሥርዓት ነው ያለው። የፖለቲካ ስሪቱ አወቃቀርም አንድነትን፣ ማኅበረሰባዊ መቀራረብን የሚያመጣ ሳይሆን ልዩነቶችን ማዕከል ያደረገ ነው” ይላሉ።
አንዳንዴ ፖለቲከኞች ለራሳቸው ግብ ሲሉ የተሳሳቱ ትርክቶችን እንደ እውነት ማቅረብ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥቃቅን የታሪክ ስህተቶችን አግዝፎ ማቅረብ መኖሩን ያወሳሉ።
በታሪክ የተፈጸሙ ስህተቶችን በመጠቀም ሌላውን እንደ ጠላት ቆጥሮ የእኔ ከሚሉት ማኅበረሰብ የፖለቲካ ትርፍ ማግኘትም መለመዱን ይጠቅሳሉ።
ይህ አካሄድ ለ30 ዓመታት ገደማ ሲንከባለል መጥቶ አሁን አገሪቷ ውስጥ ማኅበረሰቡን አስተሳስረው ያቆዩ የአንድነት ገመዶች በጠቅላላ እየተበጣጠሱ መቻቻል፣ መተሳሰብ እና የአንድነት ስሜት እንዲጠፋ አድርጓል ይላሉ አቶ ያሬድ።
በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፖለቲካል ሳይንስ ውስጥ አጥኚ የሆኑት መብራቱ ከለቻ (ዶ/ር) ደግሞ ለግጭቶች መባባስ የፖለቲካ ፉክክር እና የሥልጣን ሽኩቻ በሌላ ምክንያትነት ያነሱታል።
የብሔር እና የእምነት ልዩነቶችም አንዳንዴ ግጭቶች እንዲከሰቱ ምክንያት እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ያለው አለመረጋጋትም ድንበር በመሻገር የአገሪቱ የግጭት ምንጭ የሚሆንበት አጋጣሚ የሚሆንበት አጋጣሚም አለ።
አገሪቱ ባለፉት አስርታት የተከተለችው መንገድ የግጭት ምንጭ እየሆነ መጥቷል የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ጥናታቸውን እያደረጉ ያሉት እና በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ኃይሉ ናቸው።
አገሪቱን በመግባባት ላይ ለመገንባት አለመሞከሩ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች እንዲፈጠሩ ምክንያት ከመሆን ባለፈ፣ በየአምስት ወይም በየአስር ዓመቱ ጦርነት፣ ግጭት እና አመጽ እንዲነሳ መንገድ መክፈቱን ይጠቅሳሉ።
ለረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ኢኮኖሚያዊ ችግርም እንደምክንያት መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው።
የአገሪቷ ኢኮኖሚ በቂ ሥራ ለወጣቶች አለመፍጠሩ ወደ ትጥቅ እና ግጭት እንዲያዘነብሉ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።
አብዛኛውን የሕዝብ ቁጥር የሚሸፍኑት ወጣቶች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተመረቁ የሥራ ዕድል ባለማግኘታቸው ግጭቶች ውስጥ በቀጥታ እየተሳተፉበት መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የአገሪቷን ዜጎች በኢኮኖሚ በእኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት አልተገነባም የሚሉት ሽመልስ “ድሮ ወጣቶች ሥራ ካጡ ፖሊስ ይሆናሉ፣ አሁን ግን ከፖሊስ ጋር ይጋጫሉ። አንዳንድ የመብት ጥያቄ ቢኖራቸውም የኢኮኖሚ ጉዳይ ግጭትን ያነሳሳል ብዬ አምናለሁ። ለግጭት ምክንያት በሚሆኑ ተግባራት ውስጥ በቀላሉ ይሳተፋሉ” ብለዋል።
መንግሥት ለምን ግጭቶችን መቆጣጠር አዳገተው?
መንግሥት ግጭቶችን ለመቆጣጠር ከሰው ኃይል ጋር በተያያዘ ችግር እንደሌለበት አቶ ያሬድ ያነሳሉ። ሠራዊት በማዝመት ጦርነት ውስጥ መግባት መቻሉን እና በየጊዜው በርካታ ሠራዊት ማሰልጠኑን ከግምት በማስገባት ከሰው ኃይል ጋር የተያያዘ “ችግር ያለ አይመስለኝም” ይላሉ።
ነገር ግን የፖለቲካ አመራር አቅም ማነስ ግን በግልጽ እንደሚታይ ይጠቁማሉ። “ያሉትን ችግሮች በቀላሉ መቆጣጠር፣ አደጋ አመላካች የሆኑ አሠራሮችን ተጠቅሞ በወቅቱ ምላሽ መስጠት እና የፖለቲካ አመራር ችግር በግልጽ ይታያል።”
ሰፊ የፖለቲካ መዋቅር ቢኖረውም በመዋቅሩ ውስጥ ካለፈው ሥርዓት ተንከባሎ የመጣ ችግር፣ ያለመናበብ (ፌደራል መንግሥቱ የሚያድርገውን የክልል መንግሥታት ሲጥሱ ይታያል)፣ በክልሎች መካከል ፉክክር እና መገፋፋት መኖሩ ነገሩን የበለጠ እንዲገዝፍ አድርጎታ ብለዋል።
እንደ አቶ ያሬድ በመንግሥት በኩል እነዚህ እየተደጋገሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑን “በሚያሳዝን ሁኔታ ጥረት የማድረግ ምልክቶች እንኳን አይታዩም” ይላሉ።
“አንዳንዴም የሚፈጠሩ ችግሮች በመንግሥት እውቅና አይሰጣቸውም። ለምሳሌ በቅርቡ ወደ 50 የሚጠጉ ሾፌሮች መንገድ ላይ ታፍነዋል። ግን አንድም የመንግሥት አካል ምንም አላለም። ይሄ በጣም ችግር ነው። ስለዚህ ለችግሮቹም ተገቢውን ዕውቅና ያለመስጠት ችግር በደንብ ጎልቶ ነው የሚታየው።”
ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቶችን ማስቆም አቅም አጥቶ ነው ወይስ ሌላ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልገው ያነሳሉ።
በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶችን እና የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት ዙሪያ “በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራም ውስጥ አገሪቱን የሚያስተዳድሩበት ስምምነት ያለ አይመስልም” ሲሉ ይገልጻሉ።
ዶ/ር መብራቱ ደግሞ ደካማ መንግሥታዊ ተቋማትን እንዱሁም የብሔር ጽንፈኝነትን ለሚያጋጥሙት ግጭቶች እና ውጥረቶች በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።
በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ በመንግሥት ላይ እምነት አለመኖር፣ የሃብት እና የአቅም ውሱንነት ከመኖሩም በላይ፣ አንዳንዴም የውጭ መንግሥታት ወይንም ታጣቂዎች የሚያደርጉት ድጋፍ ለግጭቶቹ ምክንያት እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሥርዓት አልበኝነት እየነገሰ ነው?
መንግሥታት ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም እና የሕግ የበላይነትን የማስጠበቅ ኃላፊነት በሕግ ጭምር የተሰጣቸው የሥልጣን አካላት ናቸው።
ይህንን ኃላፊነት መንግሥታት አይጠቀሙበትም ወይንም ደግሞ በተሳሳተ መንገድ ከልክ ባለፈ ሁኔታ ሲጠቀሙበት ይታያል።
ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ያሉ ክልሎች እና ታጣቂዎች ጉልበታቸው ፈርጥሞ በከፍተኛ ሁኔታ ከመታጠቃቸው በተጨማሪ፣ በእራሳቸው መንገድ የሚፈልጉትን ሲፈጽሙ እንዲሁም ግጭት ውስጥ ሲገቡ አጋጥሟል።
ከወራት በፊት የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ህልውና እንዲያበቃ የወሰደው እርምጃ በበርካቶች በአውንታዊ መልኩ የታየ ቢሆንም፣ ከባድ ቀውስን ያስከተሉ ታጣቂ ቡድኖችን ግን መቆጣጠር አልቻለም።
እንዲሁም ክልሎች በተሰጣቸው የሥልጣን ገደብ ውስጥ ብቻ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እምብዛም እርምጃ አልወሰደም የሚሉ አሉ።
ከዚህ አንጻር አቶ ያሬድ አውራ የሚባሉ መንገዶች በፌደራል መንግሥት ስር መሆናቸውን በምሳሌነት በመጥቀስ “እነዚህን መንገዶች በአንድ ክልል ወይም በታጣቂ ኃይል ሲዘጉ ከፌደራል መንግሥቱ በኩል የሚሰጡ ምላሾች ግን ብዙ አይደሉም” ይላሉ።
አክለውም ይህ በመንግሥት በኩል የሚወሰደው “የላላ እና የተፋዘዘ ሕግን የማስከበር እርምጃ” ግጭቶችን እና ጥቃቶችን እንዳባባሳቸው ይጠቁማሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት ነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የሕግ በላይነትን በማስከበር በጣም የወረደ ዝቅተኛ ሥራ ነው የሠራችሁት። የሕግ በላይነት እያስከበራችሁ አይደለም ብሎ ወቅሷቸው ነበር። አሁንም ግን ለውጥ የለም። ጭራሽ እየባሰበት ነው የመጣው” ብለዋል።
አሁን በየቦታው የሚታየው መልከ ብዙ ግጭት እና ጥቃት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ “የለየለት ሥርዓት አልበኝነት ነው የሚነግሰው” ሲሉ አቶ ያሬድ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
በዚህ ሁኔታ ሕይወት እና ንብረታቸው አደጋ ላይ የሚወድቅባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎችም ራሳቸውን ወደ መከላከል ስለሚያቀኑ “ያ ደግሞ ሌላ ነውጥ፣ ሌላ ቀውስን” በማስከተል ከቁጥጥር ውጪ በመውጣት አገሪቱን ወደ ከባድ አዘቅት ሊያስጋበት ይችላል ይላሉ።
ከዚህ አንጻር ክልሎችም በተናጠል እርምጃ የሚወስዱበት ሁኔታ እንደሚፈጠር በማንሳት ቀደም ሲል በትግራይ የተካሄደውን የሚመስል ጦርነት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ወይም በክልሎች መካከል ላለመከሰቱ ዋስትና እንደማይኖር አቶ ያሬድ ይገልጻሉ።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ሥርዓት አልበኝነት በግልጽ ይታያል” የሚሉት ደግሞ ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ ናቸው። ሰው ከተማ ውስጥ ተገድሎ በሥርዓት ተገቢው ምርምራ እንደማይደረግበት በማንሳት፣ ሰዎች ነጋቸው እንደሚያሳስባቸው እና በፍርሃት እንደሚኖሩ ይናገራሉ።
ከአዲስ አበባ እየተራቀ ሲኬድ የደኅንነት ስጋት እየጨመረ ይሄዳል ካሉ በኋላም፣ የሕይወታቸው መሠረት የሆኑ በሬዎቻቸው በታጣቂዎች ታርደው ተበልቶ ምንም ተጠያቂነት ሳይኖር ስለሚቀሩ አርሶ አደሮች ሁኔታ በምሳሌነት ያነሳሉ።
ምን መደረግ አለበት?
ስለዚህ መፍትሔው የሚሆነው መንግሥት በሕገ መንግሥቱም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕጎች ያሉበትን ግዴታዎች በአግባቡ መወጣት አለበት የሚሉት አቶ ያሬድ፣ ካልሆነ ግን ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ከቁጥጥር ውጪ የሚወጣበት ዕድል ሰፊ ነው።
በአገሪቷ ውስጥ የሚከሰቱትን ግጭቶች እና ጥቃቶችን ለማቀዝቀዝ አገራዊ መግባባት ላይ መሠራት አለበት የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ “አሁን ያለው የፖለቲካ አተያይ መቀየር አለበት። የተለያዩ ፍላጎቶች እና አመለካከቶች ባሉባት አገር፣ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ድርድር መደረግ አለበት። ይህ ካልሆነ ግጭቱ ሊቀጥል እና ሊብስ ይችላል” ሲሉ ያሰምሩበታል።
እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩት ችግሮች በመንግሥት ብቻ እንደማይፈቱ በማንሳት ሌሎችም የራሳቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ይመክራሉ።
ለመብራቱ (ዶ/ር) ደግሞ በርካታ የመፍትሔ አማራጮች ቢኖሩም ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሪፎርም ማድረግ ቀዳሚው ነው።
ግጭት መፍታት እና እርቅ ማውረድ፣ የኢኮኖሚ ልማት እና ፀረ ድህነት ሥራ፣ ሕግ ማስከበር፣ የክልሎች ትብብርን ማሳደግ እና የዓለም አቀፍ አጋሮችን ድጋፍ በመጠቀም ያለውን የፀጥታ ችግር መቀልበስ እንደሚቻል አንስተዋል።
መንግሥትስ ምን ይላል?
በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ቢቢሲ ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።
ሆኖም ገዢው ፓርቲ በተለያዩ አጋጣሚዎች “ከግጭት የሚያተርፉ አካላት” የሚያስጀምሯቸው በሚል ብዙዎቹን ግጭቶች በተመለከተ መግለጫዎችን ማውጣቱን ወደ ኋላ መለስ ብለን ተመልክተናል።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከወራት በፊት መጋቢት መጀመሪያ ላይ ያካሄደውን ስብሰባ ባጠናቀቀበት ወቅት ባወጣው መግለጫ፣ በወቅቱ ከአገሪቱ ሠላም እና ፀጥታ ጋር በተያያዘ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች በዋናነት ከአምስት ነገሮች እንደሚመነጩ አመላክቶ ነበር።
“ታሪክ ካሸከመን ዕዳዎች የሚመነጭ ነው” ብሎ ባስቀመጠው የመጀመሪያው ፈተና ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ውስጥ ያልፈቷቸው፣ ተጨማሪ ችግር አድርገው የጨመሯቸው እና ያልተግባቡባቸው ዕዳዎች እንዳሉ ጠቅሷል።
እነዚህ ዕዳዎች የመነታረኪያ፣ የመጋጫ እና የመከፋፈያ ምክንያቶች ሊሆኑ እንደማይገቡ በመግለጽ “ዕዳዎቹን ወረስናቸው እንጂ አልፈጠርናቸውም፣ መጡብን እንጂ አልሄድንባቸውም” ብሏል በመግለጫው።
“ነጻነትን ለማስተዳደር አለመቻል” ሲል ባስቀመጠው ሁለተኛ ፈተና ላይ በአካባቢ አስተዳደሮች፣ በሚዲያዎች፣ በእምነት ተቋማት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በአክቲቪስቶች አካባቢ የሚስተዋለው ነጻነትን የማስተዳደር ችግር፣ በቶሎ ሊገራ የሚገባው መሆኑን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ይጠቅሷል።
እንዲሁም የአገሪቱን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እየተጠናከሩ መምጣታቸው፣ የኑሮ ውድነት እንዲሁም ሌብነት ተጨማሪ ፈተናዎች ናቸው ሲል ተጨማሪ ምክንያቶችን አስቀምጧል።
በአገሪቱ ከሚከሰቱ ግጭቶች እና የሠላም እጦት አንጻር “ሕግ እያፈረሱ፣ የሌሎችን መብት እየጣሱ፣ ግጭት እና ጥላቻን እየቀሰቀሱ፣ ብሎም አገር እያተራመሱ መንቀሳቀስ ወንጀል እንጂ ነጻነት ሊሆን አይችልም” ሲል አሳስቧል።












